Site icon ETHIO12.COM

የ23 ትምህርት ቤቶች የብቃት ማረጋገጫ የእውቅና ፈቃድ ተሰረዘ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ባለስልጣን በመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሚጠበቅባቸውን የትምህርት ብቃትና ጥራት ያላሟሉ 23 ትምህርት ቤቶችን የእውቅና ፈቃድ መሰረዙን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በአስር ዓመት የፍኖተ ብልጽግና የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ሪፖርት ላይ ትናንት በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ በዘንድሮ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የትምህርት ብቃትና ጥራት ያላሟሉ 23 ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፈቃድ ሰርዟል።

ትምህርት ቤቶች በተደጋጋሚ ችግሮቻቸውን እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ማስተካከል ባለመቻላቸው የተሰረዙ መሆኑን ጠቁመው፣ የእውቅና ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው 15 መዋዕለ ሕፃናት፣ 7 የመጀመሪያ ደረጃ እና 1 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች ላይ እርምጃ ከመውሰድ በፊት በኢንስፔክሽን ማሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዲያሻሽሉ በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል ያሉት ወ/ሮ ሸዊት፤ ይህም ሆኖ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ለማስተካከል ፈቃደኛ ያልሆኑት ላይ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉትን ችግር ታሳቢ በማድረግ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
መረጃው የኢ ፕ ድ ነው።

Exit mobile version