Site icon ETHIO12.COM

አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ የውጫሌ ውል ጣልያንኛ ትርጉም ኢትዮጵያን ጥገኛ በማድረግ ዓላማ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ቀድመው የተረዱ ሊቅ ናቸው፡፡ አጤ ምኒልክ የውሉን ይዘት እንዲመረምሩ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሠረት የ17ኛው አንቀጽ ትርጉም የተዛባ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ እና ሉዓላዊነቷን የሚዳፈር መሆኑን ቀደም ብለው በምስጢር ለንጉሠ ነገሥቱ እና ለእቴጌ ጣይቱ አስረድተዋል፡፡

ከእሳቸው በመቀጠል ለትምሕርት ወደ ጣልያን ተልከው የነበሩት አፈወርቅ ገብረየሱስ ጣልያን ውስጥ የተጻፉ ጋዜጦችን በማንበብ ስሕተት መኖሩን ተገንዝበዋል፤ ይህንንም ከስምምነቱ በኋላ የኢትዮጵያን ልዑክ ይዘው ወደ ጣልያን ለተጓዙት ራስ መኮንን ወልደሚካኤል አብራርተውላቸዋል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግም ራስ መኮንን ለጣልያን መንግሥት ቁጣ የተቀላቀለበት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ በስምምነቱ ወቅት የነበሩት ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሴም የጣልያንን ሴራ ከተገነዘቡት መካከል አንዱ ናቸው፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምሕር አየነው ስለሺ ለአብመድ በሰጡት ማብራሪያ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ የውጫሌ ውል ሴራውን በመረዳት ቀዳሚ ናቸው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የጣልያንን ስውር አጀንዳ የተረዱ ኢትዮጵያውያን ለንጉሡ እና ለንግሥቲቱ በተደጋጋሚ ይነግሯቸው ነበር፡፡

የታሪክ መምሕሩ እንዳሉት አጤ ምኒልክ መንበረ መንግሥታቸው እንዳይናወጥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነትም እንዳይበላሽ ነገሮችን በጥንቃቄ ይከታተሉ ነበር፡፡ የትርጉም ስሕተቱን እውነታ በተረዱ ጊዜም ነገሮችን ለማመቻቸት ጥበብ የተሞላበት አካሄድን መርጠዋል፡፡

የሚደርሳቸውን ምስጢራዊ መረጃ በአጽንኦት እየተመለከቱ ከጣልያን ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ለማስመሰልም ጥረት አድርገዋል፡፡ ጣልያኖች ግን አይናቸውን በጨው አጥበው ለማግባባት ጥረት አድርገዋል፡፡ በተቃራኒው አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠልሸት እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፤ ርምጃ እንዲወሰድባቸውም ሀሰት የተሞላው ክስ አቅርበዋል፡፡ በቤተ መንግሥት እንዲታሰሩም አድርገዋል፡፡ አፈወርቅ ገብረየሱስም የጣልያንኛ ቋንቋ እውቀት እንደሌለው በመናገር ጉዳዩን ለማድበስበስ ጥረዋል፡፡

አጤ ምኒልክ ጉዳዩን በጥንቃቄ ሲከታተሉ እንደነበር የታሪክ መምሕሩ አብራርተዋል፡፡ “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እንደሚባለው እውነቱ ግልጽ እየሆነ ሲሄድ ራስ መኮንን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ አለመግባባቱ እየጠነከረ ሄዶ አይቀሬው ጦርነት ተካሄደ፡፡ ፍትኃዊ ጦርነት ያደረገችው ኢትዮጵያ ድሉን ተቀዳጀች፡፡ የመላው ዓለምን ታሪክም ቀየረች፡፡ እነሆ ዛሬ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል ሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል እየተከበረ ነው፡፡

አለቃ አጽመጊዮርጊስ የውጫሌ ውል ትርጉም ቀድመው መገንዘባቸው ሁኔታዎችን መልክ ለማስያዝ ጥሩ ግብዓት ሆኗል፡፡

መምሕር አየነው እንዳሉት ስምምነቱን የማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀመርም አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ የውጫሌ ውል ታሪክ የሚያስተምረው ጠንቃቃ መሆን፣ ነገሮችን በስክነት መመልከት እና ዝግጁነትን ነው፡፡ ሴራዎችን በማጋለጥ በሀገር ላይ የሚደርስ ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል ትውልዱ ከአጽመ ጊዮርጊስ ሊማር ይገባልም ብለዋል የታሪክ መምሕሩ፡፡

በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ውሳኔ ማሳለፍን ሊማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ሀገር እንዳትወረር ያደረጉትን ተጋድሎ በሚገባ ከመዘከር ባለፈ የሀገርን ጥቅም ለማስከበር አንድነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡


Exit mobile version