Site icon ETHIO12.COM

በድጋሚ “ልቀቁ”፤ በድጋሚ “ሶስት ዓመት ጠብቁ”-አብይ አሕመድ የታላላቅ ፕሮጀቶችን በጀት ምንጭ ይፋ አደረጉ

“ብዙ የምናገረው ነበር” በማለት አመስግነው ንግግራቸውን የቋጩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አጨራረሳቸው መነጋገሪያ ሆኗል። ለወትሮው ይልቅ ሰክነውና መረጃ ላይ አተኩረው መናገር ያለባቸውን ብቻ ተናገረው የተሰናበቱት አብይ አህመድ ከአብን ተወካይ “ልቀቁ” በሚል በወራት ልዩነት በድጋሚ ለተጠየቁት ሶስት ዓመት በትዕግስት መጠበቅ ያስፈለጋል ሲሉ መክረዋል።

ቀደም ባሉት ተመሳሳይ መግለጫዎቻቸው ለሚነሱ ሁሉ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና ለማስረዳት ሲጥሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው ሕዝብ ሊያገኘው በሚገባው መረጃ ላይ ያተኮሩ መስለዋል። ለተቃዋሚዎች መልስ ቢሰጡ ምን ሊሉ እንደሚችሉ፣ ምንም ቢሉ የሚሰሙ ባለመሆናቸው “ይቅር አልናገረውም ” ማለታቸው ጉዳዩ ለገባቸው አድሮ ገሃድ የሚወጣ ብዙ ጉዳይ መኖሩን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል። በተለይም ህዝብ ምሬት ውስጥ እንዲገባ በቅንጅት የሚሰራው የገፊና ጎታች ድራማ መረጃ መንግስት እጅ እንዳለ አመላካች እንደሆነ ነው አስተያየት የተሰጠው።

መንግስት ስራ እንዳይሰራ ዘመቻ እንደሚካሄድ፣ ዘመቻውን ተቋቁሞ ሲሰራ ማጠልሸትና ስንጥቅ ፈልጎ ማጣጣል ሊታረም ያልቻለ ይልቁኑም እየባስበት የሄደ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ መረጃ መስጠት ላይ አተኩረዋል። ለዚህም ይመስላል ቃል ስንጠቃ ላይ የተቸከለው የተቃውሞ ጎራና በመናበብ የሚካሄደው የሚዲያዎችና የማህበራዊ ገጾችን ለሚያስተባበሩ አብይ ብዙም እንዳልተመቹ የተሰማው።

“አልቻላችሁም ልቀቁ፣ እርስዎም ሆኑ ፓርቲዎ አገሪቷ ከገባችበት አረንቋ ማውጣት አትችሉም” ሲሉ ህዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም የአብኑ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ላቀረቡት ጥያቄ ” አስተያየቱ ለፌስቡክ ገበያተኞች ጥሩ ነው፤ ለአገር ግን ምንም አይጠቅምም” ብለው ያለፉት አብይ አሕመድ የተቃዋሚዎች አመለካከት አስፈላጊ እንደሆነ ግን አልሸሸጉም። ይሁን እንጂ ጨለማ ብቻ መሆን እንደሌለበት መረዳት እንደሚገባ የጠያቂውን ስም ሳያነሱ የሚዛናዊነትን አስፈላጊነት አመልክተዋል። አዲስ ህዝባዊ መንግስት ምርጫ አስመልክቶ የምርጫ ምኞት መኖሩን አድንቀው ሶስት ዓመት መጠበቅ ግድ እንደሆነ አስታውቀዋል። ምክር ቤቱም ይህን ጊዜ አውካክቶ ነበር።

በብልጽግና ውስጥ ሌቦችና ህግን የሚያዛንፉ መኖራቸውን ሳያስተባብሉ ተቃዋሚዎችን ” የነበረውን ባህል አበላሽተናል” ሲሉ መክረዋቸዋል። ከአሁን በሁዋላ የሚመጣው መንግስት ቢሮ ሆኖ መስራት እንደማይችል፣ የፕሮጀክት ጥራት ካልጠበቀ ህዝብ ወግድ እንደሚል፣ ጥራትና ታላላቅ ፕሮጀክቶችን የለመደ ህዥብ ስለሆነ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉና እንዲያስቡ አስገንዝበዋል።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ልታፈርሱ ተብሎ ሲጠየቅ ከመለሱት

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ባየበት መድረክ “ውረዱ፣ ልቀቁ” የሚል ጥያቄ የሚያቀርቡት የአብን ወኪሎች ሙሉ በሙሉ የፓርቲውን አቋም ስለማራመዳቸው ጥያቄ ያላቸው አሉ። ብልጽግና በህዝብ እንደተመረጠ አምኖ የተቀበለ ፓርቲ አባላቱ ደጋመው “ስልጣን ስጡኝ” የሚል አሳብ ማራመዳቸው ፓርቲው ውስጡ የተዥጎረጎረና ሊጸዳ እንደሚገባው አመልካች እንደሆነ ጠቋሚ መሆኑ “አፍረናል” ያሉ ገልጸዋል።

ደፍን ዓለም በኢኮኖሚ ችግርና በግሽበት መመታተቱን ጠቅሰው፣ የአለም ባንክንና የአገሪቱን መረጃ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከምስራቅ አፍሪቃ አንደኛ መሆኑንን ማስታወቃቸውን ተከትሎ በእውቀት ስህተት ካለ መንቀፍ ያልቻሉ ” እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” የሚለውን የዲጂታል ወያኔ መንገድ በመከተለ የጠላ ቤት ቅዠት የሚመስል አስተያየት የሰጡ መኖራቸው ታይቷል።

የውልቃይትን ጉዳይ አስመልክተው አጥበቀው በሰላም እንዲያልቅ የመከሩትና ሰፊው የአማራና የትግራይ ህዝብ ረጋ ብሎ እንዲያስብ ያሳሰቡት ዶክተር አብይ፣ በሰላም ችግሩ እንዲፈታ አቅጣጫ መያዙን አመልክተዋል። ግልጽ ባይናገሩትም ከሰላም ውጪ ያለውን መንገድ መንግስት እንደማይፈልገው ምልክት ሰጥተዋል። በህግና በህግ ብቻ ጉዳዩ ምላሽ እንዲያገኝ፣ ሰላም እንዲወርድ ሁሉም አካላት በእኩል ደረጃ ጨዋታውን እንዲጫወቱ አሳስበዋል። መክረዋል። ወልቃይት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አቅጣጫ መቀመጡንም አመልክተዋል። ይህ ስምምነት የጋራ ስምምነት እንደሆነም አስታውቀዋል። የቢቢሲን ሙሉ ሪፖርት ከስር ያንብቡ።

ከዚህ ምስኪን ሕዝብ አንድ ብር አንሰርቅም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

“በተከበረው ምክር ቤት ፊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በኩራት እና በእምነት የምገልጸው፣ ከዚህ ምስኪን ሕዝብ አንድ ብር አንሰርቅም” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሰኔ 29/ 2015 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በእሳቸው አነሳሽነት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ የኦዲት ጥያቄ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 28ኛውን መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት በዛሬው የሰኔ 29/2015 ዓ.ም. የፓርላማ አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከፍተኛ ወጪ እያስገነቧቸው ያሉት የጫካ ፕሮጀክት በመባል የሚታወቀው የተንጣለለ ቤተ መንግሥት፣ የፓርኮች እና ሙዚየሞች፣ እንዲሁም ሌሎች ሰፊ ግንባታዎች ላይ ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉ ፓርኮች እና የጫካ ፕሮጀክት በመባል የሚታወቀው ቤተ መንግሥትን አስመልክቶ ጥያቄ አንስተው ለገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ማክሰኞ ሰኔ 27/ 2015 ዓ.ም. ጥያቄ ተነስቶላቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

አባላቱ መንግሥት ትኩረቱ በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ሳይሆን ቅንጡ በሆኑ ፕሮጀክቶች ናቸው በሚል የወቀሱ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም ኦዲት ለማስደረግ መጠየቅ እንደሚችሉ ተገልጾ ነበር።

በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእሳቸው አነሳሽነት እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ምላሽ ሰጥተዋል።

ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለአገር፣ ገበታ ለትውልድ የገንዘብ ምንጭ እና ለአገሪቱ ያለው ፋይዳ እና ሥራ መጠናቀቁንም ተከትሎ ጥያቄዎች እየጎሉ እና በአሉታዊ መልኩ የሚያዩት እንዲሁም “የሚያማቸው ሰዎች አሉ” ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ጨምሮ በመሥሪያ ቤቶች እና በቢሮ የተጀመረ ሥራ በአገሪቱ የተጀመረው የትራንስፎርሜሽን አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህም መሥሪያ ቤቶች እደሳ መካከል በላቀ ደረጃ ተሰርቷል ብለው የጠቀሱት እና አንድ ዓመት ከስድስት ወራት የፈጀው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሕንጻ ነው።

በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ የፐርፎርማንስ ኦዲት (መጠናቅ እና ጥራትን) አስመልክቶ ከበርካታ የአፍሪካ አገራትም የሚያስደምሙ አስተያየቶችን መስማታቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው ያነሱት ጉዳይ የገንዘቡን ምንጭ (የፋይናንስ ኦዲት) እነዚህ ፕሮጀክቶቻቸው ጥያቄ እንደሚነሱባቸው ገልጸዋል።

እንደ ምሳሌ ከጠቀሱት መካከል የግሪን ሌጋሲ (አረንጓዴ አሻራ) ፕሮጀክታቸውን ነው። አገሪቷ ሃምሳ ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቢያንስ 50 ቢሊዮን ዶላር ሊያስፈልግ ቢችል እንደሆነ ጠቅሰው፣

“ይሄ ፓርላማ ከየት አምጥቶ ነው ለመንግሥት 50 ቢሊዮን ዶላር የሚሰጠን። 50 ቢሊዮን ዶላር ቢያንስ የአገሪቱ ጂዲፒ 1/3ኛው ነው። ሃብቱ የመጣው ከደጋግ ኢትዮጵያውያን ነው። ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን ለማፍሰስ ከወሰኑ ኢትዮጵያውያን ነው።”

አገሪቷ እነዚህ ፕሮጀክቶችን ከመንግሥት በጀት ወይም ከእርዳታ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

አገሪቷ እየሰራቻቸው ያለችው ለምሳሌ 20 ሺህ የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ በአዲስ አበባ፣ በመቶ ሺዎችን ህጻናት እየጠቀመ ያለው የምገባ ፕሮግራም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መዋዕለ ህጻናት፣ ዳቦ ፋብሪካዎች በሕዝብ ንቅናቄ እና በአንዳንድ ባለሃብቶች ድጋፍ እንደሆነም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የመደመር መጽሐፋቸው ሽያጭ ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ውሏል ብለዋል።

“ጅማሮውም ሆነ የገንዘቡ ምንጭ ሰፊ ነው። ከመጽሐፍ ሽያጭ፣ ሃብታም ደጋግ ሰዎችም ሆነ ሌሎች ኢኖቬቲቭ መንገዶችን በመፈለግ የድህነትን መጠን እየቀነስን፣ አገርን እያለበስን ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ዩኒቲ ፓርክ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀው በራሳቸው ተቋራጭ ኩባንያ እንዳሰሩ እና ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳልተቀበሉም ገልጸዋል።

“ገንዘቡን ኦዲት ማድረግ የምትፈልጉ ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድን ጠይቁት” ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

የታችኛው ቤተ መንግሥት እደሳ በፈረንሳይ ፕሬዚዳንት፣ ፍሬንድሺፕ እና ሳይንስ ሙዚየም በቻይና ፕሬዚዳንት እንደተሰራ ጠቅሰው፣ ሁለቱም ሥራዎች መሪዎቹ የራሳቸውን ኩባንያ ቀጥረው እንዳሰሩ እና ገንዘብ እንዳልተቀበሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሌሎች ፕሮጀክቶችም እንዲሁ አገራቱ ተለምነው ሲፈቅዱ ጨረታ ወጥቶ እንደሚሰራ ጠቅሰው መንግሥታቸው የክትትል ሥራ ብቻ እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

በአገር ውስጥ ገንዘብ በማዋጣት የተሰሩ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ ሐላላ ፕሮጀክቶችም ባለቤትነታቸው ለክልሎች እንደሆንም ጠቅሰው፣ “ዐይን የመግለጥ ሥራ እየሰራን ነው” ብለዋል።

“በተከበረው ምክር ቤት ፊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በኩራት እና በእምነት የምገልጸው፣ ከዚህ ምስኪን ሕዝብ አንድ ብር አንሰርቅም” ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም እነዚህን ፕሮጀክቶች እያደነቀ እና እየመሰከረ ቢሆንም “ይህንን ስኬት እናጠልሽ ብለው የተነሱ ምስኪን ፖለቲከኞች አሉ” ሲሉም ወቅሰዋል።

በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ የምክር ቤት አባሉ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አነሳሽነት እየተገነቡ ያሉ እነዚህን ፕሮጀክቶችን ደግፈው አስተያየት ሰጥተዋል።

“ሥልጣን ያስረክቡ”

ከዚህ ቀደም እንደተጠየቀው በዛሬው የፓርላማ ውሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣናቸውን ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ ተጠይቀዋል።

ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ሲሆኑ፣ ሥልጣንን ከማስረከብ በተጨማሪ ፓርላማውን እንዲበትኑ እና ለአዲስ ምርጫ ዝግጁ ለማድረግ መንገዱን እንዲጠርጉ ጠይቀዋቸዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ “ብልጽግና ፓርቲ መራሹ መንግሥትም ሆነ ፓርላማው ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር ማውጣት ስለማይችሉ” ጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር ሥልጣን ይረከብ ሲሉም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጽግናን ወይም መንግሥታቸውን በሚመለከት የቀረቡ ክሶች አሉ ያሉ ሲሆን፣ እነዚህን ክሶች ሙሉ በሙሉ መጣል ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ሁሉንም ጨለማ ነው ብሎ በጥቅሉ መናገር ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።

“ሁሉ ነገር ጨለማ ከሆነብን ጨለማ ውሰጥ ያለነው እኛ አይደለንም። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ጨለማ ናት የሚለው አያስኬድም። ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብት በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ሦስተኛ ናት እንዲሁም፣ ታላላቅ ተቋማትን እየገነባች ያለች አገር ናት” ብለዋል።

ገዢው ፓርቲ ብልጽግና በከፍተኛ ድምጽ ብልጫ የተመረጠ መሆኑንም አስታውሰው፣ ሁሉንም ሥራዎች መንግሥት በራሱ መጨረስ ቢገባውም የተቃዋሚዎች አሳታፊነትን እንደሚረዱ ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠየቀው ጥያቄ ለማኅበራዊ ሚዲያ ፍጆታ እንደሆነ ሸንቆጥ አድርገው “ለዛሬ ዩቲዪብ እንዲህ ነው መባሉ ጥሩ ነው። ለአገሪቱ ግን ጥቅም አያስገኝም” ሲሉም ተሰምተዋል።

ምርጫን በተመለከተ የተነሳው ጥሩ ሃሳብ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ሦስት ዓመት ተቃዋሚዎች እንዲታገሱ ጠይቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅሙን ያውቃል ብለዋል።

“በከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ዕድሎች ብናይ ጥሩ ነው” ሲሉም ሃሳባችውን አስቀምጠዋል።

“የአመራሮች እና የዜጎች ግድያ እና እገታ”

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ የፀጥታ ችግሮችን በተመለከተ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፣ በተለይም እየተበራከተ የመጣው የአመራሮች እና የዜጎች ግድያ እና እገታ፣ የፀጥታ ኃይሎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ጉዳይ ተነስቷል።

ጥቃቶቹም በተቀናጀ መንገድ እየተፈጸሙ እንደሆነ እና ከሰላም መደፍረሱ ጋር ተያይዞ ዜጎች እንደሚፈናቀሉ፣ እንደሚገደሉ እንዲሁም ንብረት እንደሚወድም ተገልጿል።

ዋና ዋና የአገሪቱ መንገዶች የስጋት ቀጠና እንደሆኑም ተነስቶ በአማራ ክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት ከተከናወነው ተግባር ጋር በተያያዘ የተነሳው አመጽ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ሸኔ) ጋር በተያያዘ ችግሩ መቀጠሉንም አንድ የፓርላማ አባል አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ “ሕዝብን እያፈኑ እና እየገደሉ ሕዝብን ነጻ ማውጣት አይቻልም። ሕዝብን እያፈኑ እና እየገደሉ ያሉ ሽፍቶች የሕዝብ ነጻ አውጪ መሆ አይችሉም” ብለዋል።

ለችግሩ እልባት ለማግኘት መንግሥት በሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚያስቀጥል እና በድርድር የሚፈታ ጉዳይ ካለም መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

“ለጦርነት በሙሉ ልብ እንደሰራነው ለሰላምም በሙሉ ልብ እንሰራለን”

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ተከትሎ በህወሓት እና በመንግሥታቸው መካከከል የተደረገውን ግጭት የማቆም ዘላቂ ስምምነትን በተመለከተ የሰላም አስፈላጊነትን አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የጦርነት ሃሳብ የሚጎስሙ ሰዎች ሄደው የሚዋጉ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ያለበት ጦርነት ብሎ የሚናገር ሰው ካለ ግንባር አካባቢ አታዩትም የድሃ ልጅ የሚያስጨርስ ነው እንጂ” ሲሉ አሳስበዋል።

ከግጭት ይልቅ እርቅን የሚፈልግ ቡድን፣ መንግሥት፣ አገር ካለ የስኬት መንገድ ይጀመራል ሲሉም አክለዋል።

“የመተማመን፥ የመከባበር ዘርን ያልዘራ የሰላም አዝመራ ማጨድ አይቻልም። ጦርነት ብዙ ቁስል አለው፣ ብዙ ጥፋት አለው፤ ባለፉት መቶ ዓመታት እንዲሁም ከለውጡ በኋላ በቂ ጦርነት አድርገዋል” ሲሉም ተደምጠዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ መደረግ ያለበት የትርክት ለውጥ እንደሆነ ጠቅሰው “ወያኔ፣ ብልጽግና የሚለው መቅረት አለበት” ሲሉም ተናግረዋል።

“በአንድ በኩል የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል ነው። መገንጠል የለበትም ካልን ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ መኖር አይችልም። አንድነትን የሚሹ የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው ዜጋ የመኖር መብት እንዳለው መረዳት አለብን። በአንድ በኩል እየገፉ ሌላ በኩል አንድነት ማለት አይቻለም አያስፈልግም” ብለዋል።

መንግሥታቸው ለጦርነት ሆ ብሎ እንደተነሳው ለሰላሙም በሙሉ ልብ እየሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው ባለፉት ስድስት ወራትም የተከናወኑ ተግባራትንም ጠቀሰዋል።

የተቋረጡ መሠረተ ልማቶች ግንባታ፣ የአስረኞች መለቀቅ፣ የህወሓት ከአሸባሪነት መሳትን ጠቅሰው ለሰላሙ የሄዱት ርቀት ብዙ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነ እና ገና በርካታ ሥራዎች መሰራት አለባቸው ብለዋል።

ከነዚህም ውስጥ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው መመለስ አትኩሮት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

“ኢትዮጵያውያንን የማይሸከም መሬት ሊኖር አይገባም፤ ከበቂ በላይ ለኢትዮጵያውያን በቂ መሬት አለን። የተፈናቀሉ ዜጎችን መመለስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የቤት ሥራ መሆን አለበት። የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በሰከነ መንገድ ሰው ሳይሞት ሊፈቱት ይገባል” ብለዋል።

“አፈናቅሎ ማስፋት አይቻልም” ሲሉም በኦሮሞ እና በአማራ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችም ሊመለሱ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት፣ የሽግግር ፍትሕ እና ተጠያቂነት ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችልም ጠቅሰዋል።

ሌሎች ሰሞነኛ ጉዳዮችን በተመለከተ

በተጨማሪም ልዩ ኃይልን መልሶ በማደራጀት መልኩ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ፣ ከአድማ በታኝ፣ ከህግ ውጭ ያለ ታጣቂ ኃይል ህጋዊ በሆነ መልኩ ሊኖር እንደማይችልም ተናግረዋል።

“የታጠቀ ልዩ ኃይል የአገር አንድነት ኃይል ችግር ይጋርጣል ብለዋል። ልዩ ኃይሉ በርካታ አስተዋጽኦዎችና ድጋፎችን ቢያደርግም የተለያዩ የመንግሥት አካላት ተስማምተው፣ ምጣኔ ኃብት አደራጅተው ልዩ ኃይሉን የማዋቀር አስፈላጊትን መታመኑም ጠቅሰዋል።

ከሰሞኑ አነጋጋሪ የሆነው የቤቶችን ግብር በተመለከተ ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ አዲስ አበባ ‘የፕሮፐርቲ ታክስ’ን በተመለከተ ተግባራዊ አልሆነም ብለዋል። በአዲስ አበባ ከሰሞኑ ተግባራዊ የሆነው ከዓመታት በፊት የነበረው የጣሪያና ግድግዳ ክፍያ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸው የአዲስ አበባ ነዋሪ ቅሬታ ካለው ቅሬታውን እንዲያቀርብ ተናግረዋል።

ሌላኛው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማና በአዲስ አበባ እየተደረገ ያለውን ፈረሳ በተመለከተ ነው።

ህገወጥ ቤቶችን መፍረስ በተመለከተ የሸገር ከተማ፣ ከዚያም ካለፈ የኦሮሚያ ክልል መሆን እንዳለበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ስራውን በተመለከተ በአገር ደረጃ ህገወጥ ቤቶች መፍረስ እንዳለባቸው አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

“ከተሜነት ማለት የተጠጋጋ ቤት መስራት አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን በዚህ ሂደት ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ህጋዊ በሆነ መልኩ ሰርተው የተጎዱ ካሉ መካስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ካሉ አገራት በምጣኔ ኃብት ዕድገት በቀዳሚ ስፍራ ተቀምጣለች”

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ፈጣን ላይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት በቀዳሚ ስፍራ እንደተቀመጠች በዛሬው በፓርላማ ውሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የኢትዮጵያን ያህል እድገት ያስመዘገበ እንደሌለ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራትም ከናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ተከትላ ሶስተኛነት ስፍራ ላይ መቀመጧም ተገልጿል።

እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት (ከለውጡ በፊት ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠሩት ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ኬንያ አንደኛ እንደነበረችና ኢትዮጵያም በምጣኔ ኃብቷ የነበራት ስፍራ አምስተኛ ላይ እንደነበር አውስተዋል።

ለዚህም እንደ ማጣቀሻ ያነሱት የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሰጡትን ትንበያ ነው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓለማችን የምታስመዘግበው እድገት 2.8 እንዲሁም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት 4̀.2 እንደሆነ አስቀምጠዋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብትን በተመለከተ በዘንድሮው 6.1 መመዝገብ መቻሉን የዓይኤምፍን መረጃ ዋቢ ያደረጉ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 6.4 የምጣኔ ኃብት ዕድገት ሊኖር እንደሚችል ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መተንበዩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ እንደሆነ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብትን በተመለከተ አገሪቷ 7.5 ዕድገት እንደሚኖር እንደሚጠብቁም ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።

2ኛው የሃገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር እየተተገበረ እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ማሻሻያ ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማስቀጠልን፤ እንዲሁም የዕዳ ጫናን ማቃለልን ታሳቢ በማድረግ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

“በበጀት ዓመቱ በርካታ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም፤ ሀገር በቀል ኢኮኖሚውን በማጠናከር ችግሮቹን መሻገር ተችሏል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ወይም ጂዲፒ ውስጥ የዕዳ መጠን 59 በመቶ እንደነበር ገልጸው በዓመታት ውስጥ የእዳ መጠኑን ወደ 38 በመቶ በማድረስ ስኬት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል እንደ ስኬት የጠቀሱት የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነው።

የዋጋ ግሽበቱ 37 በመቶ ደርሶ የነበረ ሲሆን፤ በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው ምክንያት ቁጥሩን ወደ 30 በመቶ መቀነስ መቻሉን እና እንደ ሀገር ያጋጠመውን የኑሮ ውድነት ለመግታት ወደ ገበያ የተረጨውን ገንዘብ ለመቆጣጠር መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ጠቅላይረ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

“አንዱ መከራችን የዋጋ ንረት ነው … አሁን የዋጋ ንረት እንደ ኮሮና ወረርሽኝ ነው፤ አሜሪካን ያሰቃያል፣ ቻይናን ያሰቃያል፣ አውሮፓን ያሰቃያል፣ አፍሪካን ያሰቃያል፣ በኢንፍሌሽን የማይሰቃይ እና ቀዳሚ አጀንዳው ያላደረገው በዓለም ላይ አንድም ሀገር የለም።”

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የ2016 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት በጀት 801 ቢሊዮን አድርጎ አጽድቋል።

በጀቱ ከአምናው በጀት ጋር ሲነጻጸር የ15 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ገልጸዋል።

በጀቱ ማህበራዊ ዕድገትን ለማፋጠን፣ ድህነት ተኮር ለሆኑ ተግባራት ትኩረት የሰጠ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ፣ ለዕዳ ክፍያ እና በመልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በጀቱን በጥንቃቄ ለመጠቀም ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓቱን ተከትሎ በማይሰሩ መስሪያ ቤቶች ላይ በየደረጃው ያለው አካል ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ አቶ ደሳለኝ አሳስበዋል።

Exit mobile version