Site icon ETHIO12.COM

ተመራማሪዎች በአሜሪካ ሰባት አይነት የኮሮናቫይረስ አዲስ ዝርያ ማግኘታቸውን አስታወቁ

የአሜሪካ ተመራማሪዎች ሰባት ዓይነት አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎችን በአገሪቱ ማግኘታቸውን አስታወቁ፡፡

በአሜሪካ የተገኙት አዳዲስ ዝርያዎች በሳን ፍራንሲስኮ አካባቢ ደቡባዊ ካሊፎርኒያ ከተማ ከአፈር ላይ መሆኑንም ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

እንደተመራማሪዎቹ መረጃ ከሆነ ዝርያዎቹ አሁን ይለዩ እንጂ የተከሰቱት እ.አ.አ ከሀምሌ 2020 በፊት መሆኑን ገልጸዋል።

ዝርያዎቹ ተመሳሳይነት ያለው ባህሪ እንደሚታይባቸው ገልጸው፤ የአዳዲስ ዝርያዎች መገኘት ብዙ አስገራሚ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

የዝርያዎቹ ተለይቶ መታወቅ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለአሜሪካም ሆነ ለመላው ዓለም ወሳኝ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ የተገኙ ዝርያዎች ቀደም ሲል በእንግሊዝ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ ከተገኙት ዝርያዎች ጋር ተደማምረው የአዳዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎችን ቁጥር ከፍ በማድረጉ የመተላለፍ ፍጥነቱን ጨምሮታል።

ይህ ሁኔታ የወረርሽኙን ስጋት አስከፊ እንዳደረገውም ተገልጿል።

ምንም እንኳን አዳዲሶቹ ዝርያዎች አሁን እየተሰራጩ ካሉት ክትባቶች ጋር ያላቸውን መጣጣም፣ አደገኛነትና ሊያሳድሩት በሚችሉት ተጽዕኖ ዙሪያ ላይ ተጨማሪ የቤተ-ሙከራ ፍተሻ ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም እነዚህ አሁን ላይ የተለዩት ሰባት አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች አሁን እየተሰራጩ ባሉት ክትባቶች ላይ መጠነኛ የሆነ ተጽዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ የአዳዲስ ዝርያዎችን ባህሪ በቅርበት እየተከታተሉ ቫይረሱን መመከት የሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮችን መለየት የሚያስችል አንዳች ፍንጭ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ነባሩንም ሆነ አዳዲስ እየተፈጠሩ ያሉትን ዝርያዎችን መከላከል የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፣ አካላዊ ርቀት መጠበቅ እና መተፋፈግን መቀነስ ዋነኞቹ የመከላከያ መንገዶች መሆናቸውን ተመራማሪዎቹ አስገንዝበዋል። via (ኢዜአ)

Exit mobile version