Site icon ETHIO12.COM

በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ 28 ሰዎች ሲሞቱ ከ300,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል

በሶማሌ ክልል ከ33 ወረዳዎች በላይ ተከሰተ የተባለውን የጎርፍ አደጋ በተመለከተ ተጎጂዎችና ተፈናቃዮች በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ቲክቫህ ኢትዮጵያ በቦታው እርዳታ እያደረገ የሚገኘውን Save the Childrenን ጠይቋል።

የድርጅቱ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አብዲራዛቅ አሕመድ በጎርፉ የተጎዱት ከ600,000 በላይ ሰዎች እንደሚሆኑና ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንና የ28 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል።

” ምግብም፣ መድኃኒት የሚበቃ የላቸውም ችግሩ ከፍተኛ ነው። የተፈናቀሉት ሰዎች እርዳታ ይፈልጋሉ። …ትንሽ ከፍ የሚል ቦታ  ከውሃ ትንሽ ወጣ ብለው ነው የተቀመጡት። ሰው በእግር ውሃው ውስጥ ሂዶ አህያም ያላቸው ለትራንስፖርት እየተጠቀሙ ከፍ ወዳለ ቦታ እየሄዱ ነው አሁን ከከተማው ብቻ ነው የወጡት እጂ ብዙም ከወንዙ አራቁም ” ነው ያሉት።

ሴቶችና ህፃናት በምን ሁኔታ ይገኛሉ ?

አቶ አብዲራዛቅ በሰጡን ማብራሪያ፥ “እደዚህ አይነት ችግር ሲመጣ መጀመሪያ የሚጎዱት ሴቶችና ልጆች ናቸው። እስካሁን የሞቱት ጠቅላላ 28 ሰዎች ሲሆኑ ከ28ቱ ወደ ስምንት የሚሆኑት ሴቶች ናቸው” ብለዋል።

ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ ምን ይመስላል ?

ዳይሬክተሩ ይህንን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ ” ያለነውን ሪሶርስ ተጠቅመን ከመንግሥትና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሆነን የምንችለውን ድጋፍ እያረግን ነው። ግን ችግሩ በጣም ትልቅ ስለሆነ ለሁሉም ሰው መድረስ የሚያስችለን ሪሶርስ የለም። ከሁሉም አቅጣጫ የተሰበሰበ ገንዘብም ራሱ እስካሁን ሊበቃ አልቻለም ” ብለዋል።

ለተፈናቀሉት ሰዎች ጥሬ ገንዘብ እየሰጠን ነው ያሉት አቶ አብዱራዛቅ፥ እደፍላጎታቸው እዲጠቀሙ 300 ሺሕ ለሚሆኑ አባውራዎች ለእያንዳንዳቸው 7 ሺሕ 700 ብር፣ ለ1 ሺሕ 200 አባውራዎች የእቃ ድጋፍ እንዳደረጉ ጠቅሰዋል። አሁን ላይ በጣም የሚያስፈልጋቸው ምግብ እንዲሁም የሚያድሩበት ቤት እንደሆነም ጠቁመዋል።

የጎርፍ አደጋው እየጨመረነው ወይስ እየቀነሰ ?

ይህ ጥያቄ የቀረበላቸው ዳይሬክተሩ፣ “#የመቀነስ ነገር የለም፣ ዝናቡ እየዘነበ ነው በጣም የወንዙ ውሃ ከፍተኛ እየሆነ ነው። አሁን #ስጋቱ እዳለ ነው የሚቀንስም አይመስልም። ዝናቡም የወንዙ ውኃም አንድ ላይ ተጨምሮ ችግር እየሆነ ነው መንገዶች ሁሉም ተዘጋግተዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ድጋፉን ለማድረስ በጣም ፈተና የሆነው ጉዳይ ምንድን ነው ?

” ፈታኝ የሆነው ነገር መቀሳቀስ አልቻልንም። ሁሉም ቦታ ውሃ ነው። ልጆቹ [ድጋፍ ሰጪዎቹ] በብዛት በጋሪ ነው የሚንቀሳቀሱት። ሕዝቡም እደዛ ነው የሚንቀሳቀሰው። ሰው የሚበላ አዞም ይኖራል፤ይፈራሉ። በመኪና መሄድ አይቻልም። ውኃው በጣም እየጨመረ ነው። በጣም አስቸጋሪ ነው አይደርስም ያልንበት ቦታ ጎርፉ እየደረሰ ነው ” ሲሉ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል።

አክለውም፥ ” ብዙ ሰውም በዚህ ምክንያት እየተፈናቀለ ነው። እደዚህ አይነት ጎርፍ አይተን አናውቅም። ህዝቡ ራሱ እደዚህ አይነት ጎርፍ አላየንም የሚል ነገር ነው ያለው። በሜትሮሎጅ መረጃ መሠረት ጎርፍ እንደሚኖር ለህዝቡ መነገር ነበረበት። በሚያስፈልገው ልክ አልተሰራም መሰለኝ። ለወደፊትም ከተማው በወንዙ በኩል ሳይሆን በሌላኛዉ በከፍታው በኩል ቢያድግ ጥሩ ነው” ሲሉ አቶ አብዲራዛቅ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስረድተዋል።

በመጨረሻም፣ መንግሥትና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም፣ ጉዳቱ በጣም ከባድ ስለሆነ ድጋፍ ተፈናቃዮችን መዳረስ እንዳልቻለ፣ ርብርብ በማድረግ ሕዝቡን መታደግ እንደሚገባም ጥሪ ቀርባል።

ከ tikvahethiopia የተወሰደ


Exit mobile version