ETHIO12.COM

የበርሊን ማራቶን ባለማዕረግ ትግስት እነ ዱቤ ጂሎ ቢሳተፉ ታዝረከርካቸው ነበር

በማራቶን ከሁለት ደቂቃ በላይ ማሻሻል እጅግ የሚደነቅና ያልተለመደ ነው። ባለሙያዎቹ ወይም አሰልጣኞቹ የሮጠችበትን ፍጥነት በሰዓትና ርቀት ከፋፍለው ቢያቀርቡት ምን አልባትም ወንዶችን የሚገዳደር ፍጥነት ተጠቅማ ሮጣለች። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቴክኒክ ዳይሬክተርና የአትሌቶች ኮሚሽን ሰብሳቢ የነበሩት የዛሬው የተከበሩ ዱቤ ጅሎ አይነቱን ሯጮችን አዝረክርኮ ማሸነፍ የሚያስችላትን ሃይል አሳይታለች። የበርሊና ባለ ማዕረግ ትዕግስት!!

ተግስት ከአሯሯጮ ጋር ስትምዘገዘግ ላየ ልዩ ነበረች። ለምሳሌ ያህል የዛሬውን የፓርላማ አባልን አነሳናቸው እንጂ፣ በመጠቃቀም በአረብ አገሮች ማራቶን እያስመለሳቸው የሚሸነፉትን ሯጮች ያስታወሰችን ትዕግስት፣ 2 ሰዓት ከ14ደቂቃ ከ04 ሰኮንድ የገባችበትን ሰዓት ያላስመዘገቡ ወንድ አትሌቶች እጃቸውን አፋቸው ላይ እንዲጭኑ ታስገድዳለች።

አትሌቷ የትኛው ሃኪም “ዋጋ የለሽም” እንዳላት ባይገለጽም ግን ተሳዋን በልተዋታል። በቡዳፔስት የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያን አትሊቲክስ ፌዴሬሽን ገበና ለሰማን ” በቅቶልሻል” የሚለው ድምዳሜ እንግዳ አይሆንም። ምክንያቱም እርጅናና አልኮል የተጠናወተው የፌዴሬሽኑ የህክምና ማዕከል የቡዳፒስትን ሙቀት ያየው እዛው ለሽርሽር ሄዶ ሙቀቱ ልቡን ሲያጠፋው ነውና።

ቡዳፒስት አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አስለጣኝ የውጤቱን መንገራገጭ ተከትሎ ” ሙቀት መሆኑ እየታወቀ ቢያንስ ድሬዳዋና አዋሽ አካባቢ መለማመድ ሲገባን ያስታወሰም አልነበረም። ቤቱ ደንዝዟል። አመራሩም የልምድ እንጂ ሳይንሳዊ መርህ የሚከተል አይደለም። ከተናገርንም ….” ብለው ጀምረው ” እስኪ ተወኝ። ከቻልክ ናና ልጆቹን አናግር” ሲሉ ጨርሰዋል። የህክምና ክፍሉ በርክታ እንከን ያለበት። በስህተት የሚንቦራጨቅ፣ በአጉል መቀራረብ ላይ የተቸከለ፣ ተተኪ ባለሙያ አገር ውስጥ እንደሌለ የተቆጠረበት እንደሆነ መናገር ከጀመረ የሁለት ኦሊምፒክ ዘመን አልፏል።

አዲስ አሰልጣኝና አዲስ ባለሙያ በሩቁ የሚገፋበት፣ አትሌቶቹ በሚመቻቸው አሰልጣኝ እንዳይሰሩ የሚገደዱበት፣ አትሌቲክስ የግል ብቃት ውድድር ሆኖ ሳለ በቅጥፈት የቡድን ስራ ሰበብ ባርነት የታወጀበት ቤት እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ትችት የሚነሳበት ፌዴሬሽኑ፣ ለመጪው ኦሊምፒክ የሚወቀስበትን ጉዳይ ለማስወገድ ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል። ደራርቱ መልካምነትሽ እንዳለ ሆኖ እውቀት ባላቸው ሰዎች መመራትና መታገዝ እንደሚገባሽ መቀበል ይገባሻል። በአሮጌ በሬ አይታረስምና ቤቱን አድሺ። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም በሁዋላ በደቦ ጸብና ንትርክ ውስጥ እንዳትገባ ሚዲያና አትሌቶቹን፣ ታዋቂ ልምድ ያላቸውን ሯጮች፣ የተገፉትን ጨምሮ በማካተት ለመጪው ኦሊምፒክ የዝግጅት ግብአት ሰብስቡ። በግልጽ የቴክኒኩን ስራ ማንና እንዴት እንደሚመራው ከአሁኑ አሳውቁ። ቢቢሲ ስለ የትእግስት የዘገበውን ከስር ያንብቡ።

አትሌቷ ከገባችበት ሰዓት እስከ ሮጠችበት ጫማ አድናቆት ተቸሮታል። ትዕግሥት ከጤናዋ ጋር እየታገለች ለውጤት የበቃች አትሌት መሆኗን ብዙዎች አንስተው ድሏን አወድሰዋል።

በጀርመን በርሊን በተካሄደ 48ኛው የማራቶን ውድድር አትሌት ትዕግሥት አሠፋ የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል ነበር ያሸነፈችው።

የ26 ዓመቷ አትሌት እንደ አውሮፓውያኑ 2019 በተካሄደው የችካጎ ማራቶን በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ ተመዝግቦ የነበረውን 2:14.04 ከሁለት ደቂቃ በላይ አሻሽላለች።

ትዕግስት ከውድድሩ በኋላ እንደተናገረችው “የዓለም ክብረ ወሰንን የመስበር ፍላጎት ቢኖረኝም፣ አሁን ይሆናል ብዬ ግን አላሰብኩም፤ ይህ ጠንክሬ የመሥራቴ ውጤት ነው” ብላለች።

ከአስደናቂ ድሏ በኋላ ቢቢሲ ትዕግስትን አግኝቶ ለማናገር ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርግም ባላት ተደራራቢ ፕሮግራሞች ምክንያት ለአሁን ሳይሳካ ቀርቷል። ነገር ግን ከአሠልጣኗ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

አሠልጣኟ ገመዶ ደደፎ፣ ትዕግሥት በጀርመን በርሊን ለነበረባት ውድድር ሁለት አሯሯጮችን አዘጋጅተው እንደ ነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንን የማራቶን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ላለፉት አራት ወራት ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አልሸሸጉም።

“ሪከርዱን ለማሻሻል ጥሩ ልምምዶችን፣ ጥሩ ዝግጅቶችን ስናደርግ ነበር” በማለት አሠልጣኝ ገመዶ የትዕግስትን ሃሳብ አጠናክረዋል።

አሠልጣኝ ገመዶ፣ አትሌት ትዕግሥት ስታሸነፍ ስለተሰማቸው ስሜት ሲናገሩ “ለፍተናል፣ የለፋንበትን ውጤት ደግሞ በቀላሉ ነው ያገኘነው” ይላሉ።

አሠልጣኙ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአትሌት አማኒ በሪሶ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘታቸውን በማስታወስ፣ አሁን ደግሞ የዓለም ክብረ ወሰንን በመስበራቸው ለእርሳቸው ትልቅ ነገር መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትዕግሥት እና 400 ፓውንድ የሚያወጣው መሮጫ ጫማዋ

ትዕግሥት በበርሊን ማራቶን ከሁለት ደቂቃ በላይ የዓለም ሪከርድን አሻሽላ ስታሸንፍ ጫማዋን አውልቃ ከፍ አድርጋ ስታውለበልብ ታይታለች ። የትዕግሥት ድል ለአትሌቶች ብቻ ሳይሆን ለመሮጫ ጫማ አምራቾችም የፉክክር መድረክ የከፈተ ይመስላል። ትዕግሥት የሮጠችበት አዲዳስ ጫማ ይፋ ከሆነ ገና ሳምንት አልሞላውም።

ይህ አዲዜሮ አዲዮስ ፕሮ ኢቮ 1ኤስ [Adizero Adios Pro Evo 1s] የተሰኘው የመሮጫ ጫማ በአምራቹ “በልዩ ቴክኖሎጂ የረቀቀ የሩጫ ሜዳ ላይ ያለ ተግደሮትን የሚያሸንፍ” ተብሎ ተንቆለጳጵሷል። ይህ ግን ለገበያ ማሻሻጫ የተቀመጠ ማግባቢያ ብቻ አይመስልም።

ቢቢሲ አሠልጣኝ ገመዶን ስለዚሁ ትዕግሥት ስለሮጠችበት ጫማ ጠይቆ እንደተረዳው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሊን ማራቶን ላይ የተሮጠበት መሆኑን ማረጋገጫ አግኝቷል።

የጫማ አምራች ፋብሪካዎች በተለያየ ጊዜ የመሮጫ ጫማዎችን እንደሚያሻሽሉ ያስታወሱት አሠልጣኝ ገመዶ፣ አዲዳስም ይህንን አዲስ ጫማ በበርሊን ማራቶን ላይ ማስተዋወቁን ይናገራሉ።

“ጫማው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሮጠበት በበርሊን ማራቶን ነበር። በመጀመሪያ ውድድር ይህንን ዓይነት ብቃት ማሳየቱ. . . ፣ ጫማ በሂደት ነበር የሚስተካከለው፣ ነገር ግን በመጀመሪያው ውድድር ትልቅ ብቃት ነው ያሳየው። ልጅቷም በእሱ በመሮጧ ትልቅ ብቃት አሳይታለች። ለዚያ ነው ስሜታዊ ሆና የነበረችው” ብለዋል።

በውድድሩ ላይ ዋናው የአትሌቱ ብቃት መሆኑን ያስታወሱት አሠልጣኝ ገመዶ፣ መሮጫ ጫማም የራሱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ።

“አይደለም የምትሮጥበት ጫማ የምትለብሰው ልብስ ይረዳሃል” ካሉ በኋላ “አየር ዝውውር ካለው፣ ብዙ የማይበላህ ከሆነ፣ የማይረብሽህ ከሆነ፣ የማይረዳህ ነገር የለም” ይላሉ። አትሌት ትዕግሥት አሰፋ የዓለም ሪከርድን በማሻሻል ካሸነፈች በኋላ ዓለም ሁሉ የሚያወራው ስለድሏ ነው።

ለመሆኑ ምን ያህል ትሸለማለች? ለእርሶስ ምን ያህል ይደርሳል? ሲል ቢቢሲ ለአሠልጣኝ ገመዶ ጥያቄ ቢያርብም፣ አሠልጣኝ ገመዶ “ይህ የግል ጉዳይ ስለሆነ አይነገርም” በማለት ጥያቄውን አልፈውታል።

ባለ ክብረወሰኗ ትዕግሥት

ትዕግሥት 400 እና 800 ሜትር ሮጣለች። የግማሽ ማራቶን አሸንፋለች። በ2016 እኤአ በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በ800 ሜትር ኢትዮጵያን ወክላለች። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ከጤናዋ ጋር ትታገል እንደነበር አሠልጣኝ ገመዶ ያስታውሳሉ።

እርሷም እግሯ ላይ በደረሰባት ህመም በሕክምና ባለሙያዎች ‘ከዚህ በኋላ ወደ አትሌቲክስ የመመለስ እድልሽ ጠባብ ስለሆነ ሌላ ነገር ብትሞክሪ’ ተብላ እንደነበር ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ባደረገችበት ወቅት ተናግራ ነበር።

አትሌት ትዕግሥት የ800 ሜትር ሯጭ ነበረች። በዚህ መስክ ውጤት ሳይቀናት ሲቀርም ወደ አሜሪካ እሄዳለሁ ብላ ተነስታ እንደነበር አሠልጣኟ አይረሱም።

የምትሮጥበትን ርቀት መቀየር እንጂ ሩጫን ጥሎ መሄድ መፍትሄ እንደማይሆን ተነጋገሩ። አትሌት ትዕግሥት ግን ቁርጭምጭሚቷ አካባቢ በተደጋጋሚ ትታመም ነበር።

ትዕግሥትን ያከሟት የሕክምና ባለሙያዎች ሩጫ እንድታቆም ነግረዋት እንደበር አሠልጣኝ ገመዶም ያስታውሳሉ። ስለዚህ የትራክ ሩጫ ሊስማማት አልቻለም። ከዚህ በኋላ ነው የጎዳና ላይ ሩጫ እንድትሞክር የተደረገው። በስፔን ቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን ስትሮጥ እግሯ ላይ የጡንቻ መመንጨቅ ስሜት እንደነበራት ያስታውሳሉ። ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎች ሲያይዋት፣ ጅማቶቿ ሙሉ በሙሉ ተጎድተው ነበር።

ከዚያ በኋላ ሰው ሁሉ የገጠማት ችግር ‘ወደ ቦታው አይመለስም’ ይላት እንደነበር የሚያስታውሱት አሠልጣኝ ገመዶ፣ ትዕግሥት በጉዳቷ የተነሳ የመሮጫ ጫማ ማድረግ ስላልቻለች ወደ ጎዳና ሩጫ ትኩረቷን አደረገች።

አሠልጣኝ ገመዶ “ተስፋ ተቆርጣ ነበር። ያን ጊዜ ሁላችንም ተስፋ የመቁረጥ ነገር ውስጥ ነበርን። ግን ከአጠገቧ አልራቅንም ነበር። ያንን ሁሉ አልፋ ለዛሬ ውጤቷ መብቃቷ ትልቅ ነገር ነው” ብለዋል።

አክለውም ባለፈው ዓመት በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ካሸነፈች በኋላም በመታመሟ የለንደን ማራቶን አንድ ወር ሲቀረው መሰረዟን ይናገራሉ። የለንደን ማራቶን ላይ ባለመሳተፏ ደግሞ የዓለም አትሌቲክስ ላይ ሳትካፈል ቀርታለች።

አትሌት ትዕግሥት በጣም ታታሪ፣ ለሥራዋ ቅድሚያ የምትሰጥ ናት የሚሉት አሠልጣኝ ገመዶ፤ የተባለችውን ወደ ተግባር የምትቀይር አትሌት መሆኗንም ይመሰክራሉ። “ልክ አንደ ስሟ ትዕግሥት ያላት” በማለትም ያንቆለጳጵሷታል።

አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ፣ ትዕግሥት በድሉ ምን እንደተሰማት ሲናገሩ ይህ ሦስተኛ ማራቶኗ በማስታወስ ነው። “በሦስተኛ ማራቶኗ የዓለምን ሪከርድ ማሻሻሏ ለእርሷ ትልቅ ነገር ነው፤ ደስተኛም ነች።”

ሪከርዱ ከሁለት ደቂቃ በላይ ነው የተሻሻለው እና በዚህን ያህል በብዙ ደቂቃ ለማሻሻል አቅዳችሁ ነበር ልምምድ ስትሰሩ የነበረው? የቢቢሲ ሌላው ጥያቄ ነበር።

“እኛ 13 ቤት [2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ] ትጨርሳለች ብለን ገምተን ነበር። እርሷ ግን 11 አደረገችው። ያው ለ12 ቅርብ ነው። [2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ] እንግዲህ ትልቅ ነገር አድርጋለች። ሰውነቷ ከቻለ መሄድ ነበረባት። እርሱንም አድርገዋለች። ያስደስታል” ሲሉ መልሰዋል።

ከበርሊን በኋላስ?

አሠልጣኝ ገመዶ ወደፊት ሲመለከቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ እንደሚጠብቃቸው አልዘነጉም። ኦሊምፒክ ለአገርም ለአትሌቶችም ትልቅ ነገር ነው። በርካታ ታዋቂ አትሌቶችም የሚሳተፉበትን ውድድር አሸንፈው፣ የአገራቸውን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ እና ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ለማስፈር ተዘጋጅተው ነው የሚመጡት።

አሠልጣኝ ገመዶም ይህንኑ ከግንዛቤ ያስገባ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ። አሠልጣኙ ከውድድሩ በፊት ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ የቀድሞ ሴቶች ማራቶን ሪከርድ ባለቤት የነበረችው ኬንያዊቷ አትሌት ብሪጂድ ኮስጌ የተናገረችውን እና ሴቶች ከ2 ሰዓት 10 ደቂቃ የመግባት ብቃት አላቸው የሚለውን አስተያየት እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።

ይህንንም ቢቢሲ ጠይቋቸው ሲያስረዱ ሴቶች እና ወንዶች በግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ የገቡበት ሰዓት የ5 ደቂቃ ልዩነት ብቻ እንዳለው ያስረዳሉ።

የወንዶች ማራቶን የዓለም ሪከርድም ሁለት ሰዓት ከአንድ ደቂቃ መሆኑን በማንሳት እና የግማሽ ማራቶን ስሌትን በማየት ሴት አትሌቶች 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ መግባት ይችላሉ የሚለው ሀሳብ እንደሚያስማማቸው ያብራራሉ።

ሴቶች በበርካታ ጫና ውስጥ ሆነው እንደሚሮጡ የሚናገሩት አሠልጣኝ ገመዶ፣ ሁኔታዎች እየተመቻቹላቸው በመጡ ቁጥር የሚገቡበት ሰዓት እየተሻሻለ እንደሚሄድ በማንሳት ወደፊት ከ2 ሰዓት 10 በታች ይገባሉ የሚል ሙሉ አምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።

አሠልጣኝ ገመዶን በጥቂቱ

ከአሠልጣኝነታቸው በፊት ሆለታ አካባቢ የስፖርት ሳይንስ እና የባዮሎጂ መምህር ነበሩ። ባለቤታቸው ለይላ አማን ደግሞ ሯጭ ናት። የአክስታቸው ልጅ ሐጂ አድሎ ደግሞ የአትሌቲክስ ማናጀር ነው። ይህ የሳባቸው አሠልጣኝ ገመዶ እርሳቸውም አትሌቶችን ማሰልጣን ጀመሩ።

አሠልጣኝ ገመዶ በስፖርት ሳይንስ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በርካታ አትሌቶችን በማራቶን፣ በ10 ሺህ እና በ5ሺህ ማሠልጠናቸውን ይናገራሉ።

በአሠልጣኝነት እና በማናጀርነት ላለፉት 18 ዓመታት መቆየታቸውን የሚናገሩት አሠልጣኝ ገመዶ፣ ትዕግሥት አሰፋ፣ አማኔ በዳሶን የመሳሰሉ ውጤታማ አትሌቶች አፍርተዋል።

ከወንድ አትሌቶችም ቢሆኑ ማራቶንን ሁለት ሰዓት ከ03 ደቂቃ መግባት የቻሉ እንደ ታምራት ቶላ፣ ነሚ ብርሃኑ፣ ሲሳይ ለማ፣ ሂርጳሳ ነጋሳ፣ ታደሰ ታከለን የመሰሉ አትሌቶችን አሠልጥነዋል።

ከዚህ ቀደምም እንደ ትርፌ ፀጋዬ፣ አሰለፈች መርጊያን የመሰሉ አትሌቶች በእርሳቸው ስር ሲሰለጥኑ አንደነበር ይጠቅሳሉ።

ሙሉ ዘገባው የቢቢሲ ነው


Exit mobile version