Site icon ETHIO12.COM

ገነነ መኩሪያ “ሊብሮ” ተሸኘ

በኢትዮጵያ የኳስ አጨዋወት ላይ ለውጥ መደረግ አለበት በሚል የራሱን ተከታዮች ማፍራት የቻለና በዚሁ አሳቡ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለው የስፖርት ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ተሸኘ። የቀብር ስነ ስርዓቱ የተከናወነው በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ነው፡፡

አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ከቅርብ ወራቶች በፊት ከህመሙ ጋር በተያያዘ እግሩን ማጣቱ ቢሰማም ከህመሙ ጋር ትግል እያደረገ ባለበት ሰዓት ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ንጋት ላይ ህይወቱ እንዳለፈ ነበር የተገለጸው።

ገነነ እምነቱን ለማራመድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሳይቀር የትብብር ድጋፍ መጠየቁን የኢትዮ12 አዘጋጅ ያውቃል። ገነነ “ጥለዛ” የሚያዋጣ እንዳልሆነ በማስረጃና በገሃድ በሚታይ ውድቀታችን ማሳየነት ሲከራከር “ሳይንሳዊ አጨዋወት” በሚሉ አካላት በደቦ ተቃውሞ ቢሰነዘረበትም አሳቡ አሸናፊ መሆኑ ዛሬ ምስክር ነው።

ከኢትዮጵያ ተጨዋቾች አካላዊ ቁመናና አስተዳደግ አንጻር የአጭር ቅብብል እንደሚያዋጣ፣ ኳስን አብዝቶ በመቆታጠር ተጋጣሚን ማዛል እንደሚገባ አበክሮ ሲከራከር የነበረው ገነነ አሳቡን አብረው የሚጠምቁለት እንደ አበበ (ካሜራ ማን) የመሳሰሉ የማይታዩ አጋሮች ነበሩት።

በባህሪው ደግ እንደሆነ የሚነገርለት ገነነ ሲያዘጋጀው በነበረው ሊብሮ የስፖርት ጋዜጣ ላይ አሳቡን ለማስረጽ ከሚያደርገው ውጭ በሌሎች ጉዳዮች ሲሳተፍ የሚታይ ሰው አልነበረም።

የቀደሙ የስፖርት ኩነቶችና ታሪኮችን ከሌሎች በላቀ የሚገነዘበውና የሚያውቀው ገነነ አንዳንዴ የሚጽፋቸው ጽሁፎች አንባቢን ያዝናኑ ነበር። ሊብሮ ጋዜጣ በጣም በደቀቀ ጽሁፍ ይታወቅ ስለነበር “መነጽር ግዛልን” በሚል ጋዜጣውን በማጉሊያ መስታዋት ሲያነቡ የሚታዩ ሰዎች ፎቶ ልከውለት እንደነበር የዚህ ሚዲያ አዘጋጅ ያስታውሳል።

“ዶሮን በግልህ ሰፊ ሜዳ ላይ አባረህ ልትይዝ አትችልም” ሲል እምነቱን ለማስረጽ ባቀርበው ምሳሌ የሚታወሰው ገነነ ” ዶሮን ለመያዝ በወደ አንድ ጠርዝ በመግፋት አጥብቦ መንቀሳቀሻዋን በማሳነስ መያዝ ይቻላል። የኢትዮጵያ ኳስም እንዲሁ ነው” ሲል አቅምን ያገናዘበ ኳስ መጫወት ግድ እንደሆነ ለማስረዳት መከራውን ሲያይ የነበረው ገነነ፣ ይህን እምነቱን ለማጉላት ባርሴሎናን ያጣቅስ ነበር። ቡናም ይህንኑ አካሄድ በመከተል ማራኪ ኳስ በማሳየት አግዞታል።
በ1957 ዓ.ም በይርጋለም የተወለደው ጋዜጠኛ ገነነ፤ በኢትዮጵያ በእግር ኳስ ተጫዋችነት፣ በጋዜጠኝነት እና በመጻሕፍት ደራሲነት እንደሚታወቅ ግለ ታሪኩ ያስረዳል።

ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ያሳለፈው ገነነ መኩሪያ፤ኢህአፓ እና ስፖርት፣መኩሪያ እና ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል።

ገነነ መኩሪያ በአሻም ቲቪ ትኩረታቸውን በስፖርት እና በታሪክ ላይ ያደረጉ “የገነነ” እና “ጥቁር እንግዳ” የተሰኙ ፕሮግራሞችን ለዓመታት በአዘጋጅነት እና አቅራቢነት ሲሰራ መቆየቱም ይታወቃል።

ለእግር ኳስ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦም፤ በ2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተሰናዳው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አገልግሎት ሜዳይ ማግኘቱን ግለ ታሪኩን የጠቀሱ ሚዲያዎች አስታውቀዋል።

ኢትዮ12 ለቤተሰቦቹና ወዳጆቹ መጽናናትን ትመኛለች።


Exit mobile version