Site icon ETHIO12.COM

የደብረታቦር ውጊያ፤ ከተማ መሽጎ ወደ ተራራ ማጥቃት፤ ሰላማዊ ዜጎች ከተማ ውስጥ ተገድለዋል

በሽምግልናና በይቅርታ ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ የተጀመረው ጥረት እየተሳካ መሆኑ ተሰማ

ባለፈው ሳምንት ደብረታቦር ውጊያ እንደነበር ተመልክቷል። ውጊያው ከተማ ውስጥ መሽገው ራሳቸውን ፋኖ ብለው በሚጠሩና በአገር መከላከያ ሰራዊት መካከል ነበር። ከስፍራው በተገኘው መረጃ መሰረት ውጊያው የተከፈተው ስትራቴጂክ የሆነውን የታቦር ተራራ ወይም ከፍተኛ ቦታ ከመከላከያ ለመንጠቅ በተያዘ ዕቅድ ነው።

በህልውናው ጦርነት ወቅት ትህነግ ደብረታቦርን በመቆጣጠር ወደ ባህር ዳርና ጎንደር ለመገስገስ ከፍተኛ መስዋዕት ከፍሎ ውጊያውን በኪሳራ እንደቋጨ በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።

ስለውጊያው ያወጉን እንዳሉት ቅዳሜ ነሐሴ 20/2015 ዓ. እስከ ሰኞ ውጊያ ነበር። ያፋኖ ሃይል ከተማ ውስጥ ሆኖ ነበር የሚዋጋው። ውጊያው በድሽቃ ጭምር የታገዘ በመሆኑ ከባድ ነበር። ተራራው ላይ የሰፈረው የአገር መከላከያ ላይ ፋኖዎቹ ጥቃቱን አጠናክረው ስፍራውን ለመቆጣጣር ቀለበቱን እያጠበቡ ገፍተው ነበር።

ምላሽ በመስጠት ራሱን መከላከል የጀመረው መከላከያ ጥቃቱ ሲጨምር በስፍራው ገዢ መሬት ይዞ የነበረውን አነስተኛ ሃይል በፍጥነት ለማጠናከር ሃይል ጭምሯል። ሃይል ከጨመረ በሁዋላ እሁድ አመሻሽ ላይ ቀለበት ሰርቶ ገዢ መሬት የያዘውን ሃይል በማገዝ ማጥቃት ሲጀመር ስልክ እንዲጠፋ ተደረገ።

ፋኖዎቹ በስልክ ግንኙነት የሚዋጉ በሞኑ ግንኙነታቸው ተበጠሰ። መከላከያም ከጀርባና ከጋራ ሆኖ በወሰደው ጥቃት በአጭር ሰዓታት ውስጥ የፋኖ ሃይል በነበረበት ሆኖ መዋጋት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጠረ። ምስክሮች ምን ያህሉ ከውጊያው ቀጠና እንደወጡ፣ ከሁለቲኡም ወገን ስለደረሰው ጉዳት ለመናገር ባይችሉም የፋኖ ሃይል ወደ ጋይንት አቅጣጫ መሸሹንና መከላከያም ከጋይንት አቅጣጫ ያለውን ተጠባባቂ ሃይል አሰማርቶ እግር በግር ከሶስት አቅጣጫ እየተከታተላቸው እንደሆነ አመልክተዋል።

አሁን ላይ ደብረ ታቦር ሃዘን ላይ ናት። ከተማ ውስጥ መሽጎ የሚዋጋውን ሃይል ለመምታት ይሁን ከራሳቸው ከፋኖዎቹ በይፋ ዝርዝር ባይቀርብም ንጹሃን ዜጎች ሞተዋል። ተቋማት ተጎድተዋል። ሆስፒታል ተጎድቷል።

በአማራ ክልል የተጀመረውን ጦርነት የሚመሩም ሆነ በቅርብ ሆነው መረጃ በማሰራጨት የሚያገለግሉ በግልጽ እንቅስቃሴውን ጠቅሰው፣ በአሃዝና በመረጃ ያሉት ነገር የለም።

የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ጠቅላይ መምሪያ የአማራ ክልልን ወደ ሰላም ለመመለስ እየተሠራ ያለውን  የሕግ ማስከበር ሥራ ገምግሞ የህግ ማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ ማስተላለፉ አይዘነጋም።

(ቢቢሲ እዚህ ላይ ያንብቡ )የከተማ ነዋሪዎችን ” አሁን ውጊያ የለም የተኩስ ድምጽም አይሰማም። መከላከያ ቤት ለቤት እየዞረ እየፈተሸ ነው” ብሏል። ህይወታቸው ያለፉ ወገኖች ቁጥር ለጊዜው በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ይፋ ባለመሆኑ ለማቅረብ አልቻልንም። ይሁን እንጂ ከመከላከያም ሆነ ከፋኖ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ምስክሮች ገልጸዋል።

የኮማንድ ፖስት ከፍተኛ አመራሮች አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ ጀኔራል አበባው ታደሰ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ፣ የመከላከያ ከፍተኛ ጀኔራል መኮንኖች እና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግምገማው ሲካሄድ ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር እየተላቀቀ ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ሕግ የማስከበር ሥራ ውጤታማ መሆኑን አስታውቀው መግለጫ ማሰራጨታቸው ይታወሳል።

በክልሉ ያለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴም መሻሻል ማሳየቱ በግምገማው መነሳቱን አሚኮ ዘግቧል፡፡ በቀጣይ የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ሥራ በውጤታማነት በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ተሟላ ልማት እንዲገባ እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ መምሪያው አመልክቶ፣ ሕብረተሰቡ የሕግ ማስከበር ሥራው እንዲሳካ ላሳየው ሁሉ-አቀፍ ድጋፍ ጠቅላይ መምሪያው አመስግኗል፡፡

በቀጣይም ሕብረተሰቡ በየደረጃው ካለው የሕግ አስከባሪ እና የኮማንድ ፖስት አመራር ጋር በመሥራት የተለመደ አስተዋጽኦውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቅላይ መምሪያው ጠይቆ ነበር፡፡ ግምገማው የተካሄደው የኮማንድ ፖስቱ ከፍተኛ አመራሮች የጎርጎራ ፕሮጀክትን ከጎበኙ በኋላ እንደነበርም ተመልክቷል።

ይህ በንዲህ እንዳለ አገራዊ እርቅ ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ ዜጎች፣ የሃይማኖት ሰባኪዎች፣ አሜሪካ፣ አፍሪካ ህብረትና አግባብ ያላቸው ተቋማት ጦርነቱ ቆሞ ንግግር እንዲጀመር እይወተወቱ ነው። የስራ መልቀቂያ ያቀረቡት የክልሉ መሪ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በተደጋጋሚ “እንነጋገር” ሲሉ ጥሪ ማቀረባቸው የሚታወስ ነው።

የሰላም ንግግሩ ግፊትና ጥያቄ እንዳለ ሆኖ “ጦርነቱ በቃን” ያሉ የተዋጊዎቹ አንዳንድ መሪዎች በታዋቂ ሰዎች ሽምግልናና ንግግር ወደ ሰላም አማራጭ ለመመለስ መስማማታቸው እየተገለጸ ነው።

መረጃው ከገለልተኛ አካል በይፋ ማረጋገጫ ባይሰጥበትም፣ ይቅርታ አውርደው ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ ንግግር የጀመሩ በቅርቡ ስምምነታቸውን ይፋ ያደርጋሉ ብለው እንደሚገምቱ ዜናውን ያጋሩን አመልክተዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሰላም ንግግር እንዳለ መጠቆማቸው አይዘነጋም። ይህንኑ የሰላም ንግግር ጭምጭምታ ተከትሎ የንቅናቄው አጋር እንደሆኑ የሚታወቁ፣ ለንቅናቄው መመሪያና አቅጣጫ የሚይሳዩ ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው። ወደ ሰላም ለመመለስ ንግግር የጀመሩትን በስም ባይጠቅሱም በደፈናው ” ገንዘብ ተቀብላችሁ ነው። ከሃዲዎች” በሚል ሰፋፊ ጽሁፍ እያሰራጩ ነው።

የአማራ ህዝብ ተፈርጆ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በስፋት መከራ ሲቀምስ፣ ሲገደልና ሲፈናቀል እንደነበር መካድ እንደማይቻል የሚጠቅሱ ” የአማራን መከራ ለማስቆም፣ የተጠና፣ ዓላማው የሚታወቅ፣ የበሰሉ መሪዎች ያሉት፣ ወጥ አመራር የሚሰጥበት፣ ከምንም በላይ ማንም እየተነሳ የማይዘላብደበትና ከሌሎች የአገሪቱ ህዝብ ጋር በማያጋጭ መልኩ የተገራ የአርቆ አስተዋይ ትግል አስፈላጊ ነው። ከዚህ መለስ ያለው የጨረባ ተስካር አይነት ትርምስ ዳግም ሌላ ጉዳት ከማስከተሉም በላይ ኪሳራው እስከወዲያኛው ይሆናል” ሲሉ በተደጋጋሚ አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል።


Exit mobile version