Site icon ETHIO12.COM

ዳግም ትኩረት ለኮቪድ -19


በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ላይ ልክ የዛሬ አመት በዚህ ቀን አንድ ብሎ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

የጤና ሚኒስትር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች እና ከማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ወረርሽኙ የከፋ ቀውስ እንዳያስከትል የቅድመ መከላከል እና የድህረ መከላከል ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፤ በመስራት ላይም ይገኛል። በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከገባ አንድ ዓመቱን ባስቆጠረበት ዕለት የኮቪድ-19 ቫይረስ ክትባትንም በዛሬው ቀን መስጠት ጀምራለች። ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘበት ግለሰብ የ48 አመት የጃፓናዊ ዜግነት ያለው ሲሆን ከቡርኪና ፋሶ አገር የጉዞ ታሪክ የነበረው እንደሆነ ይታወሳል፡፡በኢትዮጵያ ለ 2‚214‚180 ግለሰቦች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን 172‚ 571 ግለሰቦች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 141‚195 ግለሰቦች ያገገሙ ሲሆን የ2‚510 ግለሰቦች በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥርም እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፤እስከ ትላንትናው እለት ብቻ 454 ግለሰቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ እለት ጀምሮ ይሄ ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ወደ ኮቪድ- 19 የህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 61 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ በዛሬው እለት በደረሰን መረጃ ብቻ 7 ያህል ግለሰቦች ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕብረተሰቡን መዘናጋት እና የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ አለመተግበር ተከትሎ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች አስደንጋጭ እና አስከፊ በሆነ መንገድ በወረርሽኙ ስዎች እየተያዙ እና ህይወታቸው እያለፈ ይገኛል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለው የተለያዩ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየጨመረ ስለመጣ ችላ ሳንል የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር ልንከላከል ይገባል።

የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ከተከሰተበት በአንድ አመት በዚህ ዕለት የኮቪድ 19 ክትባት ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች፣ እድሜያቸው የገፉ እና ተጓዳኝ ህመም ያላቸው እንዲሁም ሌሎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን እንዲያገኙ ደረጃ በደረጃ ለመከተብ መርሀግብር ተዘጋጅቶ ስራ መጀመሩ ትልቅ እምርታ ሲሆን ክትባቱን ለሁሉም የማህበረስብ ክፍል ማዳረስ የማይቻል መሆኑን በመገንዘብ የኮቪድ 19 የመከላከያ መንገዶችን ተግራዊ ልናደርግ ይገባል፡፡

የጤና ሚኒወቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ የተከሰተበትን አንድ አመት በምናስታውስበት እለት ለኮቪድ-19 መከላከል እና ቁጥጥር የበኩላቸውን ሲያበረክቱ የነበረውን ሁሉንም የማህበረሰብ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የሐይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የጤና ባለሙያዎች፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ምስጋና እያቀረብን፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት የስርጭት አቅሙን አጠናክሮ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ፤ በቫይረሱ ህይወታቸውን የሚያጡ ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ከዚህ የከፋ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ሳያስከትል መጀመሪያ ላይ እንደነበረው ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የጥንቃቄ እና የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብር ኮቪድ-19 ከዚ በላይ ዋጋ ሳያስከፍለን ቀድመን እንድንጠነቀቅ የጤና ሚኒስቴር ጥሪውን ያቀርባል።

Via Ministry of health

Exit mobile version