Site icon ETHIO12.COM

ፖሊስ አስለቃሽ ሿሿዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ተሳፋሪ መስለው የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ውስጥ በመግባት የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ስድስት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ እና በህብረተሰቡ ትብብር ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ይገኛል፡፡

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የመሪ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን አማረ ታደሰ እንደገለፁት ተጠርጣሪዎቹ በወረዳ ሁለት ጣፎ መስጊድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ታክሲ ተራ ላይ ተሳፋሪ መስለው ሰልፍ ሲጠብቁ ከቆዩ በኋላ ከአንድ ግለሰብ ኪስ ውስጥ ሞባይል ስልክ ሰርቀው ይሰወራሉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው መረጃ የደረሰው ፖሊስ ክትትል ሲያደርግባቸው እንደቆየ ያስረዱት መርማሪው፤ በድጋሚ ተሳፋሪዎችን እየጫነ በነበረ ሃይገር ባስ ውስጥ ተሳፋሪ መስለው ለመግባት እየተጋፉ ከሌላ ተሳፋሪ ኪስ ውስጥ 12ሺህ 150 ብር ሰርቀው ለማምለጥ ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የታክሲ ሰልፍ ሲጠብቁ ሞባይል ስልክ የተወሰደባቸው ግለሰብ ስልካቸው በእነዚሁ ተጠርጣሪዎች እጅ መገኘቱን የጠቀሱት ዋና ሳጅን አማረ፤ ገንዘብን ጨምሮ ከሃይገር ባሱ ውስጥ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ላይ የተሰረቁ ተጨማሪ አራት ሞባይል ስልኮች እና ሶስት የእጅ ሰዓቶች ተይዘው የምርመራ ስራው መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡

በትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ውስጥም ሆነ ትራንስፖርት ለመጠበቅ በሚኖር ሰልፍ ላይ አልፎ አልፎ የሚያጋጥመውን መገፋፋት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ለወንጀል ተግባር የሚሰማሩ ግለሰቦች ስለሚኖሩ ህብረተሰቡ ትራንስፖርት በሚጠብቅበትም ሆነ ተሳፍሮ በሚጓዝበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ትራንስፖርት መጠበቂያ እና መናኸሪያ ቦታዎች ላይ በመገኘት መሰል ወንጀሎችን ይፈፅሙ እንደነበረ ከህብረተሰቡ የተሰጠው መረጃ ስለሚያስረዳ ንብረታቸው የጠፋባቸውና ተጠርጣሪዎቹን ለይተው ለፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃ መሆን የሚፈልጉ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሪ አካባቢ ፖሊስ በመገኘት መረጃ መስጠት እንደሚችሉ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ምንጭ አዲስ አበባ ፖሊስ

All reactions:

347Dagmawi Tessema and 346 others

Exit mobile version