Site icon ETHIO12.COM

ኬንያን መሰረት ያደረጉ ተቃዋሚዎች አደጋ ውስጥ ናቸው፤ ተላልፈው ሊሰጡ ነው

መቀመጫቸውን ኬንያ ያደረጉ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች ስጋት ላይ መሆናቸው ተሰማ። ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በገባችው አዲስ ስምምነት መሰረት ተላልፈው ሊሰጥ እንደሆነ እየተገለጸ ነው። ንግግርም እየተደረገ ነው።

በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ያሉ ነዋሪዎችን የደም ዝምድና መሰረት በማድረግ አንዴ ኢትዮጵያ፣ አንዴ ኬንያ በመግባትና አድራሻ በመቀያየር ጥቃት የሚያደርሱ ታጣቂዎች ለመንግስት ችግር እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊትም በተደጋጋሚ የማጽዳት ሲሰራ ወደ ኬንያ ዘልቀው በመግባት እንደሚሸሸጉ፣ ተመልሰውም አገግመው እንደሚመጡ በመጥቀስ ዘመቻውን አስቸጋሪ እንዳደርገው ዘመቻውን የሚመሩ ሲያስታውቁ እንደነበር ይታወሳል።

ሰሞኑንን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኬንያ የነበራቸውን ቆይታ ተከትሎ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እግር በግር ኬንያ ተገኝተው ከጸትታና ከአገሪቱ መከላከያ አዛዦች ጋር ተገናኝተው በጸጥታና ተመሳሳይ ጉዳዮች አብረው የሚሰሩበትን ጉዳይ ዝርዝር መምከራቸውን የኬንያ መገናኛዎች ዘግበዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የሁለቱ አገሮች ሚኒስትሮች ዓመታዊ ስብሰባቸውን አካሂደው ጸጥታን መሰረት ያደረገና በርካታ ስምምነት ማድረጋቸውን የመንግስት መገናኛዎች ይፋ አድርገው ነበር።

ኬንያና ኢትዮጵያ የድንበር ግጭትን የሚያስቀርና በአካባቢው ልማትን የሚያፋጥን ስምምነት ሞያሌ ላይ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የሚከሰተውን ግጭት የሚያስቀርና በአካባቢው ልማትን የሚያፋጥን የመግባቢያ ስምምነት ረዘም ላለ ጊዜ አከናውነዋል። ስምምነቱን የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በተገኙበት የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ነበሩ። ይሁን እንጂ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።

የኢትዮ12 የአዲስ አበባ ተባባሪ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላት እንደነገሩት ጠቅሶ ሲዘግብ ” የመጨረሻው ስምምነት ሁሉንም የቀደሙ ስምምነቶች እንከን የነቀሰና በቀጥታ ተግባራዊ የሚደረግ ነው” ብሏል።

ኬንያን መቀመጫቸው አድርገው ኢትዮጵያን የሚያጠቁ ሃይሎችን መከላከያ ከኬንያ የጦር ሃይል ጋር በመሆን እንዲያጸዳ ስምምነት ተደርሷል። የአገር መከላከያ እንደ አስፈላጊነቱ የኬንያን ምድር ተጠቅሞ እርምጃ እንዲወስድ የሚያስችለው ፈቃድ አግኝቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ናይሮቢን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች ተቀምጠው የትጥቅ ትግል የሚያስተባብሩ በሰላም ስምምነት ጉዳያቸውን እንዲቋጩ ኬንያ እያግባባች እንደሆነ ተሰምቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን ይህ ጥረት በአጭር ጊዜ ካልተሳካ ኬንያ አሳልፋ ልትሰጥ የምትችልበት አግባብ መቀመጡን ዜናውን ያስታወቁት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ ከእንግሊዝ ጋር የቀይ ባህርን ደህንነት ለማስጠበቅ ውል መግባታቸውን ተከትሎ አካባቢውን ሰላም ማድረግ ቀዳሚ የሚሰጠው አጀንዳ በመሆኑ ሁለቱ አገራት ከመቼውም በበለጠ በጸጥታ ጉዳይ አብረው ለመስራት መወሰናቸው ነው የተገለጸው።

ኬንያና ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ጉዳዮች አብሮ ለመስራት ሰፊ ዝርዝር ስምምነት መስማማታቸው፣ ኢትዮጵያም ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ግንባታ መጠናቀቁም የሰሞኑንን ጉብኝት ተከትሎ በይፋ መገለጽ ይታወሳል። ሁለቱ አገራት በመሰረተ ልማት፣ በልማት፣ ንግድን ለማስፋፋት፣ በኢንቨስትመንትና በቀጠናው ሰላም ጉዳይ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን መሪዎቹ በይፋ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

Exit mobile version