ETHIO12.COM

የኢትዮጵያን መጻዒ ዕድል የሚወስኑ “ሁለቱ የውሃ አካላት”

ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተጋሪ የነበረችና አሁንም ቢሆን በቅርብ ርቀት የምትገኝ ወሳኝ ሀገር ናት፡፡ ለዓባይ ተፋሰስም ቢሆን ከፍተኛውን ድርሻ የምታበረክት ቁልፍ ሀገር ናት፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ከቀይ ባህርና ከዓባይ ፖለቲካ አውጥቶ ማሰብ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ የውሃ አካላት ጋር የተያያዘ ዘላቂ ፍላጎት እንዳላት የሚያሳዩ መረጃዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለመሆኑ ሁለቱ የውሃ አካላት ከሀገሪቷ መጻዒ እድል ጋር ያላቸው ቁርኝት ምን ይመስላል?

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ እንደሚሉት፤ ልብስን ለመስፋት መርፌው ቀድሞ መንገድ ሲመራ ክሩ ደግሞ እየተከተለ እንደሚያጸና ሁሉ የቀደመውን ትውልድ ህልሞች፣ ምኞቶች ፍላጎቶችና ጥያቄዎች መመለስ ይገባል:: የተጀመሩ ውጥኖች መጻዒ እድሎችና ፈተናዎችን ለመሻገር ፋና ወጊ የሆነውን መስመር መከተልም ይገባል:: ይህም የሚገለጸው በዓባይ ወንዝና በቀይ ባህር ላይ ያለው አቋም ነው::

በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ውሃ በተለያዩ መስኮች አስፈላጊ የትኩረት አጀንዳ እየሆነ መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ለኢትዮጵያ የውሃ ሀብትን በስፋት መጠቀም ወሳኝ ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት የታደለች ብትሆንም፤ ሀብቶቿን ተጠቅማ ብልጽግናዋን ከማስጠበቅ አንጻር ብዙ ሥራ ይጠበቅባታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሁለቱ የውሃ አካላት ላይ የሚንጸባረቁ ስትራቴጂዎች ሲኖሩ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በሚገባ እየፈታችና ስብራቶቿን እየጠገነች እንደምትሄድም ያመላክታሉ::

ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት፤ የዓባይን ወንዝ ተፋሰስ ተከትለው በምዕራብ አቅጣጫ የሚፈሱ ወንዞችና በምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኘው የቀይ ባህር ክልል የኢትዮጵያን ዕድገትና ጥንካሬ፤ ውድቀትና ድክመት የሚተነብዩ ናቸው::

“ወደ ቀይ ባህር እየቀረብን ስንሄድ ታላቅነት፤ ከባህሩ እየራቅን ስንሄድ ደግሞ መዳከም እንደሚከሰት የታሪክ ዑደቶች በአንክሮ ያመላክታሉ” ሲሉ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ::

ኢትዮጵያ ነባራዊ ፍላጎቶቿን በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት ከሚደጋገሙ ታሪኮቿ የዓባይና የቀይ ባህር ጉዳይ አንዱ መሆኑን በማንሳት፤ ስትራቴጂካዊ እይታዎችንና ትልሞችን በማፍለቅ መጻዒ በጎ ዕድሏን ማረጋገጥ እንደሚቻል ይጠቅሳሉ:: ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓባይና በቀይ ባህር ላይ ያላትን አቋም የሚያንጸባርቀውና “የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” የተሰኘው ታሪካዊ መጽሐፍ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነም ይናገራሉ::

የስትራቴጂ መጽሐፉ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ በታሪክ ሂደት ችግር ሆነው ለዘለቁ ጉዳዮች መፍትሔ የሚሰጥ ከመሆኑ ባሻገር፤ የዓባይ ተፋሰስንና የቀይ ባህር ጉዳይን አንድ ላይ በማምጣት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያነሳሉ:: ለሀገሪቷ መሪ ስትራቴጂና የትኩረት ማዕከል መሆኑን ይጠቅሳሉ::

የዓባይ ወንዝና ቀይ ባህር የኢትዮጵያ መጻዒ ተስፋ ናቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም የዓባይ ተፋሰሶችን በስፋት በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላላቸው ዘርፎች መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ::

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በዓለማችን በጣት ከሚቆጠሩ ወሳኝ ስትራቴጂካዊና ቁልፍ ስፍራዎች አንዱ ቀይ ባህር ነው:: በዓመት ቢያንስ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ የባህር ላይ ንግድ መተላለፊያ መስመር ነው::

የቀይ ባህር ቀጣና የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት የቆየ የውሃ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል:: ኢትዮጵያ ለባህሩ ስትቀርብ ማደግን ስትርቅ መውደቅን የምታይበት ታሪካዊ ሀቅ ነው::

ሀገሪቷ ወደ ውሃው በመቅረብ የምታገኘው ጥቅም ሲሰላ በርካታ መሆኑን አንስተው፤ ወደ ውሃ አካሉ እንዳትጠጋ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶቿ የሚያደርጉትን ርብርብ መቀልበስ እንደሚገባም ነው የሚያስገነዝቡት:: ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ እነዚህ የውሃ አካላት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ዳይሬክተሩ አመላክተዋል::

“የዓባይ ተፋሰስና የቀይ ባህር ቀጣና ለኢትዮጵያ እንደ ዓይን ብሌን የሚታዩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ናቸው በማለት፤ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስና የባህር በር ባለቤትነትን ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ትብብርን በማሳደግ አብሮ መልማት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ወሳኝ ስትራቴጂዎች መሰነዳቸውን ጠቅሰዋል::

የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሐመድ ሀሰን በበኩላቸው፤ ሁለቱ የውሃ አካላት የሚታወቅ የሚመስል ነገር ግን ዝርዝሩ ጥልቅ የሆነ ጉዳይ ነው ይላሉ::

“ሁለቱ የውሃ አካላት ለምን ለኢትዮጵያ አስፈለጉ የሚለውን ተንትኖ መገንዘብ ካልተቻለ ወደ ፊት መራመድ አይቻልም::” የሚሉት አቶ መሐመድ፤ በዓባይም ሆነ በቀይ ባህር በኩል እንደ ሀገር ትልቅ እርምጃ መራመድ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::

ሁለቱ የውሃ አካላት የኢትዮጵያን መጻዒ ዕድል የሚወስኑ እንደመሆናቸው ስሜት መር የሆኑ ምኞቶችን በመሻገር አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በአግባቡ ማኖር የዚህ ዘመን ትውልድ ግዴታ መሆኑን በአጽንኦት ይናገራሉ::

ዓባይና ቀይ ባህር የኢትዮጵያ ወሳኞቹ አጀንዳዎች መሆናቸውን አንስተው፤ ሆኖም ትልቅ ጥቅም ባለበት ሁሉ ከባድ ጩኸቶችም እንደማይጠፉ ጠቅሰዋል::

ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ግንባታ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መርሀ ግብር የገጠሟት ተቃውሞዎች ብዙ መሆናቸውን በመግለጽ፤ አሁን ላይ በዓለም መድረክ እውቅናን እንዳገኘችባቸው አንስተዋል::

አሁን በውሃ ላይ የተጀመረው እንቅስቃሴም በርካታ ጩኸቶች ሊስተናገዱበት የሚችል ቢሆንም፤ ሀገር የጀመረችውን እርምጃ ግን ሳታቆም እጣፈንታዋን ለመወሰን በቁርጠኝነት መገስገሷን ነው የተናገሩት::

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬትና ከአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ጋር በትብብር ያዘጋጀው “የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚያትተው፤ ዓባይና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ደህንነትና ህልውና ከማስቀጠል አንጻር ቁልፍ ሚና አላቸው::

ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት ዕድገት በላይ ወደፊት እንድትሄድ ካስፈለገና በታሪክ በቀጣናው ላይ የነበራትን የጎላ ሚና ተመልሶ እንዲመጣ እነዚህ የውሃ አካላት ሚናቸው የጎላ ነው::

የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ የቀይ ባህር ተጋሪ ከመሆኗ ጋር የተያያዘ እንደነበር የሚያትተው መጽሐፉ፤ አሁንም ቢሆን ወደ ባህር ተጋሪነቱ መማተር እንደሚገባት ያስቀምጣል::

ወደ ቀይ ባህር መማተርና ወደ ዓባይ ተፋሰስ የሚቀላቅላት ውሃ በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ በሚገለጽበት ጊዜ የውሃ አካላትን ለመንካት ሲታሰብ ተጨማሪ ስጋት እንደሚኖር መጽሐፉ ያመላክታል::

ኢትዮጵያ ወደፊት ለምታደርገው ጉዞ ችግሮች ሊገጥሙ ይችላሉ በሚል ስጋት አርፎ መቀመጥ ሳይኖርባት ይልቁንም የትኛውንም ችግር እንደየባህሪው እየተጋፈጠች ጥቅሟን እያስከበረች መሄድ እንደሚገባት አመላክቷል::

አዲሱ ገረመው አዲስ ዘመን  የካቲት 22 ቀን 2016

Exit mobile version