Site icon ETHIO12.COM

ሸኔ መከፈሉ ተሰማ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎቹ እጅ እየሰጡ ነው፤ ተማራኪዎቹ ድርጅቱ መፈረካከሱን አስታወቀ

“የህግ የበላይነት ለማስከበር እየተወሰደ ያለዉን እርምጃ መቋቋም የተሳናቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የአሸባሪዉ ሸኔ አባላት ለመንግስት እጅ ሰጡ” ሲል የዘገቡት መገናኛዎች እንዳሉት ድርጅቱ ቁመናው ፈርሷል።

በቅርቡ በታንዛንያ ለስምምነት ብዙ ርቀት ከተኬደና ከንግገሩ መልካም ዜና የተጠበቀ ባለበት ወቅት ስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ መንግስት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በሰላም ንግግሩ የተኩስ ማቆም ስምምነት ተደርሶ እንደነበር፣ አነጋጋሪ የነበረው የስምምነቱ ቴክኒካል አፈጻጸም ጉዳይና ታጣቂዎችን አስመልክቶ እንዴት ይስተናገድ የሚል እንደነበር ውይይቱን የሚከታተሉ አስታውቀው መግለጻችን ይታወሳል።

በሁሉም ረገድ እጅግ ተስፋ ሰጪ ስምምነት ላይ እየተደረሰ ቆይቶ በመጨርሻው ቀን ሙሉ የአቋም ለውጥ በማድረግ ከአመክንዮ ውጭ የሆነ ጥያቄዎችን በማቅረቡ ውይይቱ መጨናገፉ ይፋ ቢሆንም፣ ቀጣይ ንግግር እንደሚኖር ተጠቁሞም ነበር።

በታንዛንያ ንግግሩ እየተደረግ ባለበት ወቅትም ቢሆን ወታደራዊ ኦፕሬሽኑን ያላቋረጠው መንግስት በተለያዩ ቀናት ኦነግ ሸኔ ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደና ታጣቂዎቹ በተለያየ መጠን እጅ መስጠታቸው ሲገለጽ ስንብቷል። ብዙ ባይባልም መሳሪያ መማረኩንም በምስል የሚያሳዩ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር።

ዛሬ ኦቢኤን እንዳለው ከሆነ በሺህ የሚቆጠሩ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እጅ ሰጥተዋል። እጃቸውን የሰጡት መከላከያ የሚያሳርፈውን ድብደባ መቋቋምና መመከት ባለማቻላቸው ነው።

“የተወሰደባቸዉን እርምጃ መቋቋም ተስኗቸዉ የተማረኩት ታጣቂዎች እንደ ተናገሩት ሸኔ ክፉኛ ተመትቶ በመፍረስ ላይ ይገኛል:” ያለው ሚዲያው “የሸኔ ኃይል በዉስጡ በተፈጠረዉ መከፋፈል እርስ በራሱ ወደ መጠፋፋት የተሻገረ በመሆኑ ለመንግስት እጅ ሰጥተናል” ሲሉ ታጣቂዎቹ ተስፋ መቁረጣቸውን አስታውቋል።

“ሸኔ የፍትህና የህዝብ ጥቅም ጠላት በመሆኑ እየፈረሰ ነው” ሲሉ እነዚህ የተማረኩትና በሰላም እጃቸዉን ለመንግስት የሰጡ የሸኔ ታጣቂዎች መናገራቸውን ዘገባው አክሎ ገልጿል። ይህን አስመልክቶ ኦነግ ሸኔ ይህ እስከታተመ ድረስ ማስተባበያ አልሰጠም።

Exit mobile version