Site icon ETHIO12.COM

ከንግድ ባንክ ደነበኞች ሂሳብ ቀንሰው ወደ ሌላ ገለሰብ የጠረተሩ የባንኩ ሰራተኞችና ተባባሪዎቻቸው በሌብነት ተከሰሱ

 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ደንበኞች ሒሳብ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ቀንሰው ለሌላ ግለሰብ በማዘዋወር ወጪ አድርገዋል የተባሉ ስምንት ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል 1ኛ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የእንዶዴ ቅንጫፍ ባንክ ትሬኒ በረከት መኮንን ረዳ፣ 2ኛ በእንዶዴ ቅንጫፍ ሲኒየር ባንኪንግ ኦፊሰር ሁንዳኦል ታደሰ ኡርጌ፣ 3ኛ በእንዶዴ ቅንጫፍ ጁኒየር ኦፊሰር ፋሲካ አዳሙ ለኩ፣ 4ኛ በእንዶዴ ቅንጫፍ ጁኒየር ኦፊሰር በቀለ ከበበ ገዳ እና በእንዶዴ ቅርንጫፍ ባንኪንግ መኮንን አሸናፊ ዘውዴ ማሞ ይገኙበታል። ቀሪዎቹ ማለትም ከ6ኛ እስከ 8ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ደግሞ በግል ስራ የሚተዳደሩ ናቸው ተብሏል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ ብቻ በቀረበው ክስ ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 9/1/ሀ/ እና /2/ ስር የተመለከተውን ተላልፈዋል የሚል ነው።

በዚህም ከ2ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ግብይት ያለአግባብ በማጽደቅ፣ በቀረበ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ሒሳብ መክፈትና ቅድመ ኦዲት ያለአግባብ ማድረግ የሚል የተሳትፎ ደረጃ የተጠቀሰባቸው ሲሆን÷ አንደኛ ተከሳሽን በሚመለከት ግን ከባንኩ መመሪያና አሰራር ውጪ ከሁለት ደንበኞች ሒሳብ ተቀናሽ በማድረግ በ6ኛ እና በ7ኛ ተከሳሾች ሒሳብ የደንበኞችን ገንዘብ ያለአግባብ ማዘዋወር የሚል ክስ ቀርቦበታል።

በአጠቃላይ የባንኩን መመርያና አሰራር በመጣስ የተሰጣቸውን ሥልጣን ወይም ኃላፊነት በግልጽ ተግባር ያለአግባብ በመገልገል ከሌሎች ካልተያዙ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር የባንኩ ደንበኞች ከሆኑት 1ኛ አቶ አብርሃ ገብሬ ከተባሉ ግለሰብ ሒሳብ ላይ በተለያዩ ቀናት 3 ሚሊየን 41 ሺህ 165 ብር እንዲሁም ከሁመራ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት ሒሳብ ደግሞ 2 ሚሊየን 576 ሺህ ብር በመቀነስ በድምሩ 5 ሚሊየን 817 ሺህ 180 ብር ወደ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ያለአግባብ ገቢ በማድረግ በደንበኞቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ መሆኑ ተጠቅሶ÷ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሥልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከስሰዋል፡፡

5ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ ተከሳሹ በባንኩ እንዶዴ ቅርጫፍ ሲሰራ ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ለ7ኛ ተከሳሽ ከተዘዋወረ ገንዘብ ውስጥ ለ4 ግለሰቦች እና በአንድ የግል ድርጅት ስም ወደ ተከፈተ ሒሳብ በተለያየ የገንዘብ መጠን ያዘዋወረና 50 ሺህ ብር በጥሬ ያወጣ መሆኑ ተጠቅሶ÷ የንብረቱን ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን በማሰብ ገንዘቡን በይዞታው ያደረገ፤ የተጠቀመ እና ያስተላለፈ በመሆኑ በወንጀል የተገኘን ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከስሷል፡፡

6ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 11 የተሰጠ የሚል ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በመገልገል መስፍን ተፈራ በሚል ስም የባንክ ሒሳብ የከፈተና መንግስታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት፤ ወደ ሀሰት መለወጥ ወይም በሀሰት በመገልገል ከግል ተበዳይ በአቶ አብርሃ ገብሬ እና ከሁመራ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት ሒሳቦች ተቀንሶ በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ወደ ሒሳቡ የተዘዋወረለትን ገንዘብ በተለያዩ ቀናቶች ወጪ በማድረግ 190 ሺህ 15 ብር ወደ አቶ ጌትነት ውቤ አደራ ወደተባለ ግለሰብ ሒሳብ ያዘዋወረ በመሆኑ ገንዘቡን በይዞታው ያደረገ፤ የተጠቀመ እና ያስተላለፈ በመሆኑ በፈፀመው በወንጀል የተገኘን ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከስሷል፡፡

7ኛ ተከሳሽ በሚመለከት ደግሞ ወደ ሒሳቡ በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት የተዘዋወረለትን ገንዘብ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም የንብረቱን ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን በማሰብ 2 ሚሊየን 300 ሺህ 120 ብር ያለአግባብ ገቢ የተደረገለትን ገንዘብ በሙሉ ለ5ኛ ተከሳሽ ሒሳብ በቁጥር ያዘዋወረ በመሆኑ በፈፀመው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብ ወንጀል ተከስሷል፡፡

8ኛ ተከሳሽ ላይ በተመሳሳይ የሙስና አዋጁ በአንቀጽ 23/ ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የባንኩ ደንበኛ የሆኑት አቶ አብርሃ ገብሩ የተባሉ ግለሰብ ሒሳብ ቁጥር ውስጥ ብር 3 ሚሊየን 241 ሺህ 180 ብር መኖሩን እና ሒሳቡ የማይንቀሳቀስ መሆኑን በማጥናት አቶ አብርሃ ገብሬ የተባሉ ደንበኛን ስም በመጠቀም ወካይ ሆኖ በመቅረብ እራሱ ተወካይ ሆኖ የራሱን ፎቶግራፍ በመጠቀም በደንበኛው ውክልና ሳይሰጥ ውክልናው በደንበኛው የተሰጠ መሆኑን የሚገልጽ ሀሰተኛ ውክልና ማቅረቡ በክሱ ተመላክቷል።

ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው በዚህ መልኩ የቀረበባቸው ክስ በችሎት ከደረሳቸው በኋላ የዋስትና መብታቸውን እንዲከበር ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች የቀረበባቸው የክስ ድንጋጌ ዋስትና እንደማያስፈቅድ ገልጾ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎል።

5ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ድንጋጌ ዋስትና የማያስከለክል ባለመሆኑ የዋስ መብቱ ተጠብቋል።

ፍርድ ቤቱ በችሎቱ የቀረቡ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት የክስ መቃወሚያ እና ያልቀረቡ ቀሪ ተከሳሾችን ለመጠባበቅ ለጥር 8 ቀን 2016ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ ፋና

Exit mobile version