Site icon ETHIO12.COM

የኮሚሽኑ የቀድሞ ሠራተኞች ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የሙስና ክስ ጋር ተያይዞ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሆነ

የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የቀድሞ ሠራተኞች ከ40 ሚሊየን ብር በላይ  የአልባሳት ግዢ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ።

ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ ያደረገው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከሁለት ወር በፊት በአጠቃላይ በስምንት ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ተከሳሾቹም÷ 1ኛ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የቀድሞው ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ፣ 2ኛ የተቋሙ የመንግስት ግዢ ዳይሬክቶሬት የቀድሞው ዳይሬክተር ግሩም ወልዴ፣ 3ኛ የኮሚሽኑ የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት የቀድሞው ባለሙያ ደረጄ ተፈራ፣  4ኛ የኮሚሽኑ የሎጂስቲክስ ምዝገባና ቁጥጥር የቀድሞው ባለሙያ ወንድሜነህ ምስጋናው፣ 5ኛ የአደጋ ስጋት ትግበራ የቀድሞው ቡድን መሪ ኢዮብ ታደሰ ካሳ፣ 6ኛ በኮሚሽኑ የቀድሞ የሕክምና ባለሙያ ሲስተር  አልማዝ ጌቶ፣ 7ኛ በኮሚሽኑ የቀድሞው የአደጋ መረጃ ሀርድ ዌርና ሶፍትዌር ባለሙያ መስፍን ለገሰ  እና 8ኛ  ነጋዴ የሆኑት ንጉስ አማን ናቸው።

1ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ሌሎቹ ግን ቀርበዋል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ባቀረበው የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ላይ እንደተመላከተው÷ በ2014 ዓ.ም ሰኔ ወር ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች የግዢ ጨረታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ  በስውር በመመሳጠር፣ በወቅቱ በተደረገ የገበያ ዳሰሳ ጥናት ቡልዶዘር የተሰኘ የእሳት አደጋ መከላከያ የአልባሳት ዋጋ በፍሬ 46 ሺህ 923 መሆኑ እየታወቀ ተከሳሾቹ ግን አንዱን በ184 ሺህ 644 ብር ከ8ኛ ተከሳሽ ተጫራች ድርጅት ግዢ እንዲፈጸም አፅድቀዋል መባሉ ይታወሳል።

በዚህም በአጠቃላይ 217 ፍሬ አልባሳትን በ40 ሚሊየን 67 ሺህ 748 ብር ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግስት ላይ በልዩነት 29 ሚሊየን 885 ሺህ 441 ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሶ ነበር።

ከ1ኛ እና 8ኛ ውጭ ያሉት ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት ከተነበበላቸው በኋላ የዋስትና መብት ይከበርልን ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበባቸው የከባድ ሙስና ክስ አንቀጹ ዋስትና እንደማያሰጥ ገልጾ ክርክር መደረጉ ይታወቃል፡፡

ክርክሩን የመረመረው ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተከሳሾቹ ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ የክስ ዝርዝሩ እንዲሻሻልላቸው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ በጽሑፍ አቅርበዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግም ክሱ ግልጽ መሆኑን ጠቅሶ ሊሻሻል አይገባውም በማለት በጽሑፍ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ክሱ እንዲሻሻል የቀረበው ጥያቄ የሕግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

በቀጣይ ታኅሳስ 1 እና 2 ቀን 2016 ዓ.ም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቀድሞ ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ እና 8ኛ ተከሳሽ ነጋዴ የሆኑት ንጉስ አማን በተደረገ የጋዜጣ ጥሪ ችሎት ባለመቅረባቸው ምክንያት በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ብይን ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ – FBC

Exit mobile version