Site icon ETHIO12.COM

በአንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

አንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሕግ ውጭ በመንቀሳቀስ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተመለከተ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትምህርት ጥራት ላይ ተወያይተዋል።  

ተቋማቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ራሳቸውን እንዴት ማዘመን ይችላሉ፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችንስ በምን መልኩ መስራት ይኖርባቸዋል የሚሉትና ሌሎችም በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።  

በውይይቱ እንደተመላከተው ተቋማቱ ባለፉት ዓመታት በቁጥር ደረጃ ቢጨምሩም፤ ጥራትና አግባብነት ላይ ውስንነት ይታይባቸዋል። ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት አጀንሲ የተገኘው መረጃ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር 278 መድረሱን ያሳያል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ እንደተናገሩት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት የጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።   “አንዳንድ ተቋማት ከ10ኛ ክፍል ላቋረጡ ተማሪዎች ዲግሪ ይሰጣሉ፤ ማንበብና ማጻፍ የማይችሉ ሰዎችም እንዲሁ ወረቀት እየወሰዱ ነው” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ። 

መቁረጫ ነጥብ ሳያሟሉ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ መኖራቸው መረጋገጡን ያነሱት ዶክተር አንዱዓለም እውቅና ሳይሰጣቸው እንደሚያስተምሩና ከተፈቀደው ተማሪ ቁጥር በላይ እንደሚመዘግቡም ተናግረዋል። ችግሮች እርምጃ በመውሰድ ብቻ ስለማይፈቱ ተቀራርቦ በመስራትና በመደጋገፍ ለማስተካከል መስራት ይገባል ብለዋል።

ዶክተር አንዱዓለም ተቋማቱ ከሕገወጥ እንቅስቃሴ ተቆጥበው ወደ ትክክለኛው መስመር መግባት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል። ከዚህ በኋላ እውቅና የሚሰጣቸው ተቋማት ተመዝነው የጥራት መስፈርት የሚያሟሉበት ስርዓት እንደሚዘረጋ አስታውቀዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ተቋማቱ የትምህርት ጥራት ችግር ተብለው ከተለዩት መካከል መምህራንን በጥራት በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። መንግስትና የግሉ ዘርፍ በመቀናጀት ችግሮችን ለማቃለል ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንደሚያግዛቸውም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ ጸጋዬም ተቋማቱ ጥራታቸውን እንዲያሻሽሉ ከሚመለከታቸው አካላት የሚሰጠው ድጋፍ ይጠናከር ብለዋል።

በተለይም የመምህራን ስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ ይደረግልን ሲሉ የጠየቁት ፕሬዚዳንቱ ተቋማቱም ራሳቸውን ለማብቃት ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

Exit mobile version