Site icon ETHIO12.COM

የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን መግደላቸውን ሪፖርት ጠቆመ

በጦርነት እየታመሰች ካለችው የመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንን የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች መግደላቸውን የሂማን ራይትስ ዋች ሪፖርት አመለከተ።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ድረስ ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ የድንበር ጠባቂዎች ተገድለዋል ብሏል በሪፖርቱ።

የመብት ተሟጋች ቡድኑ የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች ስልታዊ በሆነ መልኩ ስደተኞችን ለመግደል ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ከመጠቀማቸው በተጨማሪ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ስደተኞችን በቅርብ ርቀት በጥይት ገድለዋል ብሏል።

ስደተኞችን መግደል የሳዑዲ መንግሥት ፖሊስ አካል ከሆነ ግድያዎቹ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዋች።

በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች ስደተኞችን የትኛውን የሰውነት ክፍላችሁን እንምታ ብለው ጠይቀው ነው በጥይት ይመቷቸዋል ይላል ሪፖርቱ።

የድንበር ጠባቂዎቹን ጥቃት በመሸሽ ወደ የመን ድንበር በሚሸሹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይም ተቀጣጣይ ነገር እንደሚተኩሱባቸው የመብት ድርጅቱ አመልክቷል።

ቢቢሲ አማርኛ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ እና ስቃይ ዝርዝር ዘገባ ሠርቶ የነበረ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ የሳዑዲ መንግሥት አስተያየትን ለመጠየቅ ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢሜይል መልዕክ ቢልክም ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ከመጋቢ 2014 እስከ ሐምሌ 2015 ድረስ ከየመን ወደ ሳዑዲ ለመሻገር የሞከሩ 38 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ካነጋገረ እና ከ350 ያላነሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዲሁም ፎቶግራፎችን በተጨማሪም የሳተላይት ምስሎችን ከተመለከተ በኋላ ነው ይህን ሪፖርት ያወጣው።

በአሁኑ ወቅት ድህነት እና ግጭትን በመሸሽ ከ750ሺህ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ እንደሚኖሩ የሂዩማን ራይትስ ዋች አሃዝ ያሳያል።

የመብት ተሟጋች ቡድኑ ከእአአ 2014 ጀምሮ ድንበር ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን የመረመረ ሲሆን፣ ግድያዎች የጨመሩበት ሁኔታ ግድያዎቹ ሆነ ተብለው እንደሚፈጸሙ ያሳያል ብሏል።

ስደተኞች እንደሚሉት የኤደን ባሕረ ሰላጤን በመናኛ ጀልባዎች ከተሻገሩ በኋላ የየመን ሰው አዘዋዋሪዎች በሁቲ አማጺያን ቁጥጥር ሥር ወደምትገኘው እና ለሳዑዲ ድንበር ቅርብ ወደሆነችው ሳዳ ግዛት እንደሚያሻግሯቸው ይናገራሉ።

በርካታ ስደተኞች ከሳዑዲ ጋር እየተዋጉ የሚገኙት የሁቲ አማጺያን እና ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎቹ በጥምረት እንደሚሠሩ ገልጸው፤ በትውልድ የመናውያን የሆኑት አዘዋዋሪዎች ለሁቲ አማጺያን ካስረከቧቸው በኋላ አማጺያኑ ወደ ማጎሪያ ካምፖች ካስገቧቸው በኋላ “የመውጫ” ገንዘብ እንደሚከፍሉ ስደተኞቹ ይገልጻሉ።

ስደተኞች እንደሚሉት አብዛኛውን ጊዜ በቁጥር 200 የሆኑ ሰዎች በአንድ ላይ በመሆን ድንበር ለማቋረጥ ሙከራ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ወላጆቻቸው አብረዋቸው የሌሉ ሕጻናት እና ሴቶች ያሉባቸው ቡድኖች ድንበር ለመሻገር ሲሞክሩ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

ስደተኞቹ የሳዑዲን ድንበር እንደተሻገሩ ሞርታር እና ሌሎች ፈንጅዎች በሳዑዲ ወታደሮች እንደሚተኮሱባቸው ይገልጻሉ።

በሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች በቁጥጥር ሥር የሚውሉም በእስር ቤቶች ለወራት ታስረው እንደሚቆዩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጨምረው ተናግረዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ፀረ ፈንጅ የሆኑ እና ከባድ መሳሪያ የተገጠመባቸው ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች የታጠቀ የሳዑዲ ድንበር ጥበቃ ድንበር ላይ ጥበቃ ሲያደርግ ባገኘው የሳተላይት ምስል ማረጋገጡን ገልጿል።

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ስደተኞች “አካላቸው ስለሚቆራረጥ ማንነታቸውን መለየት እንኳን አዳጋች የሆኑ በርካቶች አሉ” ብሏል አንድ ለመብት ተሟጋች ቡድኑ ቃሉን የሰጠ ስደተኛ።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ሕይወታቸው ያለፈ እና በጽኑ የተጎዱ ስደተኞች ምሥሎች እና ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የመቃብር ስፍራዎችን የሚያሳዩ ቪዲዮችን ማመሳከር ችሏል።

ኢንተርናሽናል ሪሃብሊቴሽን ካውንስ ፎር ቶርቸር ቪክትምስ የተባለ ተቋም መርማሪዎች በምሥሎች ላይ የሚታዩ ሰዎች የተጎዱት ወይም ሕይወታቸው ያለፈው በፍንዳታ፣ በጥይት በመመታት እና በቃጠሎ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ያነጋገራቸው ስደተኞች ድንበር ጠባቂዎቹ ከቅርብ ርቀት እንደተኮሱባቸው፣ ተቀጣጣይ መሳሪያ እንደተኮሱባቸው እና በብረት እንደሚደበድቧቸው ተናግረዋል።

አንድ የ17 ዓመት ስደተኛ የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች እርሱ እና ሌላ ስደተኛ ሁለት ሴት ስደተኞችን እንዲደፍሩ እንዳስገደዷቸው ተናግሯል። ይህ ታዳጊ ስደተኛ አንዲት ስደተኛን አልደፍርም ያለን ሌላ ስደተኛ መግደላቸውን ጨምሮ ተናግሯል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ሳዑዲ አረቢያ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መግደል በአስቸኳይ ማቆም አለባት ብሏል።

የሚመለከታቸው ተቋማት እና መንግሥታትም ሳዑዲ ይህን ፖሊሲዋን እንድታቆም እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጫና መፍጠር አላቸው ሲል አሳስቧል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ጉዳዩ ያሳስበናል የሚሉ መንግሥታት በሳዑዲ እና በሁቲ አመራሮች ላይ ማዕቀቦችን መጣል አለባቸው ያለ ሲሆን፣ በስደተኞች ላይ የተፈጸመው ግድያ በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር ስለመስተካከሉ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፍ አጣሪ ቡድን መቋቋም አለበት ብሏል።

credit – BBC Amharic


Exit mobile version