Site icon ETHIO12.COM

ሰላምና የቱሪዝም ፈተና በአማራ ክልል

ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በየጊዜው በተፈጠሩ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ችግሮች ምክንያት የከፋ ጉዳት ከደረሰባቸው የሀገሪቷ የገቢ ምንጮች መካከል ቱሪዝም ቅድሚያውን ይወስዳል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የከፋ ዳፋ ያሳደሩበት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲያንሰራራ ለማድረግ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የጥንት አሻራዎች በተለያዩ ቦታዎች ያሏት ኢትዮጵያ የዓለም ቱሪስትን ቀልብ ከሚስቡ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትኾን አድርጓታል፡፡ ከዓለም የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የቱሪስት ማዕከላት መካከል ስሟ ደጋግሞ የሰፈረው ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ የቱሪዝም ዋና ዋና መዳረሻዎች መካከል በርካቶቹ በአማራ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ከላሊበላ እስከ ስሜን ሰንሰለታማ ተራሮች፣ ከግሸን ደብረ ከርቤ እስከ ጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ ከአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ እስከ ጣና ሐይቅ ገዳማት፣ ከጭስ ዓባይ ፏፏቴ እስከ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ከጎርጎራ እስከ ጉና፣ ከዓባይ ሰከላ እስከ ሰቆጣ ሰሃላ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ መዳረሻዎች አሉት፡፡ በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች እና ከተሞች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የነዋሪዎቻቸው ሕይዎት የተመሰረተው ከቱሪዝም በሚገኝ ገቢ ነበር፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት የሀገሪቱ ብሎም የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቋረጦ ነበር ማለት ይቻላል ያሉን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ አበበ እምቢያለ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፋዊ የጤና ስጋት የኾነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም አቀፉን የቱሪስቶች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ገትቶት ቆይቷል የሚሉት አቶ አበበ አንጻራዊ ክፍተቶች ባሉበት ወቅት ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሌላ መሰናክል ነበር ይላሉ፡፡

የቱሪዝም እንቅስቃሴው መዘጋት በተለይም ሕልውናቸው ሙሉ በሙሉ በቱሪዝም ገቢ ላይ ለተመሰረተ ግለሰቦች እና ከተሞች ከፍተኛ አደጋ ኾኖ ቆይቷል የሚሉት አቶ አበበ ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ባለፈው አንድ ዓመት ትኩረት ሰጥቶ ሠርቷል ብለዋል፡፡ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያነቃቃ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር፣ ሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል በሰቆጣ፣ ላሊበላ እና ራያ ቆቦ፣ እንግጫ ነቀላ በምሥራቅ ጎጃም፣ መስቀል እና ግሸን በግሸን ደብረ ከርቤ፣ ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ጥርን በባሕር ዳር፣ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በአዊ፣ መርቆሪዎስ በደብረ ታቦር እና በመካነ ኢየሱስ፣ የድንቅ ምድር አማራ እና ወይዘሪት ቱሪዝም የቁንጅና ውድድር በጎንደር እና ሌሎች ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት በተለየ ተከብረዋል ብለዋል፡፡ ይህም በተለይም በሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ጉልህ ተፅዕኖዎችን መፍጠር እንደቻለ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው አንስተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት እንዲመለስ የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ ነው ያሉት አቶ አበበ አንጻራዊ የኾኑ መሻሻሎች እንዳሉም አንስተዋል፡፡ ባለፉት 9 ወራት የታቀደውን እና የተጠበቀውን ያክል ባይኾንም ካለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በተሻለ መልኩ የውጭ ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ በመግባት ጎብኝተዋል ነው የተባለው፡፡

የውጭ ጎብኝዎች ለጉብኝት ከመምጣታቸው በፊት ስለሚጎበኙት አካባቢ ወቅታዊ እና አጠቃላይ መረጃ ኖሯቸው ነው የሚመጡት የሚሉት አቶ አበበ ቀልብን የሚስብ መስህብ፣ ትራንስፖርት እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መኖራቸው የጎብኝዎችን መጠን እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በተለይም በውጭ ጎብኝዎች ዘንድ እንደመርህ የሚያዘው “ሰላም ከሌለ ቱሪዝም የለም” የሚለው አቋም ነው ብለዋል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሰላማዊ እልባት ቢያገኝም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም እጦት ምልክቶች የውጭ ጎብኝዎች ወደ ክልሉ እንዳይመጡ ምልክት እየኾነ እንደመጣም ያነሳሉ፡፡

የቱሪዝም እንቅስቃሴው መሻሻል ከገቢ በላይ ለቅርሶች እና ለቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች ዋስትና ነው ተብሏል፡፡ ሕዝቡ ከቱሪዝም እንቅስቃሴው የሚገኘው ገቢ በመቋረጡ በመዳረሻዎች ላይ የሚስተዋሉ ቸልተኝነት እና ጉዳቶች አሳሳቢ እንደኾኑ ተነስቷል፡፡ የክልሉ ዘላቂ ሰላም የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በእጅጉ ይወስናል ያሉት አቶ አበበ የክልሉን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ዘላቂነት ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ እና በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ሁሉ የክልሉን ገጽታ መገንባት እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው አሚኮ

Exit mobile version