Site icon ETHIO12.COM

ጠበቃ ሳይሆን ነኝ በማለት በርካታ ጉዳዮችን በከፍተኛው ፍርድ ቤት የረታው ኬንያዊ ተያዘ

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ ነኝ በማለት በርካታ ክሶችን ተከራክሮ የረታው ግለሰብ በባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር ዋለ።

ግለሰቡን በተመለከተ የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት “ጠበቃው” ከመታሰሩ በፊት ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ጀምሮ አስከ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ድረስ 26 ጉዳዮችን ይዞ በመከራከር ለመርታት ችሏል።

ግለሰቡ ሊያዝ የቻለው ለኬንያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ተገቢው ትምህርት እና ብቃት ሳይኖረው በማስመሰል በዘርፉ በመሰማራቱ ከተለያዩ ሰዎች ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ነው።

የሕግ ባለሙያዎቹ ማኅበር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው ግለሰቡ፣ ጠበቃ እንዳልሆነ እና በኬንያ ውስጥ በጠበቅና እንዲሠራ የሚያስችለው ፈቃድ የሌለው ነው።

“ግለሰቡ በኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠበቃ እንደሆነ እና የማኅበሩ አባል መሆኑን በመግለጽ ሲያጭበረብር ነበር” ሲል ማኅበሩ ከሷል።

የሕግ ባለሥልጣናት ጨምረውም ግለሰቡ ተገቢው ትምህርት እና ፈቃድ ሳይኖረው ለምን ያህል ጊዜ በጥብቅና እንደሠራ ባይገለጹም በርካታ ጉዳዮችን ለማሸነፍ መብቃቱ ተነግሯል።

ብሪያን ምዌንዳ በሚል ስም የሚታወቀው ይህ ግለሰብ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ውስጥ አሳሳቢ ሆኖ የነበረው “ሙንጊኪ” የተባለው የወንጀል ቡድን መሪን በመወከል በቴሌቪዥን በተለላፈ የፍርድ ሂደት ላይ ተሳትፎ እንደነበር ይነገራል።

ግለሰቡ ሐሰተኛ መሆኑ ከተነገረ በኋላም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይኽው ቪዲዮ በስፋት እየተዘዋወረ ይገኛል።

የኬንያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ግለሰቡ ተመሳሳይ ስም ያለውን ሕጋዊ ጠበቃ ግለ ታሪክ ከማኅበሩ ድረ ገጽ ላይ በመውሰድ እርሱን መስሎ ሲያጭበረብር ቆይቷል ብሏል። BBC


Exit mobile version