Site icon ETHIO12.COM

“ዐቢይን ግንባሩን ብለህ ዳዊት ሁን” ያሉት አቡነ ሉቃስ የወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው፤ ተላልፈው ይሰጣሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እንደ ጎልያድ በማስመሰል በአንድ ምሳሌያዊ ዳዊት እንዲግደሉ የሃይማኖታዊ ግድያ ጥሪ ያስተላለፉት አቡን ሉቃስ የወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው። አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 እና 251 ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

ክሱ የቀረበባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ሕገመንግስታዊና በሕገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው። በአቡነ ሉቃስ ላይ ሁለት ክሶችን ያቀረበው የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡

ይህም ተከሳሽ አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 (ሐ) እና አንቀጽ 258(ሀ) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ እንዲሁም የወንጀል ህግ አንቀጽ 251 (ሐ) እና አንቀጽ 258 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚሉ ሁለት ክሶች ናቸው የተመሰረቱባቸው።

በተጨማሪም ተከሳሹ በፀረ ሰላም ሃይሎች የሚፈፀሙ የወንጀል ተግባሮችን ተከትሎ መንግስት ፈፃሚዎቻቸውን ለሕግ ለማቅረብ እና ሕግ ለማስከበር የሚያደርግባቸው ጥረቶችን ለማደናቀፍ እና ህዝብ መንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ማነሳሳታቸው በክሱ ተመላክቷል።

የክስ ዝርዝሩ የደረሰው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ፋና)

አቡን ሉቃስ ይህንን የግድያ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ የኦርቶዶክስ ቤተክስቲያን ጳጳሱን እንድታወግዝ ከተለያዩ አካላት ጥያቄ ቢቅርብላትም ሳትፈጽመው ቀርታለች። ይህም በርካታ በሚባሉ ምዕምናኖቿ ዘንድ ቅሬታን የፈጠረ መሆኑ በስፋት ይነገራል።

በወቅቱ ካለው የፖለቲካ ትኩሳት አኳያ በአደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ባያሰሙም ጥቂት የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች “ጠቅላይ ሚኒስትሩን የምንቃወም ብንሆንም በዚህ ልክ ግን ግድያ እንዲፈጸምባቸው በተለይ ከሃይማኖት አባት መስማታችን አሳፍሮናል” በማለት በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል።

“ጠላትህን ውደድ” የሚለውን የወንጌል ቃል ፍጹም በመጻረር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ግድያ እንዲፈጸም ሃይማኖታዊ ጥሪ ያስተላለፉትን አቡን ሉቃስ ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቡነ አብርሃም ከጥምቀት በዓል በፊት መልስ ሰጥተው ነበር። በአንድ በኩል ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ መታየት ነው ያለበት ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ልናወግዝና መግለጫ ልንሰጥ አስበን ነበር ግን የሚያስከትለውን መጠላለፍ ተመልክተን ትተነዋል ማለታቸው ይታወሳል።

ይህንን የአቡነ አብርሃም ንግግር የሰሙ “እንደ ቅዱሱ ቃል የአቡነ ሉቃስን ንግግር ማውገዝ ተገቢ ነው፤ ግን ካወገዝን ደግሞ ከፋኖ እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር ያጣላናል” በሚል የተረዱት እንዳሉ ብዙዎች ይስማማሉ።

በመጨረጫ በተሰማው መረጃ ተከሳሹ ካህን የፈጸሙት ወንጀል በህግ የሚያስቀጣ በመሆኑ ተላልፈው እንዲሰጡ ክሱን የመሰረተው የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ከሚመላከታቸው ጋር እየሰራ መሆኑ ታውቋል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ   

Exit mobile version