Site icon ETHIO12.COM

እነ ጃዋር – አሁን ባለንበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ያስቸግራል፤

ፍርድ ቤቱ እነ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ የ18 ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ


የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት እነ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 18 የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ጥር 04 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በነበረው ችሎት እንዲያሻሽላቸው ከታዘዘው የተወሰኑትን አሻሽሎ አቅርቧል።

ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ማመልከቻ አቅርቧል።

የማመልከቻው ይዘት በእነ ጃዋር የክስ መዝገብ አምስት ክሶች በተለይም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ጋር በተያያዘ አዋጁን ጠቅሶ ዋናው ክስ ላይ የጠቀሰውን የክስ ጭብጥ ፍርድ ቤቱ እንዲያሻሽል ትእዛዝ ቢሰጥም ማሻሻል እንደማይችል የተለያዩ ምክንያቶች ጠቅሶ ማመልከቻ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ችሎቱም የተወሰነ ጊዜ ወስዶ የዐቃቤ ሕግን ማመልከቻ መርምሯል። በመሆኑም ከጦር መሣሪያ አዋጅ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል የሰጠው ትእዛዝ አሳማኝ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ከጦር መሣሪያ ጋር ተያይዞ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስ የማያሻሽል መሆኑን በመገንዘብ እንዲቋረጥ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ይህንንም ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ ተከሳሾችን ጠይቋል፤ ነገር ግን የተከሳሽ ጠበቆች ተሻሽሏል የተባለውን ክስ በአግባቡ ለመረዳት ጊዜ ስለሚያስፈልግ እና ከደንበኞች ጋር ለመመካከር ስለሚያስፈልግ አሁን ባለንበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ያስቸግራል፤ ስለዚህ አጭር ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት አመልክተዋል።

ተከሳሾችም በዛሬው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባው ችሎቱ የተከሳሾች ጠበቆች ከጠቀሱት ወሳኝ በሚባለው የእምነት ክህደት ቃል መስጠት ጋር በተያያዘ በቂ ዝግጅት አድርገው እንዲመጡ ለመጪው ረቡዕ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በጥላሁን ካሣ

VIA- EBC

Exit mobile version