Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ተጀመረ

በትግራይ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የትራንስፖርት አገልግሎት በማስጀመር የፌዴራል ፖሊስ አባላት ትልቁን ድርሻ እንደተወጡ የመቀሌ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ከበደ አሰፋ ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት ሁሉም አገልግሎቶች ወደቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት የተቋማቱ ሰራተኞች ያለስጋት አገልግሎት እንዲሰጡ የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ነው የገለጹት፡፡የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ስራውን የጀመረው ጽህፈት ቤቱም ባሉት ውስን ሠራተኞች ፋይሎችን በማደራጀትና የተሰባበሩትን በመጠገን ወደ ስራ በመግባት ለመቐለ ከተማ ህብረተሰብ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ አቶ ከበደ አሰፋ ገልፀዋል፡፡

የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ብርድና ፀሀይ ሳይበግራቸው አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በመጠበቅ የህዝቡን የፀጥታ ሥጋቶች ከማስወገድ በዘለለ ቁጥጥርና ክትትል የሚያስፈልገውን የትራንስፖርት አገልግሎት በአራቱም አቅጣጫ ኬላዎች ህጋዊ እንቅስቃሴ እንዲፈጠርና ከታሪፍ ውጭ የሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎችን በማስተማር ፌዴራል ፖሊስ እየሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም የፌዴራል ፖሊስ የስራ ጫናን ለመቀነስ የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የክልሉን ትራፊክ ፖሊስና የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ሰራተኞችን ወደ ስራ በማሰማራት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም የመቐለ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣የታመሙ ህክምና እንዲያገኙ፣ልጆች እንዲማሩ የሁሉም ሰው ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም አስተማማኝ ሰላሙን ማረጋገጥ አለበት ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ፋና ዘግቧል።

Exit mobile version