ETHIO12.COM

ከአማራ ክልል አሳዛኝ ዜናዎች እየወጡ ነው፤ በአገው አዊ ዞን የጅምላ ጉዳት ተከትሎ የብሄር ይዘት ያለው ግጭት ተጀምሯል

“በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በአማራ ክልል ለደረሰው ዕልቂት እጃቸውን ያስገቡ በህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ ነው”

በአማራ ክልል ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲሰሙ የነበሩ “የአሸነፍን” ዜናዎችና ፉከራዎች ዛሬ በሃዘን ዜና ተለውጠዋል። በትግራይ ጦርነት ወጣቱን በአጉል ፕሮፓጋንዳ ያስጨረሱት እንዳደረጉት አሁን ላይ ዜናው ሁሉ መርዶ ሆኗል። ጣት መቀሳሰርም ተጀምሯል። አንዱ ሌላውን ” ባንዳ” እያለ አማራ ለአማራ ስም እየሰጠ ነው። ” አሳደህ በለው” ሲሉ የነበሩ የሚዲያ ባለቤቶች ” የጥይት የቀለብ መግዣ እያላችሁ አትደውሉ” በሚል “ከጉሮ ወሸባዬ” ዜናቸው ወደ ” ሰለቸኝ” ተለውጠዋል።

ሲጀመር ገና በጥሬው “ይህ መንገድ አያዋጣም” ያሉ ተወግዘው፣ ተፈርጀው ከየአቅጣጫው አዛዥና ናዛዡ በዝቶ ወደ ከተማ የመጣው ታጣቂ ህዝብ መሃል መግባቱን ተከትሎ በተደረገ ጦርነት የተፈራው ደርሷል።

ከውጭና ከአገር ውስጥ በመንግስት መዋቅር የተሰገሰጉትን ጨምሮ በተሳተፉበት የገሃድና የውስጥ ለውስጥ ቅሰቀሳ የተጀመረው ከተማዎችን የመቆጣጠር ጦርነት ውጤቱ ሃዘን ብቻ እንደሆነ የድል ዜናውን ሲያውጁ የነበሩት ናቸው እየገለጹ ያሉት። የጀርመን ድምጽ ” ባህር ዳር ሟቾቿን ስትቀብር ዋለች” በሚል ለመስማት የሚከብድ መሪ ቃል መርጦ ያቀረበው ዘገባ ገና ግርድፍ ቢሆንም ደረት የሚያስደቃ ሆኗል። አሁን ከየአቅጣጫው የሚሰማው የሃዘን ዜና አማራ ክልል አመት ሳይሞላው ዳግም በሃዘን እንዲመታ፣ እንዲጎሳቆል፣ እንዲሰደድና ወደ ባሰ ደም መፋሰሰ ማምራቱን የሚያሳይ ነው።

የአገር መከላከያን በወራሪነት ፈርጆ የተጀመረው ጦርነት መነሻውን ከተማ ውስጥ በማድረጉ ለበርካታ ንጹሃን ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ” እገሌ ነው ጥፋተኛ” ሳይሉ በርካቶች ተቃውመዋል። ያለ በቂ ድርጅትና አቅም ከተማ ውስጥ መሽጎ ጦርነት መግጠም ዓላማውና ውጤቱ ግራ የሚያጋባ ስልት እንደሆነ የሚናገሩ ” ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተባባሪ የሆኑ በአገርና ዓለም ዓቀፍ ህጎች ወደ ለህግ እንዲቀርቡ እየተሰራ ነው። ፍትህ ወዳዶች እገሌ ከገሌ ሳይሉ ድጋፍ ሊሰጡ ይገባል” ብለዋል። መከላከያ ድርጊቱን እንዳይቃወም፣ መንግስት ሲገለበጥ ዝም ብሎ እንዲያይ ” አትተኩሱ ነገሬያለሁ” ሲል ለራሱ በሰጠው ማዕረግ መመሪያ ያወረደው ታማኝን ጨምሮ ዛሬ ላይ ምን ምላሽ እንደሚኖራቸው ለመገመት አስቸጋሪ ነው። ይህ ጫፍ ጫፉ እየተሰማ ያለ የሃዘን ወሬ ውሎ አድሮ ገሃድ ሲሆን የጉዳቱ መጠን የነካቸው የሚሉት እንደሚኖራቸው ይታመናል። ከተሞች ነሳ ሲወጡ ሸሽቶ የወጣው ሃይል ምን አደረገ የሚለው ገና በገለልተኞች የሚጣራ ቢሆንም ከባድ ወነጀል መፈጸሙ ተሰምቷል።

ለዝግጅት ክፍላችን በደረሰን መረጃ መሰረት ዝርዝር ውስጥ ባይገባም በአገው አዊ ብሄርሰብ አስተዳድርና አካባባቢው ከከተሞች ተሸንፎ የወጣው ሃይል ጉዳት አድርሷል። ያነጋገርናቸው እንዳሉት ሰዎች ተገድለዋል። ከተማ ጠፍቷል። ንብረት ተዘርፏል። ለጊዜው ለመጻፍ የማይመች ማንነትና የዘር ስርን የሚነካ መፈክር በማሰማት ነበር ታጣቂዎቹ ጉዳቱን ያደረሱት። የመከላከያ ሃይል ባስቸኳይ እንዲደርስላቸው በሚችሉት ሁሉ ጥሪ አድርገው እንደነበረም እነዚሁ ክፍሎች አስታውቀዋል።

ይህንኑ ጥቃት ተከትሎ ችግሩ ወደ ብሄር ግጭት የተሸጋገረበትና አንዱ አጥቂ ሌላው ተከላካይ ሆነው ችግሩ ወደ ዚገምና አየሁ ወረዳ መስፋቱን ያመለከቱት ክፍሎች የጸጥታ ሃይሎች ባስቸኳይ ደርሰው እርምጃ ሊወስዱና ግጭቱን ሊያስቆሙት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ካነጋገርናቸው መካከል አንዱ ” የአገው ህዝብ እንደ ህዝብ ተጠቅቷል። ይህን ህዝብ ይወቀው። ምን አጠፋን?” ብለዋል። ቁጥራቸው በርካታ ሰዎች እንደተገደሉ ገልጸዋል።

“ከተሞችን አውቄ ነው የለቀኩት፤ ባሻኝ ጊዜ ዳግም መያዝ እችላለሁ” በሚል ወደ ተመረጡ አካባቢዎች ማፈግፈጉን ያመለከተው የአማራ ህዝብ ንቅናቄ ወይም የፋኖዎች ህብረት የሚባለው ታጣቂ ሃይል፣ ውሳኔው የስልት እንደሆነ አመልክቷል። በሌላ በኩል ትጥቁን እንዲፈታ ተለምኖ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ተድምስሶ የተረፈው እንደሸሸና በመታደን ላይ እንዳለ፣ ህዝብም ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ የኮማንድ ፖስቱ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ጦርነት የነበረባቸው የአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆናቸውን ተከትሎ ይፋዊ መረጃ ባይሰጥም አሁን ላይ እየወጡ ያሉት መረጃዎች አስደንጋጭ እየሆኑ ነው። በርካታ ንጹሃን በተባራሪ ጥይት እንደሞቱ፣ በያዙት አቋምና የክልሉ መንግስት መዋቅር ውስጥ አላችሁ በሚል የተረሸኑ፣ እስር ቤት ተሰብሮ የወጡ ፍርደኞች ከሳሾቻቸው ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዳቸው፤ መከላከያ እርምጃ ሲወስድ የተገደሉ በጥቅሉ አማራ ክልል ሃዘን ተቀምጧል።

አገልግሎቶች በሙሉ በመቋረጣቸው ማህበራዊ ቀውሱ ያስከተለው ጉዳይ በዳታና በመረጃ ባይዘገብም፣ ያደረሰው ጉዳት ትልቅ ነው። ተከታታይ ህክምና የሚያስፈልጋቸው፣ ምጥ የያዛቸው እናቶች፣ እለታዊ መድሃኒት የሚያሻቸው ወገኖች፣ የሚበላ ያጡ ሸቃዮችና ምስኪኖች … ምን ያህ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲታሰብ አማራ ክልል ውስጥ የሆነው ሁሉ አድሮ ሲሰማ ህመሙ የሚያስፈራ ሆኗል።

አሁን ላይ የመድሃኒት ችግር፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የማህበራዊ አገልግሎት መስተጓጎል፣ የዕለት ፍጆታ ችግር፣ የስዱዳን ስደተኞች ጣጣ፣ የተረጂዎች እርዳታ አለማግኘት ያሳደረው ተጸእኖ አንድ ላይ ተዳምሮ ውጤቱ አስከፊ ሪፖርቶች ይገለሳል ተብሎ ይጠበቃል። የሚያሳዝነው “ግፋ በለው” ሲሉ የነበሩ ሃይሎች አሁን ደግሞ ሃዘኑንን ሌላ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ላይክና ሰብስክራይብ እየወተወቱበት ነው። “አማራ ክልል የተሰሙ የድል ዜናዎች” ብለው ሲሰበስቡና ሲነገዱ የነበሩ፣ አሁን ደግሞ ” ከአማራ ክልል የተሰሙ አስደንጋጭ ዜናዎች” በሚል አዲስ ንግድ ከፍተዋል። በትግራይ ጦርነት የከበሩ መጨረሻ ላይ ጎራ ለይተው እንደተቧቀሱ የሚታወስ ነው።

ጦርነቱን ሲቆሰቁሱ የነበሩና ጦርንርቱን ሲመሩ የነበሩ በውል ሳያጤኑ በግፋ በለው እንደገቡበት የሚነገርለት የአማራ ንቅናቄ በአንድም የአገሪቱ ክልል ተቀባይነት አላገኘም። ለዚህ ይመስላል አመጹ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ቁመናና ስሪት ያላገናዘበ እንደሆነ ተደርጎ የሚተቸው። ይህን “በደመነፍስ የተመራ ነው” የሚባለውን ግጭት ከውጭም ሆነ አገር ውስጥ ሆነው ያስተባበሩ፣ የመሩ፣ የረዱና የተሳተፉ በህግ መጠየቅ እንደሚገባቸው እየተነገረ ያለው። እንደሚባለው ጉዳዩ ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረ የሽብር ወነጀል ክስ እንዲፋጠን ስራ ተጀምሯል።

አሁን ላይ እንደሚሰማው መንግስት ከአውሮፓ አገራትና አሜሪካ ጋር በዚህ ጉዳይ ቀደም ሲል የጀመረውን ንግግር ገፍቶበታል። አንድ የአውሮፓ አገር ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠትና ጦርነቱን ሲገፉ የነበሩ አካሎችን አሳልፋ ለመስጠት መስማማቷ ተመልክቷል።

ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ ውጭ ያሉትን ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ሆነው ችግር በመፍጠር፣ በመናበብ ሆን ብለው ህዝብ እንዲጎዳ በማድረግና ይህንኑ ጉዳት በሚዲያ በማሰራጨት ህዝቡን ቁጣ ውስጥ በመክተት ያስተባበሩ ለህግ እንዲቀርቡ ግፊት አለ።

በሌላ በኩል ግን የተለያዩ ታዛቢዎችና እርጋታን የመረጡ ወገኖች እንደሚሉት፣ የአገሪቱ ዜጎችም እንደሚያውቁት የአማራ ህዝብ ክፉኛ በደል ስለደረሰበት፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የዋስትና ጥያቄው እንዴት እንደሚመለስለት ስልት ዘርግቶ መነጋገር ግድ እንደሆነ በብዛት አስተያየት ይሰጣሉ።

በደመነፍስ ሌላ ዓላማ ተሸክሞ የአማራን ሕዝብ ለኬሎች ወንድሞቹ ጋር የሚያናክስ፣ ይበልጥ መህበራዊ እረፍት የሚያሳጣው መግለጫና ፉከራ ቆሞ በትክክል በበደሉ ዙሪያ መፍትሄ እንዲያገኝ ህዝባዊ ትግል ሊደረግ እንደሚገባ፣ ይህ ሲሆን ሌሎችም “የአማራ ችግር የኔም ችግር ነው” ብለው ትግሉን ለማገዝ ዕድል እንደሚሰጥ እነዚሁ ክፍሎች ይመክራሉ።

ከሻለቃ ዳዊትና ዕስክንድር ነጋ ውጪ ፊትለፊት በመሪነት ወጥቶ ትግሉን የሚመራ ሃይል ይፋ ያልሆነበት የአማራ ትግል በፋኖ አደረጃጀት በዛሬዋ ኢትዮጵያ መልስ እንደማይገኝለት እነዚሁ ክፍሎች ያስታውቃሉ። በራሱ በፋኖ ውስጥም ሙሉ ስምምነት እንደሌለ በማንሳት የአማራን ህዝብ አላስፈላጊ መከራ ውስጥ ከመክተት ሰላማዊ ትግል ላይ ቢሰራ እንደሚሻል ይጠቁማሉ። ትግሉንም አጭር ያደርገዋል። ሌሎችንም ስጋት ውስጥ አይጥልም። ኢትዮጵያን ለማጥቃት ለሚነሱ የሩቅና የቅርብ ጠላቶች አመቺ ሁኔታ አይፈጥርም።


Exit mobile version