Site icon ETHIO12.COM

ከሰሜን ሸዋ ገዳም አቅራቢያ መሽገው በተያዙ 20 ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

ፍርድ ቤቱ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው ነበር የተባሉ 20 ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ማጣሪያ እንዲደረግ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በመርማሪ ፖሊስ የቀረበ የሽብር ጥርጣሬ መነሻ ምክንያቶችን እና በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል የተነሱ የጊዜ ቀጠሮ መቃወሚያ ነጥቦችን ተመልክቶ ነው ለፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ የሰጠው።

ተጠርጣሪዎቹ አጠቃላይ 20 ሲሆኑ አራቱ ሴቶች ናቸው።

ከተጠርጣሪዎች መካከል የቀድሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባል ነበሩ የተባሉት ም/አ/ አለቃ ታጠቅ ማሞ፣ ኮ/ብል ሽፈራው ሃይሉ፣ ረ/ሳጅን አብርሐም ኃይለ እየሱስ፣ መስፍን ጣልአርጌ፣ ኮ/ብል ቃሉ ግዛቸው፣ ኮ/ብል ጌታሁን ካሀብት ይመር ፣ኮ/ብል ጌታሁን መኮንን እና ም/አ/አለቃ እንዳሻው ግርማ ይገኙበታል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ተጠርጣሪዎቹን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍልና በተለይም በአማራ ክልል የብሔር ፖለቲካ ፅንፈኝነትን መሰረት በማድረግ፣ሕገ-መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስና ሽብር ለመፍጠር በማቀድ ፣የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረብርሃን 10 ኪሎ ሜትር በሚገኝ ሳሪያ ሚካኤል ቀበሌ ልዩ ቦታው ኩክ የለሽ ገዳም ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በ13ኛ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤት መሽገዋል በማለት ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጾ ነበር።

ፖሊስ አክሎም ተጠርጠሪዎቹ 1 ዲሽቃ መሳሪያ ከ501 ጥይት ጋር፣ 4 ስናይፐር፣ 2 ብሬን ከ1 ሺህ 348 ጥይት ጋር፣ 2 ሽጉጥ ፣ 3 ኤፍ አይ የእጅ ቦምብ፣5 ክላሽ ከመሰል 530 ጥይቶች ጋር በመታጠቅ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ ባሳለፍነው ሰኞ በነበረ ቀጠሮ ለችሎቱ ገልጿል።

መርማሪ ፖሊስ በወቅቱ የወረዳው የፀጥታ አካላትና ሚኒሻዎች ፀጉረ ልውጥ እና የታጠቁ ሰዎች ይንቀሳቀሳሉ የሚል ጥቆማ ደርሷቸው ወደመሸጉበት መኖሪያ ቤት ምን እየሰሩ እንደሆነ ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ በከባድ ጦር መሳሪያ ተኩስ በመክፈት ውጊያ በመግጠማቸው ምክንያት ሚኒሻዎቹም መከላከያ ሰራዊት በመጥራት ከእነ ጦር መሳሪያቸው በሰኔ 15 ቀን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል በማለት የጥርጣሬ መነሻውን ዘርዝሮ ለችሎቱ አስረድቶ ነበር።

በዚህም መነሻ በሰኔ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተጠርጣሪዎችን ከመከላከያ በመረከብ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን የገለፀው መርማሪ ፖሊስ ÷በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰውና የምስክር የሰነድ ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለመቅረብ እንዲያስችለው የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ተጠርጣሪዎቹ ለእረፍት ወደ ቤተሰብ ከሄዱ በኋላ አድማ ብተና ውስጥ ትቀላቀላላችሁ ተብለው ፣በሰላማዊ መንገድ ቁጭ ብለው እየተጠባበቁ በነበሩበት ወቅት ነው የተያዙት በማለት የፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ተቃውመዋል።

በተጨማሪም 13ኛ፣16ኛ፣19ኛ እና 21ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ግለሰቦች የልዩ ኃይል አባል እንዳልሆኑ የጠቆሙት ጠበቆቹ÷ የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ተቀምጠው ነው የተያዙት ለሚለው የጠበቆች መከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ በኩክ የለሽ ገዳም አቅራቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ጋር በመመሳሰል በ13 ኛ ተጠርጣሪ ቤት መሽገው እንደነበርና በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው መያዛቸውን ጠቅሶ መልስ ሰጥቶ ነበር።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ መንግስት በየዘርፉ እንዲቀላቀሉ ለክልሉ ልዩ ኃይል ጥሪ ባስተላለፈበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ አንቀበልምብለው ከኢ -መደበኛ አደረጃጀት ጋር በመቀላቀል ከተለያዩ ወረዳዎች በመጠራራት ተሰባስበው ነው ይህን ድርጊት የፈጸሙት በማለት ማብራራቱ ይታወሳል።

ፖሊስ አክሎም ተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ የተያዙ የጦር መሳሪያዎችን በሚመለከት በክልሉ መንግስት ምንም መሳሪያ እንዳላስታጠቃቸው በመግለፅ መሳሪያውን ገዝቶ ያስታጠቃቸው የሎጂስቲክ ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል መጣራት እንዳለበት ጠቅሶ ተከራክሮ ነበር።

በሌላ በኩል ጠበቆቹ ተጠርጣሪዎቹ መሳሪያ ከፊታቸው ተቀምጦ ፎቷቸው ተለጥፎ ንፁህ ሆነው የመገመት መብታቸውን በጣሰ ሁኔታ በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ተሰርቷል ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።

እንዳጠቃላይ የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ አስቀርቦ በመመልከት ክርክሩን መርምሮ ተጨማሪ ማጣራት እንደሚያስፈልግ በማመን የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የ14 ቀን የማጣሪያ ጊዜን ፈቅዷል።

በመገናኛ ብዙሃን ዘገባን በሚመለከት ሽብርተኛ ተብሎ ስም እና ፎቶ ተጠቅሶ የተሰራ ዘገባ አለመኖሩን በማረጋገጥ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያነሱት አቤቱታን አልተቀበለውም።

በታሪክ አዱኛ ፋና

Exit mobile version