በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ የቀድሞ ሃያ አምስት የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አባላት ላይ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው ነበር ተብሎ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 25 ግለሰቦች ላይ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ፈቀደ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በመርማሪ ፖሊስ የተሰሩ የምርመራ ሥራዎችንና በተጠርጣሪ ጠበቆዎች በኩል የተነሱ የጊዜ ቀጠሮ መቃወሚያ ነጥቦችን ተመልክቶ ነው ለፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ የፈቀደው።

ተጠርጣሪዎች የቀድሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባል ነበሩ የተባሉት ም/አ/ አለቃ ታጠቅ ማሞ፣ኮ/ብል ሽፈራው ሀይሉ፣ ረ/ሳጅን አብርሐም ኃይለ እየሱስ፣ ኮ/ብል ቃሉ ግዛቸው፣ኮ/ብል ጌታሁን ካሀብት ይመር ፣ኮ/ብል ጌታሁን መኮንን እና ም/አ/አለቃ እንዳሻው ግርማን ጨምሮ 25 ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ከ14 ቀን በፊት በነበረ ቀጠሮ ተጠርጣሪዎቹን ህገ -መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስና ሽብር ለመፍጠር በማቀድ ፣ በኢ -መደበኛ አደረጃጀት ውስጥ በመቀላቀል ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ከደ/ብርሃን 10 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኝ በ13 ኛ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤት ውስጥ በመመሸግ አንድ ዲሽቃ መሳሪያ ከ501 ጥይት ጋር፣ 4 እስናይፐር መሳሪያ ፣ 2 ብሬን መሳሪያ ከ1 ሺህ 348 ጥይቶች ጋር፣ 5 ክላሽ ከመሰል 530 ጥይቶች ጋር በመታጠቅ በአካባቢው የፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ በመክፈት ጥቃት ማድረሳቸውንና በኋላም በመከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ሰር መዋላቸውን በመጥቀስ የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

በዛሬው ቀጠሮ ደግሞ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ የሰራውን የምርመራ ስራ ለችሎቱ አብራርቷል። በዚህም በወ/መ/ስ/ህ /ቁጥር 30 መሰረት የ12 ሰው የምስክር ቃል መቀበሉን፣ በተጠርጣሪዎች እጅ ተገኝተዋል ያላቸውን ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለምርመራ ለሚመለከተው አካል መላኩን ፣ የገሚሱን ተጠርጣሪዎችን የተከሳሽነት ቃላቸውን መቀበሉን፣ የገንዘብ ዝውውርን ለማጣራት ለ20 ባንኮች ማረጋገጫ መጠየቁን፣ ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት የቴክኒክ ማስረጃ መጠየቁን፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት የሰነድ ማስረጃዎችን መጠየቁን ገልጿል።

ቀረኝ ያላቸውን ማለትም ተጨማሪ የሰው ምስክር ቃል መቀበል፣ የተለያዩ ከተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ በወ/መ/ስ/ህ /ቁጥር 59/2 መሰረት የተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።

See also  ከጤና ሙያ ጋር የተያያዙ ጥፋቶች የአስተዳደርና የፍትሐብሔር ኃላፊነት

በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል ደግሞ የልዩ ኃይል አባል የነበሩ ተጠርጣሪዎች አድማ ብተና ውስጥ ትቀላቀላላችሁ ተብለው ቁጭ ብለው እየተጠባበቁ በነበሩበት ወቅት ነው የተያዙት የሚል መከራከሪያ አንስተዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ ተጠርጣሪዎቹ ልዩ ኃይል በነበሩበት ወቅት ከመንግስት የተሰጣቸው የጦር መሳሪያ እንጂ በግላቸው የያዙት አይደለም በማለት ተከራክረዋል። የደንበኞቻቸው የዋስ መብት እንዲከበርም ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በኩል ግን ተጠርጣሪዎቹ ከፀረሰላም ኃይሎች ጋር ለመቀላቀል ተሰባስበው በነበሩበት ወቅት የአካባቢው ሚሊሻዎች ለምን እንደተሰባሰቡ ለመጠየቅ በተጠጓቸው ወቅት ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊት ከነመሳሪያቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል በማለት ከጠበቆች ለተነሱ መከራከሪያ ነጥቦዎች ላይ መልስ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባል በነበሩበት ወቅት ከተሰጣቸው ክላሽ መሳሪያዎች ውስጥ በሌሎች መሳሪያዎች የቀየሩ መኖራቸውን መረጃ እንዳለው መርማሪ ፖሊስ አብራርቷል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ አስቀርቦ በተሰጠው ጊዜ ፖሊስ የሰራቸው በርካታ የምርመራ ሰራዎች መኖራቸውን በማረጋገጥ እና ተጨማሪ የማጣራት ምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልግ መታመኑን ተከትሎ የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የ14 ቀን የማጣሪያ ጊዜን ፈቅዷል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply