የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያና ስነምግባር ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ቅጣት ይጣላል

  • መመሪያውን ጥሰው በተገኙ 12 የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ርምጃ ተወስዷል፣

የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ የቁጥጥር ሥራ በማካሄድ ከመመሪያ ውጪ ያልተገባ ክፍያ አስከፍለው የተገኙ ተቋማት ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዝግጅት ክፍል አላግባብ የክፍያ ጭማሪን አስመልክቶ ከወላጆች የቀረቡ ቅሬታዎችን መሠረት አድርጎ ለባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፤ ተቋማት የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ ባለስልጣኑ ቁጥጥር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቁመዋል።

‹‹የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ ቁጥጥር ይካሄዳል፣ በመመሪያው መሠረት ያላግባብ ያስከፈሉ ካሉ ገንዘብ እንዲመልሱ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ ርምጃዎች ይወሰዳል›› ነው ያሉት።

በተደረገው አጭር ምልከታ 12 የግል ትምህርት ቤቶች ጭማሪን አስመልክቶ የወጣውን መመሪያ ጥሰው በመገኘታቸው ከመመሪያ ውጪ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለወላጅ መልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዙንም ተናግረዋል።

በመመሪያ አተገባበሩ ላይ የተለያዩ ጥቆማዎች እየደረሱ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ አንዳንድ ተቋማት የምዝገባ ክፍያ መጨመር፣ በዓይነት መጠየቅ እና የመሳሰሉ ያልተፈቀደ ክፍያ ጭማሪ እያደረጉ እንደሚገኙ ጥቆማ ደርሶናል፤ ወርደን እያስተካከልን እንገኛለን ብለዋል።

ለክትትል የሚላኩ ባለሙያዎች አቅጣጫ ተሰጥቶ እንደሚላኩ በመጠቆምም፤ ባለሙያዎች የተከፈለበትን ደረሰኝ ተመልክተው እንዲያረጋግጡ የሚያደርግ የመገምገሚያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

ተግባሩ ባለሀብቶቹን ማነጋገር ብቻ አይደለም፣ ደረሰኝ ተመልክተው እንዲያረጋግጡ፣ ከተቻለም በየአንዳንዱ ተቋም የተወሰኑ ወላጆችን ማነጋገር የሚቻልበት አሠራር ተዘርግቷል፣ የተለያዩ ጥቆማዎች በመኖራቸው አሠራሩን እንደሚደግፍም አመልክተዋል።

ከባለሙያዎች አቅም ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ተቋማትን ለማየት በቅርንጫፍና በዋና መስሪያ ቤት ያሉ ባለሙያዎች በማሰማራት በሚገባ ለመገምገም ዝግጅት ተደርጓል። ከመመሪያው ውጪ ወርሃዊ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎችን አስከፍለው በተገኙ ተቋማት ላይ ርምጃ ይወሰዳል፣ ለሕዝብም ይፋ ይደረጋል።

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት በተዘጋጀው ወጥ የመገምገሚያ ዝርዝር ሃሳብ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ተቋማት ላይ ምልከታ በማድረግ የማስተካከያ ርምጃ ይወሰዳል።

በአብዛኛው እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ምዝገባ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከነሐሴ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማትን በመዘዋወር የሚደረገው ምልከታ ያላግባብ ክፍያ የተቀበሉ የትምህርት ተቋማት ገንዘብ እንዲመልሱ ከማድረግ ጀምሮ አስተዳደራዊ ርምጃ የሚወሰድ ይሆናል።

‹‹ከመደበኛ ክፍያ ውጪ በየትኛውም መልኩ ክፍያ ማስከፈል አይቻልም፣ አንድ የትምህርት ተቋም ፍቃድ የተሰጠው ለማስተማር እንጂ፤ መጽሐፍም ሆነ ደብተር መሸጥ አይችልም። ከተሰጠው ፍቃድ ውጪ የተንቀሳቀሰ ተቋም ከተገኘ ርምጃ ይወሰድበታል›› ብለዋል።

መመሪያው በ2014 ዓ.ም ጭማሪ ያደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ምንም ዓይነት ጭማሪ እንዳያደርጉ እንደሚያዝ አስታውሰዋል።

አምና ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ዘንድሮ መጨመር እንደማይችሉ ለመቆጣጠር የማስፈጸሚያ መመሪያ ተዘጋጅቷል። ዓላማው የኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም፣ የኑሮ ውድነት ችግርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አምና የጨመሩ ተቋማት እንዳይጨምሩ ለማድረግ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዘላለም ግዛው – (ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply