ETHIO12.COM

“ከምክክር ውጪ ሌላ መፍትሔ እንደሌለ ሕዝቡ አምኗል… የታጠቁ ሃይሎችን ለማምጣት ጥረት እያደረግን ነው” ኮሚሽነር ሒሩት

ለ14 ዓመት በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ እና ሳህል የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ምክትል ወኪል ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለስድስት ዓመታት የአፍሪካ የሴቶች የሠላምና ልማት ኮሚቴ ከፍተኛ ኦፊሰር፣ ለሦስት ዓመት በኦክስፋም አህጉራዊ የሠላም ግንባታ እና የግጭት አመራር አማካሪ ነበሩ፡፡

ከፈረንሳዩ ሰርቦን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሩቅ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥም በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ነበሩ፡፡ ለሁለት ዓመታት በሕግ እና ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ተንታኝ ባለሙያ ሆነውም ያገለገሉ ሲሆን፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በአፍሪካ ክፍል ሠርተዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት የሕግ ጥናት ኦፊሰር፣ ለሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ሌክቸረር፣ ለስምንት ዓመታት በግል የንግድ ድርጅት ከፍተኛ የሕግ አማካሪ፣ ለአራት ዓመታት ዓለም አቀፍ የንግድ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ልምድ አግኝተዋል፡፡

የዛሬዋ የዘመን እንግዳችን ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ነው። በሕፃናት መዋያ ደረጃ ፊደል ከመቁጠር ጀምረው እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው የጨረሱት ሊሴ ገብረ ማሪያም ትምህርት ቤት ነው፡፡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለሕግ ትምህርት ወደ ፈረንሳይ ያቀኑ ሲሆን፤ በውትድርና ስትራቴጂ እንዲሁም፤ በፖለቲካ ሳይንስ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ከእኚሁ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሒሩት ገብረስላሴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡ መልካም ንባብ፡-

 አዲስ ዘመን፡- ከልጅነት ሕይወትዎ እንጀምር አስተዳደጎት እንዴት ነበር?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- ለቤተሰቦቼ ሶስተኛ ልጅ ነኝ። የተወለድኩት ትምህርትን በሚወድ ቤተሰብ ውስጥ ነው። በዚህ ዕድለኛ ነኝ፤ እናት እና አባቴ ብቻ ሳይሆኑ አያቶቼ በሙሉ ዕውቀትን የሚያከብሩ ናቸው፡፡ በእኛ ቤተሰብ ውስጥ ሰውን የሚያስከብረው መማር ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ አለ።እንደአሁን ቅብጠት የለም፡፡ ሁሉም ነገር ሥርዓት አለው። ለሕይወታችን ቀዳሚው ጉዳይ ትምህርት ነው። እናት እና አባታችን የቤት ሥራችንን በየቀኑ ይከታተላሉ። በተወለድኩበት ቤት ውስጥ ትልቅ ቤተ መፅሐፍ አለ፡፡ እናቴም አባቴም አንባቢ ናቸው፡፡ መፅሐፍ ማንበብ ባህላችን እንዲሆን አድርገዋል፡፡

የመጀመሪያዋ ታላቅ እህቴ የተማረችው የእንግሊዞች ትምህርት ቤት ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ናት፤ ሁለተኛዋ እህቴ ደግሞ የተለየች ምጡቅ አዕምሮ ያላት ነች፡፡ በዛን ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለባለምጡቅ አዕምሮ ተማሪዎች ይሸልሙ ነበር፡፡ ትምህርት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ዘመኗን ያሳለፈችው በሽልማት ነው፡፡ ዶክተር ገነት ገብረስላሴ ትባላለች፡፡ አሁን የማህፀን ስፔሻሊስት ናት፡፡ ለእኔ ከገነት በታች መወለድ በጣም ፈተና ነበረው፡፡ የእኔ ፈተና ከእርሷ በታች መወለድ ብቻ ሳይሆን ሌላው የመጀመሪያው ፈተና ከፈረንጅ ጋር ማውራት ነበር፡፡ ነጮቹን ትምህርት ቤት አገኘኋቸው። እኔም እንደእህቶቼ ማታ የቤት ሥራ ሠርቼ መተኛት ሲኖርብኝ፤ መተኛቴን ትቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ማንበብ በጣም ስለምወድ ብዙ ከማንበቤ ብዛት ይበቃሻል ብለው፤ መብራት ያጠፉብኝ ነበር፡፡

ከትምህርት በኋላ እንጫወት ነበር፡፡ ቴሌቪዥን የመጣው በ12 ዓመቴ ነው፡፡ ቤት ውስጥ ቴሌቪዥን የምናይበት ቀንና ሰዓት የተወሰነ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ፈረንሳይ አቀናሁ። እዛ ሕግ እና የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርቴን ተከታትዬ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ እናት እና አባቴ የሚፈልጉት ደረጃ ላይ ደርሰንላቸዋል፡፡ አባቴ የሞተው ልጆቹ ሁለተኛ ዲግሪ መያዛቸውን አይቶ ተደስቶ ነው፡፡ እናቴ አሁንም ድረስ አለች።

አዲስ ዘመን፡- መጀመሪያ ከፈረንሳይ መጥተው ወደ ሕግ ሥራ ሲገቡ ሁኔታው እንዴት ነበር?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- በጣም ልጅ ነበርኩ፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት የልጅነት ሕይወቴ ትምህርት ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር፡፡ ስለዓለም ብዙ የማላውቃቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በተጨማሪ በዕድሜም ልጅ ነበርኩ። ስለዓለም የማውቀው የተወሰነ ነገር ነው፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፅህፈት ቤት የተወሳሰቡ ጉዳዮች የሚላኩበት ነው፡፡ ፈተና ተፈተንን። በአጋጣሚ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕግ ያረቀቁት ፈረንሳዮች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ አርቃቂዎች አስተማሪዎቼ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ፈተናው አልከበደኝም፡፡

አብዛኛዎቹ ጉዳዮች የነፍስ ወይም በጣም የረቀቁ የማጭበርበር ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ጊዜዎችን ከሠራሁ በኋላ ሥራዬን መለወጥ ፈለግኩ፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካል ሳይንስ ተምሬያለሁ፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመለከትኩኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ውጪ ጉዳይ የተቀጠሩበት ሁኔታ በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ ከአቃቤ ሕግነት ወደ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባልደረባነት እንዴት ተዘዋወሩ?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- አመለከትኩ ብልም መጀመሪያ በፅሁፍ አልጠየቅኩም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሰው ሀብት ቢሮ ገብቼ በቃሌ ቅጠሩኝ የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ‹‹እኛ ገና ሠራተኛ እና ሥራ እያገናኘን ነው፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡ ‹‹ሠራተኛ እና ሥራ እስከ አሁን አልተገናኘም?›› ብዬ ስጠይቅ፤ ‹‹የበፊቱ በቀድሞ ሥርዓት ነው፡፡ አሁን ለእዚህኛው ሥርዓት በሚያመች መልኩ ሥራ እና ሠራተኛን ልናገናኝ ነው›› አሉኝ። ስሜን እና ስልክ ቁጥሬን ሰጥቼ ተመለስኩ፡፡ ብጠብቅም ማንም አልጠራኝም፡፡

የመጀመሪያ ልጄን ድርስ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ሆኜ በድፍረት በድጋሚ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄድኩ። ሚኒስትሩ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ነበሩ፡፡ ቢሯቸው ገብቼ ፀሃፊያቸውን ሚኒስትሩን ማነጋገር እፈልጋለሁ አልኩ፡፡ ስሜን ጠይቃኝ ስነግራት፤ ሚኒስትሩ የሚያውቁኝ መስሏት ገብታ ‹‹ወይዘሮ ሒሩት ልታነጋግሮት ነው።›› አለቻቸው፡፡ እርሷ የሚያውቁኝ መስሏታል፡፡ እርሳቸው ደግሞ የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ ወይም አንድ የተቋሙ ሠራተኛ ላይ ክስ ለመሥርት የመጣሁ መስሏቸው ነበር፡፡

እንድገባ ተፈቅዶ፤ ሚኒስትሩ ‹‹ምን ልርዳዎት?›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ዐቃቤ ሕግ መሆኔን እና ፖለቲካል ሳይንስ መማሬን፤ በተቋሙም መሥራት እንደምፈልግ ገለፅኩላቸው፡፡ የትምህርት ማስረጃዬን እና የሥራ ልምዴን አዩት፡፡ ወዲያው 45 ደቂቃ የፈጀ ቃለመጠይቅ አደረጉልኝ፡፡ ሕገመንግሥት፣ ጂኦ ፖለቲክስ፣ ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ብዙ ጉዳዮች ላይ እርሳቸውም ሳያስቡት እኔም ሳላውቅ በዛው ቃለመጠይቁ ተካሔደ፡፡ ላቀረቡልኝ ጥያቄ በሙሉ ምላሽ ሰጠሁ፡፡ ከዛ በኋላ ‹‹በዝውውር እወስድሻሁ›› አሉ፡፡ በጣም ተደሰትኩ። በመጨረሻ ‹‹ሌላ ጊዜ ሰው ሥራ ሲያመለክት እርጉዝ ሆኖ አያመለክትም›› አሉኝ፡፡ አራስ ቤት ሆኜ ወደ ውጭ ጉዳይ መዘዋዋሬ ተነገረኝ፡፡ ሚኒስትሩ በጣም ጥሩ ሰው ነበሩ። አለቆቼ እስኪገረሙ ድረስ ትልልቅ ሥራዎች በሚኒስትሩ ትዕዛዝ እሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳልቆይ ለእስር ተዳረግኩኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡-እንዴት እና ለምን ታሠሩ፤ እስኪ ያስታውሱና ያጫውቱን?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- እንደሚታወቅ ጊዜው የደርግ ዘመን ነበር። ውጭ ጉዳይ ተቀጥሬ ብዙም ሳልቆይ አፍሪካ ክፍል ውስጥ እየሠራሁ መዋቅር ተከለሰ፡፡ እኔ ጄኔቫ ተመደብኩ። አንዲት ሴት ያንን ቦታ ትፈልገው ነበር፡፡ ስለዚህ ‹‹የህቡዕ ድርጅት አባል ትመስለኛለች፤ የግራ ሰው ናት›› ብላ ጠቆመችብኝ፡፡ በሴትየዋ እጅግ አዝኜያለሁ። ምክንያቱም በዛ ጊዜ የምሞትበት አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡ በሰዓቱ የስድስት ወር እና የሁለት ዓመት ልጆች ነበረኝ፡፡ በሕይወት ዘመኔ እንደዛ ዓይነት አስቀያሚ ጊዜ አላሳለፍኩም፡፡

በእርግጥ በወቅቱ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነ ሰው ወዲያው በመኢሶን ይጠረጠር ነበር፡፡ እኔም ትልቅ ወንጀል ሳልፈፅም፤ ‹‹አስተሳሰብሽ ከደርግ ጋር ይቃረናል፡፡›› በሚል ለእስር ተዳረግኩ። የደርግ መንግሥት የእኔ እና እኔ የተጠረጠርኩበት ቡድን (የመኢሶን) አስተሳሰብ ስላልጣመው ግማሾቹን ገደለ፤ ግማሹን ሲያስር እኔ እድለኛ ሆኜ አልሞትኩም፤ ታሳሪ ሆንኩ። አምስት ዓመት ታሠርኩ።በአጠቃላይ ድርጅቱም በደርግ ጠፋ።

እስር ቤት ሆነን ፍርድ ቤት መቅረብ የሚታሰብ አልነበረም። በየቀኑ እገደላለሁ ብሎ መሳቀቅ የተለመደ ነው። ያ ጊዜ ዘመኔን ሁሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንዳልገባ አድርጎኛል፡፡ አውዱ ሰው በቀላሉ የሚሞትበት ነበር፡፡ ሌላ ሀገር ሰው ይታሠራል እንጂ አይሞትም፡፡ ልጆች ያለው ሰው እስር ቤት መግባት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ሊሞት የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን እያሰበ አምስት ዓመታትን ማሳለፍ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ከእስር ቤት ስወጣም ምንም ዓይነት ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍም ሆነ የመንግሥት ተቋም ውስጥ መግባት አልፈልግም ብዬ ወሰንኩ፡፡

የተወሰነ ጊዜ የጥብቅና ፍቃድ በማውጣት ሠራሁ፡፡ ፍርድ ቤት ያለው ሁኔታ ክብርን የሚነካ እና ጨዋነት የጎደለው ሆኖ ታየኝ፡፡ ከሌላ ሀገር በተለየ መልኩ ብዙ ልምድ ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች ጠበቆች ናቸው፡፡ ጀማሪ የሕግ ባለሙያዎች ዳኛ መሆናቸውን ስመለከት ጥብቅናውንም ጠላሁት፡፡ ስለዚህ ሕጋዊ አማካሪ ሆኜ ለተወሰነ ጊዜ ሠራሁ፡፡

በኋላ ግን ወደ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለመቀጠር ወሰንኩ። በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች ጋር ኦክስፋም፣ አህጉራዊ የሠላም ግንባታ እና የግጭት አመራር አማካሪ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ህብረት ያቋቋሙት የአፍሪካ የሴቶች የሠላምና ልማት ኮሚቴ ከፍተኛ ኦፊሰር ሆኜም እሠራ ነበር፡፡ ከዛ እንደገና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥራ የማግኘት ዕድሉን አገኘሁ፡፡ በዛ ጊዜ ጦርነት ውስጥ ወደ ነበረችው በጊዜው ማንም ወደማይመርጣት ኮንጎ ሔድኩኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ውጭ ጉዳይ፤ ከዛ ደግሞ እስር ቤት በድጋሚ ወጥተው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው እንዴት መሥራት ቻሉ?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- ከእስር ከወጣሁ በኋላ መጀመሪያ የሕግ ልምምድ ለማድረግ አሰብኩ፡፡ ነገር ግን ከእስር ስፈታ የሥራ ማመልከቻ እንኳ እንዴት እንደሚፃፍ ጠፍቶብኝ ነበር። ባለቤቴ የሥራ ማመልከቻ ፃፈልኝ፡፡ ባለቤቴ በጣም መልካም ሰው ነበር፡፡ እስር ቤት ሆኜ ልጆቼን በአግባቡ ተንከባክቦ ያሳደገልኝ እርሱ ነው። በብዙ መልኩ ይደግፈኝ ነበር፡፡ ባለቤቴ ከትምህርት ቤት ጀምሮ አብሮኝ የሆነ ሰው ነው፡፡ ተጋብተን ሶስት ልጆች አፍርተናል፡፡ ሁሉም ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው፤ እርሱ ካረፈ ሶስት ዓመት ሆነው። ጓደኞቼ ‹‹እስር ቤት ስታስተምሪ ስለነበር ሥራሽን በማስተማር ብትጀምሪ ይሻላል።›› አሉኝ። እዚህ ሀገር ከእስር ቤት በኋላ ማገገሚያ የለም። ለተወሰነ ጊዜ አካባቢ ዩኒቨርሲቲ አስተማርኩኝ፡፡ ከዛ የሕግ ልምምዴን አጠናከርኩ፡፡

የተማርኩት ሰርቦን በተሰኘው በተከበረው ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ እዛ የተማረች በዛ ዘመን የምታስታወሰኝ አንዲት ሴት ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡ አስታውስሻለሁ አለችኝ። እኔ አላስታወስኳትም ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ስብሰባ ሲኖር እንደአማካሪ ጉዳዮችን የማቅረብ ሥራ ሥሪ አለችኝ፡፡ ከዛን ቀን ጀምሮ ስለተባበሩት መንግሥታት የመቀጠር ጉዳይ አሰብኩ፡፡ ማመልከቻ ላኩኝ፡፡ በኦክስፋም ውስጥ የአስራ አንድ አገሮች አማካሪ እንድሆን ተጠራሁ። የሥራ ባልደረቦቼ ዓለም አቀፍ ሆኑ፡፡ ድርጅቱ የእንግሊዝ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ሲሆን፤ ቢያንስ ሀገሬ አባል ናት ብዬ ገባሁ። ስገባ የማንንም ርዳታ አላገኘሁም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ ሴቶች የሠላም እና ልማት ኮሚቴ ከፍተኛ ሃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ የገቡት ሴቶችን ለመደገፍ አስበውበት ነው ወይስ በአጋጣሚ ነው?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ሕብረት በዚህ ላይ መሥራት አለብን ብለው ድርጅቱን አቋቋሙ። እዛ ላይ ትልልቅ ታሪክ የሠሩ ሴቶችን እንደኮሚቴ አቋቋሟቸው፤ ለእነርሱ ቦርድ ሆኖ የሚሠራ ዋና ቢሮ ማቋቋም ነበረባቸው፡፡ ስለዚህ ቢሮውን ሲያቋቋሙ የሥራ ልምዴን አይተው እኔን ወሰዱኝ፡፡ አፍሪካ ላይ ብዙ ግጭት አለ። እንደሚታወቀው ከጦርነት በኋላ በሚካሔዱ ድርድሮች ለሴቶች ቦታ አይሠጥም፡፡ እነዛው መዋጋትን የሚፈልጉ ሰዎች ይሠበሰባሉ፤ ነገር ግን ሴቶች የሚጫወቱት ሚና በጣም ውስን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ድርጅት የሴቶችን ሚና ለማጉላት የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

የሴቶች አሠራር እና አመራር ከወንዶች ጋር አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ሴቶቹን ማካተት ግጭቶችን ያረግባል ተብሎ ስለታመነ ድርጅቱ ተቋቋመ፡፡ የዛ ቢሮ ሃላፊ ስሆን፤ ፕሮግራሙ በሙሉ የሚመራው እና ምን እንደሚሠራ የሚለየው በእኔ ነው። እነዚህ ትልልቅ ልምድ ያላቸው በዕድሜም የሚበልጡኝ ሴቶች በሥሬ ተደርገው ሠራን፡፡

ማኖሪቨር በሚባል ፕሮግራም ምዕራብ አፍሪካ አካባቢ ላይቤሪያ፣ ጊኒ፣ ሴራሊዮን ላይ ለነበሩ ግጭቶች በሚካሔዱ የሰላም ውይይቶች የሴቶች ተሳትፎ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አደረግን። ሶማሊያ ውስጥም የሚሰበሰቡት የጎሳ መሪዎች ናቸው። እነርሱ ተሰብስበው ውጤት አይመጣም፡፡ መጨረሻ ላይ ሰባተኛ ጎሳ፤ ሴቶች ይሁኑ ብለን ሃሳብ አቀረብን። ከሁሉም ጎሳ የተሰበሰቡ ሴቶችን አደረግን፤ ያንን ማድረጋችን በጣም ጠቀመን፡፡ ቡሩንዲ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ በዚህ መልኩ የሴቶችን ተሳትፎ ለማምጣት ጥረት አደረግን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደ ኮንጎም ሆነ ወደ ሌላ ሀገር ለሥራ ሲሔዱ ቤተሰብ ይዘው ነው? የተለያየ ሀገር እየሄዱ ልጆች ማሳደግ እንዴት ይቻላል?

ኮሚሽነር ሒሩት፡– ኮንጎ የሄድኩት ልጆቼን ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ ከላኳቸው በኋላ ነው፡፡ ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ የወለድኩት ልጅ ከፍ ብሏል፤ ከአባቱ ጋር መኖር ይችል ነበር። ሥራው በጣም ከባድ በመሆኑ ለስድስት ሳምንት እየሠራሁ፤ ለሁለት ሳምንት ረፍት ወደ ኢትዮጵያ እመጣለሁ።ለሰባት ዓመት ኮንጎ ሰርቻለሁ፡፡ እነዛ ዓመታት ከባድ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ኮንጎ መንግሥት የፈረሰባት ሀገር ናት። በተጨማሪ እኔ የተመደብኩት ዋናው ጦርነት የሚካሔድበት ቦታ ላይ ነበር፡፡

የኮንጎ ሰሜን አካባቢ በመሆኑ፤ የተባበሩት መንግሥታት (ዩኤን) እዛ የሚሠራው እንደመንግሥት ሆኖ ነበር፡፡ መንግሥት በመፈራረሱ የመንግሥት ተቋማት በአብዛኛው ፈርሰው ነበር፤ ውስኖቹም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት አይወጡም ነበር፡፡ ስለዚህ ለሲቪሉ ማህበረሰብ ጥበቃ እናደርግ ነበር፡፡ በመጠኑ እየሠሩ ለነበሩ ተቋማት ድጋፍ እየሠጠን እንደመንግሥት እንዲሠሩ እንሞክር ነበር፡፡ እኛ ደግሞ እንደአንድ የዩኤን ድርጅት በየቀኑ የመንግሥት ሥራ በሚጎድልበት አካባቢ በሙሉ አሟልተን እንሠራ ነበር። የእዛ ሃላፊ ነበርኩ፡፡ ከተለያየ ዓለማት የመጡ የሥራ ባልደረቦች ነበሩኝ፡፡ ከተለያየ ዓለም ከመጡ ሰዎች ጋር ሥራ ሲሠራ አመለካከትን በጣም ያሰፋል፡፡ ስለሰው፣ ስለባህል እና ስለቋንቋ ያለንን ዕውቀት እና አተያያችንን ይቀይራል፡፡

በጠረጴዛ ዙሪያ ሰላሳ እና አርባ ሰው ሆነን ተሰብስበን እንወያያለን፤ እንሠራለን፡፡ ከምዕራባውያን ብቻ ሳይሆን ከደቡብ ድሃ ከሚባሉ ሀገሮችም የተውጣጡ ሠራተኞች ነበሩን። ወታደሮቻችን ከተለያዩ ሀገሮች የተውጣጡ ሲሆኑ፤ ትልቁ ተጠባባቂ (ኮንቲንጀንቱ) ከህንድ ነው፡፡ ሁለተኛ ፓኪስታን ሶስተኛው ደግሞ ዑርጋ የሚባል ፓኪስታናዊ ነው።

ፖሊሶቻችን ሴኔጋሎች ሲሆኑ፤ በህብረት በጣም ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠርተናል፡፡ ነገር ግን የዓለም ችግሮች በተናጥል ስለማይፈቱ እና በዓለም ላይ ያሉት ችግሮች የተያያዙ በመሆናቸው ጂኦ ፖለቲክሱ እና ሌሎችም ብዙ ችግሮች በመኖራቸው ጊዜያዊ መፍትሔ እንሰጥና ችግሩ እንደገና ያመረቅዛል፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ የሃይል አሰላለፉ ስላልተለወጠ ነው፡፡

በግጭቱ የሚጠቀሙ ሃይሎች ጦርነቱ እንዲቀጥል ያደርጉታል። ሳህል የሚባል 16 ሀገራት ያሉበት የጂኦግራፊ ቀጣና ውስጥ፤ ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት ሃላፊ ሆኜ ሔድኩኝ፡፡ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮድን ተካሁኝ። የእዛን ጊዜ ስሰጥ የነበረው ምክረ ሃሳብ፤ በዓለም የሃይል አሰላለፍ ምክንያት ተፈፃሚ አልሆነም፡፡ እዛ አካባቢ ሰላም በመስፈኑ ጥቅማቸው የሚነካባቸው ሃይሎች በሁለት ምክንያት ሰላም እንዲሰፍን አያደርጉም፡፡ የዛን ጊዜ የሠጠሁትን ምክረ ሃሳብ ስላልተከተሉ፤ ዛሬ የሚታየው ፈረንሳዮች ይውጡ የሚለው ጉዳይ ተከሰተ፡፡ ይህ እንደሚመጣ በፊትም አውቀው ነበር፡፡ ከዛ ከሳህል ሃላፊነቴ በኋላ በጠቅላላ ለምዕራብ አፍሪካ ምክትል ዋና ሃላፊ ሆንኩኝ፡፡ ደረጃዬ የዋና ፀሃፊ ረዳት ዋና ፀሃፊ ጄኔራል የሚል ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ምዕራብ አፍሪካም ሆነ ሌሎች ሀገሮች ላይ ከግጭር ጋር ተያይዞ ሲሠሩ ትልቁ ፈተና የነበረው ምንድን ነው?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- ብዙ ጊዜ የሚያሳዝነው ያለንበት አህጉር ውስጥ በድህነታችን ምክንያት፤ የሴቶች ጉዳይን እንደመተዳደሪያ የሚያደርጉ ሰዎች መኖራቸው ፈተና ነው። ያ በጣም ያሳዝነኛል። ከሥር የሚነሱ በትክክል በዓላማ የሚሠሩ ገንዘብ ሳያገኙ፤ ከላይ ይህንን መተዳደሪያ ያደረጉ ሰዎች ገቢ መሰብሰቢያ ማድረጋቸው በጣም ያስቀይመኝ ነበር። በአጠቃላይ በአፍሪካ ላይ ብዙ ጊዜ በድህነታችን ምክንያት አስተዋፅኦ እናደርግላችኋለን ይላሉ። ነገር ግን በአብዛኛው ገቢው ለራሳቸው ነው፡፡ ድሃ ሀገር ላይ እንደሚታየው በአብዛኛው መንግሥታዊ ያልሆነ የርዳታ ድርጅት የሚቋቋመው ራስን ለማቋቋም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የድሃ ሀገራት ችግር ሲጠቀስ፤ የራሳችን ክፍተት እንዳለ ሆኖ፤ የተባበሩት መንግሥታትን እንደፈለጉ የሚያዙ ሀገራት ጣልቃ ገብነታቸውን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ የዓለም አቀፍ ተቋሞች መቋቋማቸው፤ የአሸናፊዎችን ጥቅም ተቋማዊ አድርጎታል፡፡ ዓለም ትልቅ እና ብዙ ሀገሮችን የያዘች ናት። ነገር ግን ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት እና ማብራሪያ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አምስት አባል ሀገራት ብቻ ድምፅ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህ በየትኛው አመክንዮ ተቀባይነት የለውም፡፡ አንድ ሀገር ከሌላው ሀገር ይበልጣል ማለት አይቻልም፡፡ የእነርሱ ድምፅ ብቻ ተቀባይነት ማግኘቱ፤ በነፃነት እንደፈለጉ እንዲሆኑ ተመችቷቸዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ድርጅት በተለይ የፀጥታው ምክር ቤት አወቃቀር፤ ቋሚ አባላት ተፈጥረው 5ቱ የተለየ ድምፅ አላቸው። የሶስተኛው ዓለም የሚባሉ አባል ሀገራት፤ በተቋሙ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ውስን ነው፡፡ እንደዕድል በስንት ዓመት አንዴ እንደሎተሪ ከገቡ በኋላም ምንም ሚና የላቸውም፡፡ አሁን ግን ዓለም ላይ ያለው ፖለቲካ ቀስ በቀስ እየተለወጠ ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ ድምፅ እየተሰማ ነው። ያ ተቋም በሚገባው ልክ በፍትሃዊነት ጉዳዮችን የሚያይ አለመሆኑ፤ አሁን ሌሎች የሥልጣን ማማዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸው አንዱ ምልክት ነው፡፡

ብሪክስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ መለወጥ አለባቸው። አብዛኛውን ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት የሚወሰኑ ውሳኔዎች የእነርሱ ፍቃድ እና አቋም እንዲሁም የእነርሱን ጥቅም የሚያስከብር ብቻ ነው፡፡ የእኛ ሚና አጃቢነት ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን የደረስንበት ሁኔታ ዓለም ያንን እየጠየቀ በመሆኑ፤ ሁኔታው መልክ እየያዘ ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡-በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮችም ዞረዋል። በኢትዮጵያ አሁን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት ሰፋፊ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ካልዎት ልምድ አንፃር ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- ኢትዮጵያውያን እንደዕድል የብዙ ሀገራት ጥቅም ያለበት ቦታ ላይ የምንገኝ ነን፡፡ በዚህ ምክንያት ያለምንም ጥርጥር ከውጭ በኩል ያሉት ስውር ጣልቃ ገብነቶች ኢትዮጵያን አሁን ያለችበት ሁኔታ ላይ አድርሰዋታል። ያለፈው የኤርትራ መገንጠልም ሆነ፤ አሁን ያለው ችግር ከውጭ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ አለመሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ በተጨማሪ እንደሚታወቀው ሀገራችን አሁን ያለውን ካርታ የያዘችው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ በሀገር ታሪክ ውስጥ ሌሎች ሀገሮች ምናልባትም ካርታቸው አንድ ምዕተ ዓመትን የያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግማሽ ምዕተ ዓመትም አላስቆጠረም።ያ እንዲጣጣም ሆኖ የብሔራዊነትን ‹ኔሽን ቢውልዲንግ›› በሚገባ መሥራት ሳይችል ሌሎች የውጭ ተፅዕኖዎች ችግር ፈጠሩብን። ይህ ዛሬ የምናውቀው ካርታ አንድ ሺህ ዓመት የፈጀ ። ጊዜ ይፈጃል፡፡

መጀመሪያ ላይ የነበሩ መንግሥታት የጋራ ማንነት መገንባት ላይ ያባከኑት ጊዜ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ እነርሱ የተወሰነ ነገር ቢሠሩም፤ በቅኝ ግዛት ያልተገዙበት ምክንያት ተጨማምሮ የውጭው ተፅዕኖ ተደማምሮ ዛሬ የምናየው ሁኔታ ላይ ደርሰናል። ዋናው ጉዳይ የጋራ ማንነት ነው፡፡ የጋራ ማንነት ሲፈጠር አብሮ ሰላምም ይመጣል። የጋራ ማንነት ሳይኖረን፤ የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ሥራው ሳይሠራ ሁሉም የራሱን ማንነት እና የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ተከፋፍሎ ተነሳ፡፡

የራስን ማንነት ለማስጠበቅ ጥያቄ አታንሱ ማለት አይቻልም። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የብሔር አብዮት ዓይነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁሉም አንድ ቦታ ላይ በእኩል ደረጃ መስተናገድ የሚፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ይህንን ደግሞ በትክክል መወጣት አለብን፡፡ ይህንን ለማድረግ ስንሞክር እንደአንድ ዜጋ የጋራ እኩል የሚያደርጉንን እሴቶች ማጠናከር አለብን፡፡ ሁለቱንም እኩል ማስኬድ አለብን። የጋራም ሆነ የራስ ማንነት ጉዳይ ጎን ለጎን እኩል መሔድ አለባቸው፡፡ የጋራ ላይ ላተኩር በሚል የተናጥል ማንነትን ጥያቄ ማስቆም አይቻልም። ምክንያቱም አመፅ ይከተላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቀይ ባህር ያለን ርቀት ቅርብ መሆኑ፤ ማለትም ከላይ እንደጠቀሱት የኢትዮጵያ አቀማመጥ ያለችበት ቦታ እና የዓባይ መነሻ መሆናችን በረከት ነው መርገምት?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- አፍሪካ ውስጥ ግጭት እና ጦርነት ያለባቸው አካባቢዎች በአብዛኛው ሲታዩ ሀብት ያለባቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ ሀብት የሌለበት ሀገር ብዙ ጦርነት የለም። ሀብት አንዳንዴ መርገምት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። የተገኘው ፀጋ በሌሎች ሲፈለግ የሀብቱ ባለቤት ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ ያንን ያለአግባብ ለመጠቀም ሲባል ሆን ተብሎ በእዛ ሀገር ረብሻ እንዲኖር ይደረጋል።

የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ሀብት መርገምት ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ለእኔ ዓባይ ለኢትዮጵያ በፈጣሪ የተሠጠ ፀጋ እንጂ፤ መርገምት አይደለም፡፡ በዓለም ስኖር የሚገባኝንም ቢሆን ማንም በትሪ ላይ አያቀርብልኝም፡፡ ዓባይን ለመጠቀም እየተዘጋጀን ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ ጥቅማችን ይጎድልብናል ብለው የሚያስቡ አካላት፤ የማያነሱት ነገር አይኖርም፡፡ ግብፆች መብት ይሠጠናል የሚሉት ስምምነት ኢትዮጵያ እንደሀገር ያልተሳተፈችበት ነው፡፡ በገዛ ሀብቷ ለመጠቀም ስትሞክርም ቢሆን፤ ማንም ዝም ብሎ አያይም፡፡ ይህ ራሱ ሌላ የትግል ግንባር ነው፡፡ ችግር እየፈጠሩብን ያሉ ሀገራት እንደቀላል የሚታዩ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ሃያላን የሚደግፏቸው ሀገራት ናቸው፡፡ ነገር ግን እነርሱ ችግር ስለፈጠሩ ሀብታችን መርገምት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች ሀብታቸው መርገምት ከሆነባቸው የአፍሪካ ሀገሮች የእኛ ይለያል፡፡ እኛ አቅማችንን ሰብስበን ያለንን ሀብት ለመጠቀም ዝግጁ ሆነናል፡፡ እነርሱ ግን ገና ሀብታቸውን መጠቀም ሳይችሉ ድምጥማጣቸውን አጥፍተዋቸዋል፡፡

ከባህር በር አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ውስጥ እኔ እንደማምነው ትልቅ ክሕደት ተፈፅሟል፡፡ የባህር በር እንዳይኖረን በሚያደርግ መንገድ የተፈፀመው ስምምነት ከክህደት የሚያንስ አይደለም፡፡ ያንን የፈፀሙ ሃይሎች ለምን ያንን እንዳደረጉ እነርሱ እና ፈጣሪ ይወቀው፡፡ በዓለም ላይ ይህን ያህል ሕዝብ ያለው ቁጥር የባህር በር የሌለው የለም። እኔ የነበርኩበት ኮንጎ እንኳ በዜጎቻቸው ብቻ ሳይሆን በቅኝ ገዢዎች ሳይቀር በጣም በከፍተኛ ድርድር ቀጭን የባህር በር እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ እኛ በገዛ ፈቃዳችን የገባንበት ሁኔታ ግራ ያጋባል፡፡ ያ ታሪካችን ሆነ፡፡ ያንን በምን መልክ እንወጣው ከተባለ የተለያዩ ሰላማዊ መንገዶችን ፈልጎ መቀጠል የተሻለ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሕጎች በሚፈቅዱት መልኩ በሰላማዊ መንገድ መታገል እና በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይሻላል። ከዛ ውጪ ሌላ መንገድ የለውም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እየሠሩ ወዳሉበት ኮሚሽን እንመለስ፤ ከተቋቋመ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ሆነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ምን ያህል ሰፊ ነው? እናንተስ ምን ያህል እየሠራችሁ ነው?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- መጀመሪያ ማንም ሊረዳው የሚገባው ሥራው በጣም ከባድ ነው፤ ሀገሩ ሰፊ ነው፡፡ ሕዝቡ በጣም ብዝሃነት ያለው ነው፡፡ ብዙ የተተከሉ ግጭቶች አሉ፡፡ ያለው አውድ ይህ ነው፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ የምንሞክረው ለይምሰል ላይ ላዩን አይደለም፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ለዚህ ጉዳይ ሃላፊነት ሲሰጠን በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡ ከፍተኛ ተጠያቂነት ያለበት ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ሥራችንን በአግባቡ መሥራት አለብን ብለን ሌሎች ሀገሮች ላይ እንደእዚህ ዓይነት ብሔራዊ ምክክሮች የተካሔደባቸው እና ያልተሳኩባቸውን ቦታዎች በማጥናት ምን ሲደረግ የሚሳካልን መሆኑን አጥንተን በዛ መልክ ለመሥራት ወስነን ተንቀሳቅሰናል።

ይህ አካሔዳችን በጣም አድካሚ መሆኑን እናውቃለን። ነገር ግን ይህንን ሥትሠሩ ይህንን አጉድላችሁ ነበር እንዳንባል እንፈልጋለን፡፡ ትልቁ ነገር እንዲህ ዓይነት ሂደት ምንም ዓይነት ምክክር በሌለበት ሀገር ላይ ሲሠራ ዋናው ጉዳይ በትክክለኛው መንገድ ማስጀመር ነው። ለዚህም ከሁሉ በፊት ባለድርሻ አካላት ይህንን ምክክር እንዴት ታዩታላችሁ? በምን መልክ ቢካሔድ የሚበጅ ይመስላችኋል? የተለያዩ ክልሎች ስላሉ በእናንተ አውድ ምን ይመስላችኋል? እያልን አንድ ዓመት የፈጀ የማማከር ሥራ ሠርተናል፡፡ ያንን ካደረግን በኋላ ከየቦታው ያገኘነውን መረጃ ይዘን የብሔራዊ ምክክር መንገዱን አካሔድ ነድፈናል፡፡

በተጨማሪ መልሰን በሀገር ደረጃ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ያሰብነውን አስረድተናል፡፡ ከእነርሱም ግብዓት ወስደን አካታች እንዲሆን ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ አካታች ወይም አሳታፊ ማለት ባዶ ቃል ሳይሆን በእርግጥም ሕዝቡን በማሳተፍ፤ አካታች ሲባልም ማንም ሳይተው በየወረዳው እየሔድን እየሠራን ነው፡፡ አሁን የደረስነው ተሳታፊን እየለየን ሲሆን፤ ሕዝቡ አጀንዳዬ ይሔ ነው ብሎ እንዲነግረን እያደረግን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በምክክሩ እርሶ ተስፋ የሚያደርጉት ምንድን ነው? በእርግጥ የኢትዮጵያ ችግር በእናንተ ብቻ ይቀረፋል?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- እዚህች ሀገር ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ከተለያየ ብሔረሰብ የተውጣጡ ሰዎች መንግሥትን ጨምሮ ተሰብስበው ቁጭ ብለው እንደሀገር ለመቀጠል የምንስማማባቸው እና የምንፈልጋቸው ነገሮች ምን ይሁኑ? ብለው ተነጋግረው አያውቁም፡፡ እንደማህበረሰብ እና እንደፖለቲካ መሪዎች ይህ ንግግር ተደርጎ አያውቅም። ጥግ ይዞ መጯጯህ ነው። አንድ ቤተሰብ አንድ ጉዳይ ላይ ለመወሰን አባት፣ እናት እና ልጅ ተሰብስበው እንደቤተሰብ ይመክራሉ፡፡ ልክ እንደአንድ ቤተሰብ በመምከር ቢያንስ በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት አለብን የሚል ንግግር አልተደረገም፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሔደው ሀገራዊ ምክክር አዲስ የፖለቲካ ጅማሮን መፍጠሪያ አጋጣሚ ይሆናል፡፡ አብሮ አንድ ሀገር ውስጥ ለመኖር የዛ ሀገር መሠረታዊ ሕጎች ላይ መስማማት አለብን። ይህ እስከ አሁን አልተደረገም፡፡ ይህ ሀገራዊ ምክክር በመሠረታዊነት ሊያስተዳድሩን የሚገቡ ሕጎች እና እሴቶች ላይ ቁጭ ብለን እንደ አንድ ሀገር አባል ለመጀመሪያ ጊዜ የምንነጋገርበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ፈጣሪ ከረዳን ምክክሩ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደአንድ ሀገር በጋራ የምናስበው ይሔንን ነው ብለን የምናስቀምጥበት ወቅት ይሆናል፡፡

ከየወረዳው እያስወከልን መጥተናል፡፡ ከዛ በኋላ ጉባዔው ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ እነዛን ውሳኔዎች መንግሥት ያስፈፅማል፡፡ መግባባት የሚያቅተን ጉዳይ ላይ ደግሞ ወይም በሪፈረንደም ወይም በሌላ በሚወሰን አማራጭ ሊፈታ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ሁለት ነገር አለ፡፡ አንደኛ ቁጭ ብሎ መመካከር አስፈላጊ መሆኑን ማመን እና መቀበል ነው፡፡ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የእኔን ድምፅ ማጉላት ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ድምፅ ማዳመጥ እንደሚገባ ማወቅ፤ በዚህ ላይ ንግግር ለማድረግ መስማማት ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛ ደግሞ በጣም በተወሰኑ ነገሮች ላይ መስማማት ከተገኘ በእኔ በኩል ሙከራችን ጥረታችን ውጤት አግኝቷል ብዬ አምናለሁ። ከላይ እንዳልኩት ምክክሩ አዲስ የመመካከር እና የመነጋገር ባህል ነው፡፡ ሁሉም ሰው በየጥጉ መጮህ ሳይሆን የመመካከር እና የመነጋገር ባህል ከተመሠረተ ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይሔ ከእዚህ ኮሚሽን ሕይወት ጋር አይገናኝም። ይሔ ኮሚሽን ሃላፊነቱ የመጀመሪያውን የምክክር ምእራፍ ማስፈፀም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ፈቃደኝነቱን ኮሚሽኑን በማቋቋም ጀምሯል፡፡ ከወረዳ ጀምሮ ከሥር ስትሠሩ በሕዝቡ በኩል የምታዩት ችግር ምን ነበር? ሕዝቡም ሆነ መንግሥት አካባቢ ያያችሁት ምንድን ነው?

ኮሚሽነር ሒሩት፡- አንድ ትልቅ የሚያስጨንቀን ነገር ሕዝብ በዚህ ሒደት ላይ የጣለው እምነት እና ጉጉት ነው።ከምክክር ውጪ ሌላ መፍትሔ እንደሌለ ሕዝቡ አምኗል፡፡ አሁን ፈተናው የተለያዩ ማህበረሰቦች አሉ፡፡ በአንዳንድ ክልሎች የትጥቅ ትግል ውስጥ የገቡ አሉ፡፡ ሕዝቡ በምክክሩ ያምናል፡፡ እነዚህ የታጠቁ ተዋናኞችን ማምጣት ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ያለነው እነርሱን ለማምጣት ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሮች የሚፈቱት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተማከረበት ሲሆን ነው፡፡ ተስፋ የምናደርገው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይሳተፋል ብለን ነው፡፡ ፈተናውም እዛ ላይ ነው፡፡

በመንግሥት በኩል የጠየቅነውን ድጋፍ አጥተን አናውቅም፡፡ የእኛ ፈተና በሒደቱ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ቡድኖችን ወደ ምክክሩ ማምጣት ነው፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ችግር እየፈጠረ የመጣው የሐሰተኛ መረጃ እና የውሸት ዜና ጉዳይ ነው። የተቸገረች ሀገር ላይ ተጨማሪ የሃሰት ወሬ በመንዛት ነገሮችን የሚያወሳስቡብን ሚዲያዎች አሉ፡፡ ይህ ሌላው ፈተናችን ነው፡፡ በተለይ የትምህርት ዕድል አግኝቶ፤ የተማረው የሕብረተሰብ ክፍል በአንድ ጉዳይ ላይ አቋም ከመያዙ በፊት ትክክለኛ መረጃ መሆኑን የማጣራት ሃላፊነት እንዳለበት መረዳት ያስፈልጋል። ዛሬ ይህ ብዙ አይታይም፤ የተገኘውን እያዳመጡ ያንኑ ማራገብ ተይዟል፡፡ ነገር ግን እዚህች ሀገር ላይ ተምሮ፣ አንብቦ መረዳት የሚችል ሁሉ፤ የሚሰማውን ነገር በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ ያዋጣናል። በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ስሜታዊ አስተሳሰብን ማራገብ ያሉትን ችግሮች የበለጠ የሚያወሳስብ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊ የሆነ በሙሉ በደንብ ሊገባው የሚገባው፤ አሁን ለጊዜው ፊታችን ለተከመሩት ችግሮች ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ነው፡፡ ይህ አማራጭ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ተረድቶ እንዲሳካ ማገዝ አለበት፡፡ እንዳይሳካ ማድረግ የኢትዮጵያን ፍላጎት የሚያሳካ አካሔድ አይደለም፡፡ እኔ ከተመለከትኳቸው ሀገራት ውስጥ ብዙዎቹ የፈራረሱት እኛ ሀገር ላይ ካለው ችግር አንድ አስረኛ በማይሆን ምክንያት ነው። እኛ ብዙ እጥፍ ችግሮች ኖረውብን ቢያንስ አልፈራረስንም፡፡ ሌላው እኛ ጋር ካለው ችግር በጣም ባነሰ ምክንያት ሲፈርስ አይተናል፡፡ የፈጣሪም ድጋፍ ታክሎበት እስከ አሁን መቀጠል ችለናል፡፡ ወደ ፊትም እኛ ምንም አይነት ጥረት ብናደርግ ችግሮቹ እጅግ የተወሳሰቡ በመሆናቸው የፈጣሪን ርዳታ እየተማፀንን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት ማንኛው ንም መልዕክት ካልዎት ያስተላልፉ፡፡

ኮሚሽነር ሒሩት፡- ሀገር አለመሆን መሠባበር ነው። ሀገር ሆነን እንድንቀጥል ሲባል ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በግጭት ምክንያት የፈራረሱ ሀገሮችን እናውቃለን፡፡ የእነርሱ ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስብን እንደዜጋ፣ እንደቤተሰብ አባል፣ እንደቤተሰብ መሪ ሁላችንም ይህችን ሀገር ለማዳን ጥረት ማድረግ አለብን። ይህ ባዶ ቃል አይደለም፡፡ በጎ ማሰብ፤ አፍራሽ ሳይሆን ገንቢ መሆን፤ ሁሉም በትክክል በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለበት፡፡ ይህን ስል ዝም ብዬ አይደለም። አንዳንድ ጥላቻን የሚያመጡ እና የሚያዳብሩ ነገሮችን ከራስ ጀምሮ ማስወገድ ይገባል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ እየጎዳን ያለው ከሰው አፍ የሚወጣው ቃል ነው፡፡ ከሰው አፍ የሚወጣ ቃል ይጎዳል፤ ይበትናል፤ ያጠላላል፡፡ ስለዚህ በንግግራችንም ሆነ በአካሔዳችን በምንሠራው እና በእያንዳንዱ ርምጃችን በጥንቃቄ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ይህ ከእጃችን እንዳይወጣ ማድረግ አለብን፡፡ ብዙ የሚፈለግ ነገር የለም። በጣም እንድንጠላላ የሚሠራውን ሥራ ማስቀረት አለብን፡፡ አላስፈላጊ በሆነ መልኩ ሥራዬ ብለው እንደማህበረሰብ እንድንጠላላ የሚሞክሩ ሃይሎች አሉ፡፡ ይህንን ማስቀረት ወይም መጣል ይጠበቅብናል፡፡


Exit mobile version