Site icon ETHIO12.COM

“የመከላከያ ሠራዊት ከክልላችን ይዉጣ” የማንን ፍላጎት ለማሳካት?

Ethiopian defense force

የኢትዮጵያ ልብ ሠራዊታችን ነው !! ሠራዊቱ ከክልላችን ይዉጣ እያሉ የሚቀሰቅሱ ጽንፈኛ የደም ነጋዴዎች የማንን ፍላጎት እያሟሉ እንደሆነ ሕዝቡስ ምን ያህል ተረድቷል?

ለገሰ ቱሉ – የመንግስት ኮሙኒከሽን ሚኒስትር

መከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያ ጋሻና መከታ፣ ኩራትና ዋስትና ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ በሙሉ ክብር፣ ፍቅር እና አንድነት በእያንዳንዱ የመከላከያ ሠራዊታችን አመራር እና አባል ልብ ውስጥ እንዳለች ከተግባርም ከታሪክም አይተናል። ኢትዮጵያ በሠራዊታችን ልብ ውስጥ ያለችው በፍጹም የሀገር ፍቅር መስዋዕትነት ነው። በህይወት በሚከፈል እውነተኛ የሀገር ፍቅር ዋጋ ለዚህ ነው መከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያ ልብ ነው የምንለው።

ሠራዊታችን ከሕዝባዊ ባህሪው በመነጨ ስሜት በደስታዉም ሆነ በሃዘኑ ከምልዓተ ሕዝቡ ጎን የሚቆም፣ አብሮ የሚያለማ፣ ተፈጥሯዊና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጥኖ ደራሽ፣ በኅብረ ብሔራዊነትና ወንድማማችነት ማዕቀፍ ሁሉን አካታች ለሆነች ኢትዮጵያ ህልዉና ከማንም ቀድሞ ህይወቱን የሚገብር የሕገ መንግሥታዊ ስርዓታችንና አንድነታችን ጠበቂ ነዉ፡፡

በቅርቡ እንኳን በሰሜኑ ሀገራችን በተከሰተው ግጭት የተቃጣበትን ጥቃት በጀግንነት ከመከተ በኋላ የአማራን ሕዝብ ሁለንተናዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ህይወት እየከፈለ የሕዝቡን መብት ያስከበረው የምንመካበት ጀግናዉ የመከለካያ ሠራዊታችን ነዉ፡፡

ይህንን እዉነታ ወደ ጎን በመተዉ የመከላከያ ሠራዊቱን ጀግና አመራሮች እና የሠራዊቱን ስም የሚያጎድፉ፣ ሠራዊቱ አኩሪና መስዋዕትነት የከፈለባቸዉን ታሪካዊ ስራዎቹንና እሴቶቹን ጥላሼት እየቀቡ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ጥርጠሬ እንዲፈጠር የሚያደርጉ የፖለቲካ ነጋዴዎች ተፈጥረዋል። ነጋዴዎቹ ከማሕበራዊ ሚዲያ የፖለቲካ ንግድ አንስቶ ያተርፋል ያሉትን ሁሉንም ስም ማጥፋት እያካሄዱ ይገኛሉ።

ሠራዊቱ በክልሉ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸዉን እንቅስቃሴዎች ለማደናቀፍ የሚጥሩት እነዚህ ኃይሎች የሚያስጠብቁት ጥቅም የግል ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ሲሆን አንዳንዶቹም የዘመናት የሥልጣን ቅዠታቸውን ለማሳካት መሆኑን በግልጽ እና በይፋ ማሳየት ጀምረዋል። እነዚሁ ሠራዊቱ ከክልላችን ይዉጣ እያሉ የሚቀሰቅሱ ጽንፈኛ የደም ነጋዴዎች የማንን ፍላጎት እያሟሉ እንደሆነ ሕዝቡስ ምን ያህል ተረድቷል? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።

ሕዝቡ ዘላቂ ሰላሙን እና የኖረ እሴቱን ግምት ውስጥ አስገብቶ የደም ነጋዴዎችን ያሰቡትን እኩይ የጥፋት ትርፍ ሊያመክን ይገባል።

የመከላከያ ሠራዊታችን የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለመረጋገጥ ከየትኛዉም አካባቢ በላይ መስዋዕትነት መክፈሉና ዛሬም ጭምር እየተዋደቀ መሆንኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የትኛዉንም አይነት ጥያቄና ፍላጎት ያለዉ ሃይል በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብ እና ለመፍትሄ መወያየት እንዲችል ትክክለኛ አማራጭ መንገድ ዘርግቶ እያለ የግል ፍላጎትና ጥቅም በሃይል ለማሳካት የሚደረግ የትኛዉም አይነት ድርጊትና እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለዉም፡፡

ከሰላማዊ አማራጭ ዉጭ የትኛዉንም አይነት ፖለቲካዊ ፍላጎትና ዓላማ ማሰካት እንደማይቻል በቅርቡ ከተከሰቱ ድርጊቶች መማሩ ጠቃሚ ነዉ፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ጥያቄዎችና ፍላጎቶችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል መሰረት መጣሉና ለአንዱ ተመልሶ ለሌላኛዉ የተከለከለ ጉዳይ እንደሌላ መታወቅ አለበት፡፡ በስክነትና የወል እዉነቶች ላይ በመቆም ብቻ የተናጠል ጉዳዮች መፍትሄ እንደሚያገኙ መረደት ይገባል፡፡ በደቦ፣ በግርግርና በማህበራዊ ሚዲያ ጋጋታ የትኛዉንም አይነት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም፡፡

በመሆኑም ሠራዊታችን የአማራ ሕዝብ ጠለትና ጥቅሙን የማያስከብር አድርገዉ የሚቀሰቅሱ ጽንፈኞችና በሰዉ ህይወት በመነገድ ኪሳቸዉን የሚያደልቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ቁማርተኞች ከድርጊታቸዉ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ መላዉ የክልሉ ሕዝብም ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ከዘራፊዎችና ሽፍቶች መጠበቅ አለበት፡፡ በተሳሳተ መንገድ ተነሳስተዉ የሠራዊቱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማስተጓጓል የሚጥሩ ሃይሎችም ቆም ብለዉ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡

አሉባልታና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመርጫት እንዲሁም የሠራዊቱን እንቅስቃሴ በማደናቀፍ በክልሉ ዉስጥ ለሚፈጠረዉ ቀዉስ እነዚህ ሃይሎችና እነሱ ያሰማሯቸዉ ቡድኖች መሆናቸዉን ከወዲሁ መገንዘብ ይገባል፡፡

Exit mobile version