Site icon ETHIO12.COM

የ”መልካም ወጣት” አስተማሪው ዮናታን ንብረቶቹ በሃራጅ እንዲሸጡ ማስታወቂያ ወጣባቸው

ራሱን የ” መልካም ወጣት አናጺና ቀራጭ ” በማድረግ ወደ መድረክ የወጣውና ሲጀምር አድናቆት ተችሮት የነበረው አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ በስሙ በተመዘገቡ ንብረቶቹ ላይ የሃራጅ ማስታወቂያ እንደወጣባቸው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጨረታ ገጹ ይፋ አደረገ።

በአገልጋዩ ዮናታን ስም በተመዘገቡ ንብረቶቹ ላይ የሃራጅ ማስታወቂያ ያወጣው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲሆን በምን ያህል የእዳ ክምር መነሻ ንብረቶቹ ሃራጅ እንዲወጣባቸው እንደተደረገ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። በአሰራር እንደሚታወቀው አቶ ዮናታን ከባንኩ የተበደሩትን ገንዘብ በገቡት ውል መሰረት መመለስ ባለመቻላቸው ሳቢያ ሃራጁ ሊወጣ ችሏል። ይህ እስከተጻፈ ድረስ አቶ ዮናታ የሰጡት መግለጫም ሆነ ማስተባበያ ወይም እግድ ስለማቅረባቸው አለተሰማም።

የንብ ባንክ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ባወጣው የሃራጅ ማስታወቂያ፣ በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች በሃራጅ እንደሚሸጡ ማስታወቁን ጋዜጣውን ዋቢ አድርጎ ዜናውን ቀድሞ ያጋራው ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ነው።

አዲስ ዘመን ላይ በተዘርዘረው መሰረት በመልካም ወጣት መምህሩ በዮናታን ስም የተመዘገበ ሃዋሳ ከተማ ላይ የሚገኝ 400ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ያለ ባለ ሶስት ወለል መኖሪያ ቤት በ22 ሚሊዮን ብር የሃራጅ መነሻ የመሸጫ ዋጋ መደብ ወጥቶለት ለተጫራቾች ይፋ ተደርጓል።

በተጨማሪም በዮናታን አክሊሉ አንጄሎ ዜብራ ግሪል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተመዘገበ ሃዋሳ ከተማ ምስራቅ ክፍለ ከተማ የሚገኝ 1ሺህ 271 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ህንጻ በሃራጅ እንዲሸጥ ጫረታ ወጥቶበታል። የሃራጅ መነሻ ዋጋውም ሰላሳ ሚሊዮን ብር ሆኗል።

በሶስተኛ ደረጃ በሃራጅ እንዲሸጥ ጨረታ የወጣበት ደግሞ በዮናታን አክሊሉ አንጄሎ ዜብራ ግሪል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተመዘገበ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኝና ብህጋዊ ካርታና ሰነድ የተመዘገበ 500 ካሬ ሜትር ይዞታ ያለው መኖሪያ ቤትም ይገኝበታል፡፡

ይህን ዜና ተከትሎ በየአቅጣጫው የሚሰሙ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት በእምነት ቤቶችና አገልጋዮች ስም በየባንኩ ያለው ሃብት ከፍተኛ መሆኑ፣ ብዙ ዋጋ የሚያወጣ ቋሚ ንብረት ያከማቹና አለ አግባብ ከህዝብ በማጭበርበር ጭምር እየሰበሰቡ ለመሆናቸው ሰፊ መረጃ ስላለ መንግስት ጥልቅ ምርመራ አድርጎ ህጋዊ መስመር ሊያበጅላቸው እንደሚገባ ነው።

በኦርቶዶክስ ምዕመናን መቆሚያና መሳለሚያ እስኪያጡ ድረስ የደጀ ሰላምን ውበትና ቅድስና በቆሸሸ መልኩ እየተካሄደ ያለው የገበያ ስፍራ ንግድ፣ የመሬት ሽያጭ፣ እንዲሆም ኮንትራት፣ በፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያናት በኩል የሚታየው ራስን የመሾመና ተቧድኖ ” የነበይ” ስራ በመስራት ደሃውን ሳይቀር ኪስ የሚያወሉ አጭበርባሪዎች ላይ መንግስት አቋም ሊይዝ እንደሚገባ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ጉዳይ ነው።

ራሳቸውን ነብይ፣ ሃዋሪያ፣ ፓስተርና ባለ ባት እያደረጉ ያለ አንዳች አፍረት የቪዲዮ ማስታወቂያ በማሰራጨት፣ የጥንቆላ ይዘት ያለው ዝርፊያ በሚያካሂዱ ላይ መንግስትም ሆነ የየአካባቢው አስተዳደር ለምን ዝምታን እንደመረጠ ለበርካቶች ግልጽ አይደለም። እጅግ መንፈሳዊ የሆኑና አገልግሎታቸውን እንደ ቃሉ በስውር ለሚያየው አምላክ በመተው በጎ ስራ የሚሰሩትን በማገዝ፣ ለራሳቸው የቅዱሳንን ስም በመስጠት በየመድረኩ ለማመን የሚከብድ ጥንቆላና መጫበርበር የሚፈጽሙ ዱርዬዎችን መንግስት እንዲያስታግስና የደሃውን ኪስ እንዲጠብቅ አሁንም በርካቶች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

እራፊ ጨርና ዘይት በሚነግዱ፣ በየአደባባዩ በጦር ሳይቀር የሚታጀቡ አገልጋዮችን የሚከተሉ ምዕመኖችም ከዕብደታቸው ሊነቁ እንደሚገባ የሚያሳስቡ፣ ይህ ጉዳይ ውሎ አድሮ የከፋ መዘዝ ሳያመጣ ሊታረ እንደሚገባው የሚያስጠነቅቁ በርካቶች ናቸው።

Exit mobile version