Site icon ETHIO12.COM

“ኦነግ ሸኔ በዝቋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት አባቶችን ገደለ”

ኦነግ ሸኔ በዝቋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት አባቶችን መግደሉን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች። በተደጋጋሚ የሚፈጸመው የዕምነት ተቋማትን ያነጣጠረ ግድያ በአገሪቱ የሃይማኖት ጦርነት ለመቀስቀስ የሚደረገው የመቸረሻው ሙከራ እንደሆነ ተደጋግሞ የሚነገር ነው። ክልሉ እርምጃ ለመውሰድ አግባብ ካላቸው አካላት ጋር ዘመቻ ላይ መሆኑንን አመልክቷል።

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሚገኘው ጥታዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እራሱን ኦነግ ሸኔ ብሎ በሚጠራው ቡድን የገዳሙን መጋቢ ጨምሮ አራት አባቶችን መግደሉን ገዳሙ ጥቅሳ ነው ቤተክርስቲያኒቱ ያስታወቀችው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኢኦተቤ ቴቪን ዋቢ በማድረግ ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት ታጣቂዎቹ ሦስት አባቶችን አግተው ወደ በረሃ ከወሰዱ በኋላ የታገቱትን ለማስለቀቅ ገዳሙ ጥረት በሚያርግበት ወቅት የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተጨማሪ አባቶችን በመያዝ

  1. የገዳሙ መጋቢ አባተክለማርያም ዐሥራት
  2. የገዳሙ ጸሐፊ አባ ኪዳነ ማርያም ጥላሁን
  3. የገዳሙ የመጽሐፍ መምህርና ቀዳሽ አባ ገ/ማርያም አበበ
  4. በአመክሮ የሚኖሩ መናኝ ኃይለማርያም ወልደሰንበት የተባሉት የገዳሙ የሥራ ኃላፊዎች እንደተገደሉና አብረው ከነበሩት አንድ አባት ብቻ ማምለጥ መቻላቸውን እንደተረዱ የገዳሙ ኃላፊዎች ለኢኦተቤ ቴቪ (EOTC TV) ተናግረዋል።፡

የገዳሙ የሥራ ኃላፊዎች ቡድኑ ከዚህ ቀደም ገዳሙን በመዝረፍ ለከፋ ችግር አጋልጦት መቆየቱን አስታውሰው ገዳሜ ጸጥታውን የሚያስከብረበት መሣሪያች በቡድኑ በመወረሳቸው ለከፋ የጸጥታ ችግር መጋለጡን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ገዳማውያን በስጋት ላይ መሆናቸውንና የመንግሥት የጸጥታ አካላትን እገዛ እንደሚሹ አስታውቀው መረጃውንም በየደረጃው ለሚገኙ የሀገረ ስብከቱና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ መግለጫ

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አገልጋይ የሆኑት አራት የገዳሙ አባቶች በአሽባሪዉ ኦነግ ሸኔ መገደላቸዉ ታውቋል፡፡

በነዚህ የሃይማኖት አባቶች ላይ የተፈፀመዉ ግድያ የወረዳዉን ማህበረሰብ ያስደነገጠና በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን ለሰላምና ፀጥታና ለፖሊስ የደረሰዉን ጥቆማ ተከትሎ አሽባሪዉን የማደን እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል::

የወረዳዉ ማህበረሰብም እንደ ከዚህ በፊቱ በየደረጃዉ ከሚገኘዉ የመንግሥት መዋቅር ጋር ሆኖ ይህን አሸባሪ እንድያጋልጥ በድጋሚ እንጠይቃለን::

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመሆን በአሸባሪ ኃይሉ ላይ በሚወሰደዉ እርምጃ የሚገኘዉን ዉጤት ለህዝብ በቀጣይነት የሚያሳዉቅ ይሄዳል::

በሌላ በኩል “የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት መነኮሳትን መግደል ለምን ያስፈልጋል? ዕምነት መርጦ መግደልስ ዓላማው ምንድን ነው? ይህንን ጨካኝ ተግባር ተከትሎ በማህበራዊ ገጾች በቅጽበት የሚሰራጨው የብጥብጥ ጥሪስ ምን ያሳያል?” የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል።

“የገፊና ጎታች ፖለቲካ” አጋፋሪዎች አልመው ድርጊቱን ከሸኔም ሆነ ከተቀጣሪ ነብሰ ገዳዮች ጋር ያስፈጽሙና መልስው “ተነስ ሃይማኖትህ ተደፈረ” የሚል ጥሪ በማቅረብ ህዝብ የዕምነት ጎራ ለይቶ እንዲጫረስ ያመቻቻሉ የሚል መረዳት ያላቸው፣ ድርጊቱ ጥብቅ ምርመራ የሚሻው እንደሆነ ይናገራሉ። አያይዘውም ” መናኩስትን የሚገሉ፣ ለይተው ቤተክርስቲያናትን የሚያቃጥሉ ለምን ይህን ተግባር እንደሚፈጽሙ አይናገሩም። ዓላማቸው ምን እንደሆነና ምን እንደሚፈልጉ ይፋ አለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን ምን ሲደረግላቸው መናኩስትን መግደል እንደሚያቆሙ የሚታውቅ ነገር የለም። እየታወቁና ምስክር እየቀረበባቸው እንደ ሂዝቦላና አልሸባብ ፊት ለፊት ወጥተው ለጥቃቱ ሃላፊነት አለመውሰዳቸው ስጋቱን ያገዝፈዋል። አሁን ላይ ከሁሉም ወገን የሚሰማው አበይት ጉዳይ ይህ ድርጊት እንዴት ያበቃል? የሚለው ነው!!

Exit mobile version