በደብረ ብርሃን ፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

ፍርድ ቤቱ በደብረ ብርሃን ፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው ነበር ተብለው በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ከ25 ግለሰቦች መካከል 21 ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ የ14 ቀን ጊዜ ፈቀደ።

በመዝገቡ የተካተቱ ሌሎች አራት ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ግን ፍርድ ቤቱ በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በመርማሪ ፖሊስ የቀረበ የሽብር ወንጀል የምርመራ ስራዎችን እና በተጠርጣሪ ጠበቃ በኩል የተነሱ የጊዜ ቀጠሮ መቃወሚያ ነጥቦችን መርምሮ ነው በ21 ግለሰቦች ላይ ለፖሊስ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሰጠው። ተጠርጣሪዎቹ አጠቃላይ 25 ሲሆኑ ፥ አራቱ ሴቶች ናቸው።

ከተጠርጣሪዎች መካከል የቀድሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባል ነበሩ የተባሉት ም/አ/ አለቃ ታጠቅ ማሞ፣ ኮ/ብል ሽፈራው ሀይሉ፣ ረ/ሳጅን አብርሐም ኃይለ እየሱስ፣ መስፍን ጣልአርጌ፣ ኮ/ብል ቃሉ ግዛቸው፣ ኮ/ብል ጌታሁን ካሀብት ይመር፣ ኮ/ብል ጌታሁን መኮንን እና ም/አ/አለቃ እንዳሻው ግርማ ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹን ፥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍልና በተለይም በአማራ ክልል የብሔር ፖለቲካ ፅንፈኝነትን መሰረት በማድረግ፣ ህገ-መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስና ሽብር ለመፍጠር በማቀድ፣ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ሰሜን ሸዋ ዞን ደ/ብርሃን 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሳሪያ ሚካኤል ቀበሌ ልዩ ቦታው ኩክ የለሽ ገዳም አካባቢ በ13ኛ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤት ከነጦር መሳሪያቸው በመመሸግና በአካባቢው ሚሊሻዎች ላይ ተኩስ በመክፈት በሰላም ማስከበር ስራ ላይ በነበሩ መከላከያ ሰራዊት አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ የሰራውን የምርመራ ስራ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም የተከሳሾችን ቃል መቀበል ስራ መስራቱን፣ በወ/መ/ስ/ህ /ቁጥር 30 መሰረት የ14 ሰው ምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለፎረንሲክ ምርመራ መላኩን፣ ሁለት ተጠርጣሪዎች ከዚህ በፊት በስነምግባር ችግር ከመከላከያ መባረራቸውን የሚገልጽ ማስረጃ መሰብሰቡን፣ ተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ የተያዙ የቡድንና የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎችን የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር መረከቡን ማረጋገጡን፣ ከተለያዩ ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር መደረጉን የሚገልጹ ማረጋገጫዎችን ማምጣቱን አብራርቷል።

See also  ሰነዶችን በኦንላይን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ከባንኮች ጋር ተፈረመ

ቀሩኝ ያላቸው የተጨማሪ የምስክሮች ቃል የመቀበልና የተለያዩ ቀሪ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ፣ ግብረአበር የመያዝ ስራ እና ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ጠይቋል።

በተጠርጣሪ ጠበቃ በኩል ደግሞ እስካሁን በተሰጠው ጊዜ ፖሊስ አዲስ የምርመራ ስራ አላከናወነም የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦች አንስቷል። ግብረአበር ለመያዝ ተብሎ እንደአዲስ መጠቀሱ አግባብ አይደለም የሚሉ መከራከሪያዎችና የተጠቀሱ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ተጠርጣሪዎችን በእስር ለማቆየት የሚያስችሉ አይደሉም በሚል ተከራክሯል።

በተጨማሪም ጠበቃው ምስክርን በሚመለከት ከሁለት ምስክሮች ውጪ ያሉት ምስክሮች ከዚህ በፊት የተቀበላቸው ናቸው በማለት ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለት ተቃውሟል። በዚህ ጊዜ በጠበቃቸው በተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦች ላይ ፖሊስ መልስ እንዲሰጥ ተደርጓል።

ግብረ አበር ለመያዝ ብሎ የተጠቀሰው አዲስ እና ተጠርጣሪዎች በስር ለማቆየት ታስቦ ነው ተብሎ በጠበቃ የተነሳውን መከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት ከዚህ በፊት የሎጂስቲክ ድጋፍ የሚያደርጉ ግብረአበሮ አሉ በሚል መግለፁን ጠቅሶ መርማሪ ፖሊስ መልስ ሰጥቷል።

ከዚህ በፊት ሲከናወኑ የነበሩ ምርመራዎች በማገዝና በመምራት ሂደት ተሳትፎ የነበራቸው የደ/ብርሃን ፖሊስ አዛዥ በተጠርጣሪዎቹ ግብረአበር የተገደሉ መሆኑን ጠቅሶ ፥ አሰራሩን በመቀየር ምርመራውን መቀጠሉን ገልጿል።

በቀጣይ የተጨማሪ ምስክሮችን ቃል እንደሚቀበል የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ፥ ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ምስክር ሊያስፈራሩና ምርመራ ሊያደናቅፉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ አምስት ተጠርጣሪዎች የልዩ ኃይል አባላት እንዳልነበሩ ገልጾ፥ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ የማሸሽ አቅም እንደሌላቸው በመጥቀስ የዋስት መብታቸው እንዲከበር ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በመዝገቡ የተካተቱ 16ኛ፣ 19ኛ፣ 21ኛ እና 22ኛ ተከሳሾች ቢወጡ ማስረጃ የማሸሽ አቅም አይኖራቸውም የሚል ግምት በመያዝ እያንዳንዳቸው በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዷል።

ቀሪ ማለትም አጠቃላይ 21 የተከሳሾች ግብረአበሮች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ምርመራውን ሲያግዙ ነበሩ የተባሉ የደ/ብርሃን ፖሊስ አዛዥ ላይ ግድያ እንዲፈጸም መደረጉ መገለጹን ተከትሎ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ቢወጡ ምርመራውን ሊደናቀፉ ይችላል የሚል ግምት በመያዝ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን በማለፍ የተጨማሪ የ14 ቀን ምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ተፈቅዷል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።

See also  ማንነታቸው በማይታወቀ ሰዎች ስም ካሳ በሚል መንግስት ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘረፈ

Leave a Reply