Site icon ETHIO12.COM

“አቋጥሬ” በአማራ ክልል እያጫረሰ ነው፤ ” ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም ” ነዋሪዎች

“አቋጥሬ አይጫረሰ ነው” አሉ አንድ አዛውንት መላው እንደጠፋቸው በመግለጽ። “አቋጥሬ ምንድን ነው?” ሲባሉ፣ በአጭሩ ደምን መበቀለ ወይም ነብስን በነብስ ማካካስ የሚባለው የቆየ ልማድ ነው።

“ጎበዝ ተጫረሰ” ያሉት የጎጃም ብቸና ከተማ አቅራቢያ ነዋሪ አዛውንት “እንደው መላም የለው” በማለት ብዙም ማብራራት አይፈልጉም። ዜናውን ያጋራን የአዲስ አበባ ተባባሪያችን ቤተሰቦቻቸው ጋር መጥተው ያገኛቸው አዛውንት ክፉኛ ሃዘን ገብቷቸዋል።

አማራ ክልል እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፋኖ ሃይሎች ወደ ከተማ ሲገቡ እስር ቤት ተከፍቶላቸው የወጡ ታራማሚዎች ቀደም ሲል የከሰሷቸውን ሰዎች መበቀላቸውን አዛውንቱን ጠቅሶ የዘገበው ተባባሪያችን፣ አንዱ ሌላውን እያደፈጠ ምላሽ በመስጠት በቀሉ ሳይታሰብ ተስፋፍቷል። የማቆሚያው መላም ቀላል አይመስልም።

በዚሁ መነሻ በተለያዩ የጎጃም መንደሮችና ከተሞች ተመሳሳይ ችግር ስለመኖሩ ለማጣራት በተደረገ ሙከራ ነገሩ ቀጣዩ የማህበራዊ ቀውስ ሊሆን እንደሚችል ፍርሃቻ ያላቸውን ተባባሪያችን አመልክቷል። ያነጋገራቸው የብቸና አቅራቢያ ነዋሪ በቀን የሚገዳደሉትን ሰዎች አማካይ ቁጥር ጠቅሰው ” አይ አገር ደም ኡእየቋጠረ ነው። ነገሩ ሁሉ ግምኛ ነው” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል። ክፉኛ ማዘናቸውን በሚያሳይ መልኩ ቁና ተንፍሰው ” ተወኝ እስኪ” በማለት ዝምታን መርጠዋል።

ከአማራ ክልል የድርቅ፣ የረሃብና የማህበራዊ ቀውስ ዜናዎች እየበረከቱ ነው። ፋታ የማይሰጡ የድርቅ አሳሳቢ ችግሮች ከአስድንጋጭ የሞት መረጃ ጋር እየተሰሙበት ያለው አማራ ክልል ከጦርነት ያለገገመ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ የከፋ ቀውስ እንዳይከሰት ስጋቱ ከፍተኛ ነውልል በዚህ ሁሉ ስጋት ላይ “ለአማራ ህዝብ እንታገላለን” ከሚሉት ጎን ለጎን ታጠቀው የሚዘርፉ፣ ህዝብ ላይ መዋጮ እየጣሉ የሚያሰቃዩ እንዳሉም ህዝብ እየገለጸ ነው።

ቲክቨሃ የአሜሪካንን ድምጽ ጠቅሶ “በአማራ ክልል ባህር ዳር እና ጎንደር ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ነዋሪው የዋጋ ንረቱን መቋቋም አልቻለም” በሚል ርዕስ ከስር ያለውን ዜና አስፍሯል።

የባህር ዳር ነዋሪው አቶ አለሙ ይርዳው ባለፈው ሳምንት ጤፍ ለመግዛት ወደ ገቢያ በወጡበት ወቅት ከወር በፊት በ10 ሺህ ብር የገዙት ጤፍ በሺዎች ብር ጨምሮ እንዳገኙት ገልጸዋል።

እኚሁ ነዋሪ ከ6 እና 7 ወር በፊት አንድ ኩንታል ጤፍ 6,700 ብር ገደማ መግዛታቸውን አስታውሰው አሁን 13,000 ብር መባሉን ገልጸዋል።

” በጣም ደንግጫለሁ ፤ ከእጥፍ በላይ ነው የጨመረው ዝቅተኛው ጤፍ 11 ሺህ 500 እና 12 ሺህ 500 ነው የሚባለው እኔ የገዛሁት 13 ሺህ ብር ነው ” ብለዋል።

ለምን በዚህ ልክ እንደጨመረ ነጋዴዎችን ጠይቀው የተሰጣቸው ምላሽ ” ከትራንስፖርት አንፃር አቅርቦት የለም ፣ በየቀኑ መንገድ ይዘጋል ” የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።

ከጤፍ በተጨማሪ ሽንኩርት አንድ ኪሎ 110 ብር እንደገዙ አመልክተዋል። ቲማቲምን ጨምሮ ሌሎችም የዕለት ዕለት ግዢዎች ላይ ዋጋ ጨምሯል ብለዋል።

” 13 ሺህ ብር ጤፍ ተገዝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻል አይገባኝም ፤ በተለይ መካከለኛ እና ዝቅተኛ እንደኔ አይነት ገቢ ያላቸው የወር ደሞዝተኞች መኖር የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ” ሲሉ አክለዋል።

ይህንን እየፈጠረ ያለው አንደኛው ወቅታዊው የመንገድ መዘጋት ነው ፤ በተጨማሪ ስግብግብ ነጋዴዎች ወቅቱን ተጠቅመው ሰው እንደተቸገረ አውቀው በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ በመሆኑ ነው ብለዋል።

አማራ ክልል በተለይ ምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም ጤፍ አምራች ቢሆንም የአካባቢው ነዋሪ በዚህ ዋጋ ለመሸመት መገደዱ አስደንጋጭ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህ ምክንያት እየሆነ ያለው ግጭት በፍጥነት ካልቆመ ህዝቡ በኑሮ ይጎዳል ብለዋል።

አንድ ስማቸው እንዲገልፅ ያልፈለጉ ከምዕራብ ጎጃም አዴት እና ጎንጂ ቆለላ ጤፍ አምራች አካባቢዎች ጤፍ እያመጡ የሚሸጡ ነጋዴ ፤ በወቅታዊ ግጭት ምክንያት አርሶ አደሩ ምርቱን ወደገበያ እንደማያወጣ ገልጸዋል።

” አርሶ አደሩ በሰላም ውለን መግባት ስላልቻልን ምርቱን እያወጣ አይደለም። ነጋዴው ደግሞ ያገኘውን ይዞ ይመጣል ” ብለዋል። እኚሁ ነጋዴ ጤፍ 12 ሺህ ብር እየሸጡ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጎንደር ነዋሪ የሆኑት ይፍቱ ስራማረው ፤ የዋጋ ንረቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል። ” እውነት ለመናገር እንኳን በሁለት ዓመት ውስጥ በዚህ ወር ውስጥ እንኳን ከፍተኛ ጭማሪ ነው ያለው። 30 እና 20 ብር ስንገዛው የነበረው እቃ አሁን 100 ቤት ውስጥ ነው።

ሽንኩርት ከግርግሩ በፊት ከ50 – 55 ብር ነበር አሁን ሱቅ ውስጥ እስከ 120 ብር ዋና ገበያ እስከ 80-100 ብር ይሸጣል። 

ሞኮሮኒ ፓስታ ከአንድ ወር በፊት ነው የጨመሩት የ20 ብር ጭማሪ አለው ፤ ጤፍ 115 ብር – 120 ብር ይባላል በኪሎ ፤ አቅርቦትም ስለሌለ ይሆናል ” ሲሉ ተናግረዋል።

አዘዞ ከተማ የሚኖሩት የችርቻሮ  ነጋዴዋ ወ/ሮ አለሚቱ ደሴ ፤ ጤፍን ጨምሮ ሌሎች እህሎች ተወዷል ብለዋል።

” የገበያው ሁኔታ በጣም ከባድ ነው ለሻጭም ለገዢም … ቀይ ጤፍ 90 ብር ነው ፣ ነጭ ጤፍ  100 ብር አሁን ላይ ነው በጣም የጨመረው 60 እና 70 ብር ነበር ፤ ግጭት ከጀመረ አንስቶ እስከ 100 ብር ገብቷል።  ሽንኩርትም እስከ 100 ብር እየተሸጠ ነው። ” ብለዋል።

እህል እየተቀበሉ ያሉት የገጠሩ ማህበረሰብ ይዞ ሲመጣ እነድሆነ የገለፁት ወ/ሮ አለሚቱ ” ባለው ችግር የገጠሩ ነዋሪዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ አልቻሉም ” ሲሉ ገልጸዋል።


Exit mobile version