ብዙ ግፍ ለመስማት ተዘጋጁ፤ ሸዋሮቢት በትህነግ ወራሪዎች በቡድን የተደፈሩት እናት ራሳቸውን አጠፉ!

“መግደልም መድፈርም መብታችን ነው” – “ተገድደነው የዘመትነው” የሚሉት የትህነግ ታጣቂዎች

እድሜያቸው 50ዎቹን ያለፈው የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዋ አዛውንት በአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች በቡድን ከተደፈሩ በኋላ ራሳቸውን አጥፍተዋል። ፖሊስና የአካባቢው የአይን እማኞች በሥፍራው ለሚገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች እንደገለጹት፤ እድሜያቸው 50ዎቹን የተሻገረውና የሸዋሮቢት ከተማ ቀበሌ 02 ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ ሞሚና አህመድ (ስማቸው የተቀየረ) በአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች በመደፈራቸው የልጄን አይን ከማይ ብለው ራሳቸውን አጥፍተዋል።

ዛሬ ትህነግን በመቃወም ስለፍ ያደረጉ ካነገቡት መፈክሮች አንዱ

ወ/ሮ ሞሚና የማገዶ እንጨት በመሸጥና እንጀራ በመጋገር የሚተዳደሩ ሲሆን፤ የ15 ዓመት ታዳጊ ልጅ እንዳላቸው የሸዋሮቢት ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሀላፊ ኮማንደር አህመድ መሐመድ ለኢፕድ ገልጸዋል። ኮማንደሩ እንዳሉት፤ ግፈኛው ቡድን ልጃቸው ላይ በር ቆልፎ እናቱን ወደ ሌላ ቤት በመውሰድ አስነዋሪውን ግፍ ፈጽሟል።

እድሜያቸው 50ዎቹን የተሻገረውና የሸዋሮቢት ከተማ ቀበሌ 02 ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ

በተመሳሳይ ከወ/ሮ ሞሚና ጋር በአንድ ቤት በአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች አብረው የተደፈሩት ወይዘሮ አለምሸት አሸብር (ስማቸው የተቀየረ) ከሟች ጋር አንድ ቤት እንደነበሩ እና እየተፈራሩቁ በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል በደል እንዳደረሱባቸው ይናገራሉ።

ዛሬም በሳቸውና በጓደኛቸው ላይ የተፈጸመው በደል ያንገበግባቸዋል። እሳቸው በህይወት ተርፈው ጓደኛቸውን የነጠቃቸውን ግፍም በሲቃ ተሞልተው ይናገራሉ። ጓደኛየ በደሉ ከደረሰባት በኋላ “ከዚህ በኋላ የልጄን አይን የማይበት ዐይን የለኝም’ ብላ ራሷን አጠፋች” ሲሉ ተናግረዋል።

እርሳቸውም በታጣቂዎቸ የተደፈሩት በቡድን መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ አለምሸት፤ ከሞራል ስብራቱና በደሉ ባሻገር አከላዊ ህመም እየተሰማቸው እንደሆነ ለኢፕድ ገልጸዋል።

የራስ ጸጉራቸውን በመንጨት ብዙ እንግልት በማድረስ ሁለቱን አዛውንት አየተፈራረቁ ድርጊቱን እንደፈጸሙባቸው ወይዘሮዋ የነገሩን ሀዘንና ሲቃ በተሞላበት አንደበታቸው ነው።

እነዚህ አረመኔዎች ግፉን ከመፈጸማቸው በፊት “እንጀራ አምጡ” ብለው ጠይቀው በእጃቸው ከበሉ በኋላ እንደሆነና፤  “መግደልም መድፈርም መብታችን ነው” እያሉ በመሳሪያ አስፈርርተው ድርጊቱን እንደፈጸሙ ተጎጂዋ ተናግረዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ንጹሃንን በጅምላ መግደል፣ ህጻናትና አዛውንት ሴቶችን መድፈርና ንብረት ማውደም መፈጸሙን የሰብአዊ መብት ተቋማት ጭምር እየገለጹ ይገኛሉ። (ምንጭ @ESATtvEthiopia

(ፎቶ፤ እንደማሳያ ከኢንተርኔት የተወሰደ)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply