የኢትዮጵያ ፓርላማ “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር” በሚል ስም የሚጠራውን ቡድንና ሸኔን “ሽብርተኛ ብሎ” ከፈረጀ በሁዋላ የጥፋት ሃይላቸውን ለማዳከም መንግስት እየሰራ መሆኑንን እየገለጸ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ሁለት አገራት ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ለመስጠት መስማማታቸው ተሰማ። ዱባይ የነበሩ ዋና ተጠርጣሪዎች ተላልፈው መሰጠታቸው ታወቀ።

የኢትዮ12 የመረጃ ሰዎች እንዳሉት ሁለቱ አገራት ከስምምነት የደረሱት ተጠርጣሪዎቹ ውጭ አገር ሆነው ከተጠቀሱት ድርጅቶች ጋር በህቡዕ መስራታቸው የሚያሳይ ማስረጃና ጥፋት እንዲፈጸም የተላለፈ ኦዲዮ ቀርቦላቸው ካረጋገጡ በሁዋላ ነው።

ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን እንዲተላለፉ ከሌሎች ሁለት አገራት ጋር ንግግርና የመረጃ ልውውጥ እየተደረገ በመሆኑ አገራቱን በስም ለይቶ መዘርዘር አስፈላጊ እንዳልሆነ ያመለከቱት የመረጃው ሰዎች፣ ሁለቱም አገራት ከአውሮፓ መሆናቸውን አመልክተዋል። የህግም አስገዳጅነት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ዱባይ ከሚገኙ መካከል ዋና ተጠርጣሪዎች ተላልፈው ስለመሰጠታቸው የጠቆሙት እነዚሁ ክፍሎች ለኢትዮ12 የአዲስ አበባ ተባባሪ እንዳስረዱት ኬንያ በተመሳሳይ ተጠርጣሪዎችን አሳልፋ እንድትሰጥ አገራቱ ባላቸው የጋራ ስምምነት መሰረት ጥያቄ ቀርቦ በሂደት ላይ እንደሆነ አመልክተዋል። ደቡብ ሱዳንም ፈቃደኛነቷን ያላማቅማማት መግለጿ ታውቋል።

ትናንት በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩና ለአሸባሪው የሸኔ ቡድን የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎች የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያመላከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ” ከወዳጅ አገራት ጋር በመነጋገር ተላልፈው ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ነው” ማለቱ አይዘነጋም።

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ ከምርጫው በፊት የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት ስልት ነድፈው የሚንቀሳቀሱ አካላትና የመረባቸው አባላት ከነመዋቅራቸው መታወቃቸውን ኢትዮ12 ሰምታለች። ይህንኑ መረብና መዋቅር አስመልክቶ መንግስት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግም ለማውቀ ተችሏል።

መንግስት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀውና በተግባርም እንደሚታየው አሁን በአገሪቱ እየሆነ ያለው ንጽሃንን የመግደል፣ አድፍጦ ንብረትና መሰረተ ልማት ማፍረስ፣ ከሁሉም በላይ ዜጎችን በማንነታቸው መፍጀትና ማፈናቀል የመሳሰሉትን ድርጊቶች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደ ዓላማ የተያዘ ጉዳይ ነው።


    Leave a Reply