ETHIO12.COM

ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ፡ ‘ቡልዶዘር’ የተባሉት የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት የጆን ማጉፉሊ ማን ነበሩ?

ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ነው ሙሉ ስማቸው። ቡልዶዘር ነው ቅጽል ስማቸው።

ሲወለዱ የጭሰኛ ልጅ ነበሩ። ሲሞቱ ግን ፕሬዝዳንት ነበሩ። ቡልዶዘር የሚለው ቅጽል ስም ከየት መጣ? ቡልዶዘር (ሺዶማ) የተባሉት ያለምክንያት አይደለም።

ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት የሥራና ከተማ ሚኒስትር ነበሩ። መንገድ በስፋት ያሠሩ ነበር ያን ጊዜ። የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ነፍሳቸው ነበር ማጉፉሊ። ሕዝቡ ቡልዶዘር ሲል ቅጽል አወጣላቸው። ይህ ቅጽል ስም ግን ኋላ ላይ እየሰፋ ሄዶ መነሻውን ሳተ። ቡልዶዘር የሚለው ስም ሰውየው የመንግሥት ወጪን በመቀነስና ሙሰኞችን መጠራረግ ስለሚወዱም ነው ተባለ። የአስተዳደር ዘያቸው መጠራረግ ስለነበር ስሙ የተስማማቸው ይመስላል።

ማጉፉሊ ሚዲያ ማስደንበር ይወዳሉ፤ ነጻ ድምጾችን ያፍኑም ነበር። ተቃዋሚዎችን አሸብረዋል። ሆኖም ሞታቸውን ያጀበው ያ ሳይሆን ለኮሮናቫይረስ ያሳዩት የነበረው ንቀት ነበር። ምናልባት እሱው ይሆን ከዚህ ዓለም ያሰናበታቸው?

“ኮሮናቫይረስ ጂኒ ነው”

ኮሮናቫይረስ ታንዛኒያ ሲገባ ማጉፉሊ ተበሳጩ። ሕዝቡ ቀን ተሌት እንዲሠራ እንጂ ቤቱ እንዲቀመጥ በፍጹም አይፈልጉም። አንድ መላ ዘየዱ። “ሕዝቤ ሆይ! ለዚህ ተህዋሲ አትንበርከክ! ቤተክርስቲያን ሄደህ ጸልይ እንጂ በፍጹም ቤት አትቀመጥ” አሉ። ሕዝቡም ያን አደረገ። “ኮሮና ጂኒ ሰይጣን ነው እንጂ ተህዋሲ አይደለም” የሚለውን ሐሳብ በሕዝባቸው ውስጥ አሰረጹ። ሳይንስ ግን ሰውየውን ታዘባቸው። ቫይረሱም ሳይናደድባቸው አልቀረም።

ከሰኔ 2020 ጀምሮ ማጉፉሊ አገሬ ታንዛኒያ ከኮቪድ-19 ተህዋሲ ነጻ ነች ሲሉ አወጁ። ጭምብል ማጥለቅን ተሳለቁበት። ኮቪድ-19ን ንቀው የዜና ማድመቂያ አደረጉት። በአገራቸው አልበቃ ብሎ ጎረቤት አገሮች የእንቅስቃሴ ገደብ ሲያደርጉ “የማይረቡ ፈሪዎች” አሏቸው። ለምዕራቡ ተንበርካኪ አድርገው ሳሏቸው።

ማጉፉሊ በ2015 የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ፣ ታንዛኒያ የሚያስፈልጓት ዓይነት ፕሬዝዳንት ሆነው ነበር የተገኙት። ሙስናን የሚጸየፉና በሥራ የሚያምኑ። ቀን ተሌት ቢሠሩ አይደክማቸውም።

ቡልዶዘራዊነታቸውን አጠናክረው ቀጠሉበት። ውጤት ተኮር የሆኑ ፕሮጀክቶችን ነድፎ የማስፈጸም አቅማቸው ተደነቀላቸው። ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ምሳሌ መሆን ጀመሩ። ገና ፕሬዝዳንት ሆነው በተመረጡ በመጀመርያው ቀን የገንዘብ ሚኒስቴር ቢሮ ሄዱ።

ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ተሟልተው አልተገኙም ነበር። ማጉፉሉ ጦፉ። ይህን በፍጹም እንደማይታገሱ እቅጩን ተናገሩ። ከሥራ የቀረ አለቀለት። ለደመወዝ ቀን ብቅ እያለ የሚጠፋ “ጎስት ዎርከርስ” እየተባለ የሚጠራን ታንዛኒያዊ ጠራርገው አባረሩ። ሥራውን የማይፈልግ የመንግሥት ሠራተኛ ብቻ ነው ከዚያ ወዲህ ከቢሮ ሥራ የሚቀር።

ማጉፉሊ የዛቻ ብቻ አይደለም፤ የድርጊት ሰው ናቸው። ከሥራ የሚቀሩትን ብቻ ሳይሆን ሙሰኛ አለቆችን ጠራርገዋል። አንዳንድ ጊዜ ሹመኞችን የሚያባርሩት ታዲያ በቀጥታ በብሔራዊ ቴሌቪዥን እየታዩ ጭምር ነበር። ለሌላው መቀጣጫ እንዲሆኑ። በዚህ ጊዜ ቡልዶዘር ኑርልን አላቸው አገሬው። እሳቸውም ተበረታቱ። ማጉፉሊ ገና ድሮ ወጪ የሚባል ነገር ያበሳጫቸዋል። በተለይ ያልተገባ ብልጭልጭ ወጪ ታንዛኒያ ማውጣት የለባትም ብለው በጽኑ ያምኑ ነበር። “ምክንያቱም ድሆች ነን” ይላሉ።

ማጉፉሊ በሥራ በዘመቻዎች በመሳተፍ ሠርተው ያሳዩ ነበር
የምስሉ መግለጫ,ማጉፉሊ በሥራ በዘመቻዎች በመሳተፍ ሠርተው ያሳዩ ነበር

በዚህ የተነሳ በድምቀት ይከበሩ የነበሩ በርከት ያሉ ክብረ በዓላትን አስቀርተዋል። በ54 ዓመታት የታንዛኒያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የነጻነት ቀን እንዳይከበር ያደረጉት እሳቸው ናቸው። “ቸበርቻቻ አያስፈልግም ሥራ ነው እንጂ” አሉ። “ሕዝቤ ሆይ! ነጻ የምትወጣው የነጻነት በዓልን በማክበር ሳይሆን ተግቶ በመሥራት ነው፤ ስለዚህ እጅህ መቁሸሽ አለበት” ሲሉ ጮኹ።

ማጉፉሉ ሕዝቡን በማዘዝ ወደ ቅንጡ ቤተ መንግሥት የሚገቡ ሰው አልነበሩም። እሳቸውም በዘመቻ ይሳተፉ ነበር። ሠርተው ያሳያሉ። ለምሳሌ የቤተ መንግሥቱን ደጅ የሚጠርጉት እሳቸው ራሳቸው ነበሩ። ኃላፊዎቻቸው በሆነ ባልሆነው ወደ አሜሪካና አውሮፓ ይጓዙ ነበር። ለሕክምና፣ ለጉብኝት፣ ወዘተ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በሕዝብ ገንዘብ ነበር።

አንድ ኃላፊ የውጭ አገር ጉዞ ቢያደርግ ወዮለት ብለው ደነገጉ። ተፈጻሚም ሆነ።

ይህ እርምጃቸው በታንዛኒያውያን ዘንድ እጅግ ተወዶላቸው ነበር። እንዲያውም በማኅበራዊ የትስስር መድረክ መነጋገርያ ሆነው ነበር። “ማጉፉሊ ቀጥሎ ምን ያደርጋሉ” የሚል የድራምባ ሐረግ (Hashtag) ተፈጥሮም ነበር። ማጉፉሊ ከአገራቸው ባሻገር በሌሎች አፍሪካውያን ዘንድ ውስጥ ውስጡን አድናቆት ማግኘት ጀማምረውም ነበር።

ለምሳሌ በ2017 አንድ እውቅ የኬንያ ፕሮፌሰር በዳሬ ሰላም ዩነቨርስቲ ተገኝተው በሰጡት የአደባባይ ዲስኩር “አፍሪካ አዲስ አስተዳደር ያሻታል” ካሉ በኋላ ይህ አፍሪካን የሚለውጠውን የአስተዳደርም ዘዬ “ማጉፉሊኬሽን” ሲሉ ሰይመውታል።

ማጉፉሊ በዚህን ያህል ተጽእኖ መፍጠር ቢችሉም የዲሞክራሲ ጸር ሆነው ነበር የሚታዩት። ተቃዋሚ በማሽመድመድ፣ ነቃፊዎቻቸውን ነቅሶ በማሰር፣ ነጻ ሚዲያን በማፈን ስማቸው ይነሳል።

ጆን ማጉፉሊ በአጭሩ

ማጉፉሊ መጀመሪያ ፕሬዝዳንት ሆነው በተመረጡ በሁለተኛ ወራቸው የፓርላማ የቀጥታ ሥርጭት እንዳይተላለፍ አገዱ። ያን ጊዜ ሰበብ ያደረጉት ወጪ ቅነሳን ነበር።

ተቃዋሚዎች ግን ይህ ነገር ለሳንሱር እንዲመች አድርጎ የፓርላማን ክርክር ለሕዝብ ለማቅረብ ነው ብለው ከሰሷቸው። እንዲያውም ይህን እርምጃ ተቃውመን ሰልፍ እንወጣለን አሉ። ሆኖም ሰልፉ በማጉፉሊ ሰዎች እውቅና ተነፈገውና ታገደ።

በ2017 ደግሞ ማጉፉሊ የታንዛኒያው ራፐር ናይ ዋ ሚቴጎ ዘፈን ዘፈነባቸው። ሚቴጎ ሙዚቃውን በለቀቀ በሰዓታት ውስጥ ራሱን እስር ቤት አገኘው።

ይህ ዘፋኝ በራፕ ሙዚቃው ያዜመው ግጥም በደምሳሳው ሲተረጎም እንዲህ የሚል ስንኞች ነበሩበት፣

እስኪ ንገሪኝ አገሬ፣

ነጻነት አለ ወይ በሰፈሬ

ያሻኝን ብዘፍን ጉራማይሌ

አገኘው ይሆን ራሴን ከከርቸሌ?

ማጉፉሊ ራፐሩን እንደምኞቹ ከርቸሌ ወረወሩት። በዳሬ ሰላም ማዕከላዊ እስር ቤት ታጎረ። በዚህም ማጉፉሊ ለትችት ቦታ እንደሌላቸው አሳዩ።

ማጉፉሊ ለሚዲያ ርዕስ የሚመቹና አንዳንዴም አስቂኝ ሰው ነበሩ።

ለምሳሌ ይህን ተቺ ሙዚቃ ያቀነቀነውን ናይ ዋ ሚቴጎን ከአንድ ቀን በኋላ ከእስር ሲያስፈቱት አንድ ምክር መከሩት። “ስለ ግብር አጭበርባሪዎች ሙዚቃ ሥራልኝ” በማለት።

ፕሬዝዳንት ማጉፉሊን ግብር አጭበርባሪዎች በጣም ያናድዷቸው ስለነበር ነው ለዘፋኙ ይህን ምክር የሰጡት።

በ2017 ደግሞ ዋንኛ ተቃዋሚያቸውና የምክር ቤት አባሉ ቱንዱ ሊሱ ቤታቸው ሳሉ ተተኮሰባቸውና ክፉኛ ቆሰሉ። የማጉፉሊ ሰዎች እንዳደረጉት ይታመናል። ሆኖም ሰውየው እንደምንም ድነው ከ3 ዓመት በኋላ ተገዳዳሪያቸው ሆነው ለፕሬዝዳንትነት ተወዳደሩ።

ሚስተር ሊሱ የግድያ ሙከራ እንደተረገባቸውና ታንዛኒያን እየመሯት ያሉት ሰው አምባገነን እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር። ማጉፉሊ እስከወዲያኛው ያሰናብቱታል ቢባልም ተፎካካሪያቸው እንዲሆን ፈቀዱለት።

የምስሉ መግለጫ,ማጉፉሊ የአስተዳደር ዘይቤያቸው የተቀዳው ከአገሪቱ የነጻነት አባት ጁሊየስ ኔሬሬ እንደሆነ ይነገራል

ምዕራብ ጠልነትና ማጉፉሊ

ማጉፉሊ ምዕራባዊያን አፍሪካን በዝብዘዋታል ብለው ያምናሉ። ስለዚህ በተራችን እነሱን መበዝበዝ አለብን ሲሉ ያስባሉ። በዚህ ረገድ በየጊዜው የውጭ ድርጅቶችን የሚያስጨንቁ አዳዲስ መመርያዎችን ያወጡ ነበር። ከነዚህ መሐል የካናዳው ባሪክ ወርቅ እህት ኩባንያ የሆነውን አካሺያ ማዕድን ድርጅትን 190 ቢሊዮን ዶላር ለመንግሥት ክፈል ብለው አነቁት።

ለምንድነው የምከፍለው ቢላቸው፣ በቃ እስከዛሬ የከበሩ ማዕድናትን ከታንዛኒያ ስታወጣ ነበር። ገቢህን ስንደምረው ታንዛኒያ ይህን ያህል ማግኘት እንዳለባት ደረስንበት አሉት። ኩባንያው ደነገጠ። ከብዙ ድርድር በኋላ 300 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

ከዚህ ዕለት በኋላም ይህ የካናዳው ባሪክ ወርቅ አውጪ ኩባንያ ከሚያወጣቸው ማዕድናት 50 ከመቶውን ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርግም ተገደደ። ማጉፉሊ የአስተዳደር ዘይቤያቸው የተቀዳው ከአገሪቱ የነጻነት አባት ጁሊየስ ኔሬሬ እንደሆነ ይነገራል። እሳቸውም ይህንን ብለውት ያውቃሉ። ማንም እንዴት አገሬን መምራት እንዳለብኝ ሊነግረኝ አይገባም ይሉ ነበር።

በአንድ ወቅት ኮሮናቫይረስ የእንቅስቃሴ ገደብን በተመለከተ የተናገሩት ይህንኑ የሚመሰክር ነበር።

“አባቶቻችን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየተነገራቸው አይደለም ያስተዳደሩን።…እንዲህ ዓይነት ቤት ዘግታችሁ ተቀመጡ የሚል መመርያ የሚያወጡ ሰዎች ከሩቅ ሊያስተዳድሩን ነው የሚሹት። የእኛ አባቶች እንዲህ አይነቱን ነገር አይቀበሉም ነበር” ሲሉ ምዕራባዊያንን ተችተዋል። “ድህነት ምን ማለት እንደሆነ አውቀዋለሁ”

ማጉፉሊ ከጭሰኛ ቤተሰብ በሰሜን ምዕራብ ቻቶ በሚባል ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው የተወለዱት። “ድህነትን በደንብ አውቀዋለሁ” ይሉም ነበር። እሳቸው ልጅ እያሉ ታንዛኒያን የሚያስተዳድሯት ጁሊየስ ኔሬሬ ነበሩ።

“ቤታችን ከጭቃ ነበር የተሰራው፣ በልጅነቴ ከብቶችን አግድ ነበር። ቤተሰቤን ለመታደግ ወተትና ዓሳ እያዞርኩ ነበር የምሸጠው። ድህነት ምን ማለት እንደሆነ ለእኔ አትነግሩኝም፤ ለዚህ ነው ድሆችን ለማገዝ ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት” ሲሉም ተናግረዋል። ማጉፉሊ ጭሰኛ ሆነው ተወልደው ፕሬዝዳንት ሆነው ሞቱ። በተወለዱ በ61 ዓመታቸው።

BBC Amharic

Exit mobile version