Site icon ETHIO12.COM

የአማራ ብሄረተኝነትና ድክመቱ !

ባለፉት ሶስት አመታት ገነው ከወጡ የሀገራችን ፖለቲካ ሁነቶች አንዱ የአማራ ብሄረተኝነት ነው። መልካም ሊባሉ የሚችሉ አስተዋጽኦዎቹን ለብሄረተኞቹ ትቼ ያስተዋልኳቸውን ጥቂትቹ ድክመቶቹን ልጠቋቁም :

፩. የአማራ ብሄረተኝነት የሀሳብ መሪዎች እጅግ ደካማ ከሚባል የሁናቴዎች እና የሀይል አሰላለፍ ትንተና ላይ ነው ፖለቲካቸውን የመሰረቱት። በአማራ ብሄረተኞች ዕይታ ሳር ቅጠሉ ሳይቀር ‘ የአማራ ህዝብ ጠላት ‘ ነው። ህወሃት ፣ ብልጽግና ፣ ኢዜማ ፣ ኢሳት ፣ ኦፌኮ ፣ ብርሃኑ ነጋ ፣ አቢይ አህመድ ፣ ታዬ ደንዳኣ እያለ ይቀጥላል። በሌላ ቋንቋ መነሻቸው ለአማራ ህዝብ ወዳጁ አማራ ብቻ ነው የሚል ይመስላል ። ይሄ የደንቆሮ ትንታኔ ግን ከአማራ ህዝብ ስነ ልቦና ጋር ፈጽሞ የተቃረነ ነው። የአማራ ህዝብ የትኛውንም የሀገሪቱ ክፍል ሀገሬ ብሎ የሚኖር ፣ ከሁለም ኢትዮጵያውያን ጋር ተዋህዶ ለዘመናት የኖረ ህዝብ ነው። አዲሶቹ ብሄረተኞች ጠላት ሊያበዙለት ደከሙ እንጂ የኖረ ትስስሩን ሲያጠናክሩ ብዙም አልታየም። አንዳንዴ ራሴን ስጠይቅ አማራ ኢትዮጵያውያንን አግብተው የተዋለዱትን አቢይ አህመድ እና ብርሃኑ ነጋን ” የአማራ ጠላት ” ብሎ ከፈረጀ ስብስብ ምን ይጠበቃል እላለሁ !

፪ . ስትራቴጂክ አጋሮቹን የማያውቅ ብሄረተኝነት። ለአማራ ብሄረተኝነት የዜግነት ፖለቲካ አራማጆችና እንደ ብልጽግና ፣ አረና ፣ ኢሶዴፓ ፣ ኦብነግ ወዘተ ያሉ ስብስቦች ስትራቴጂክ አጋሮቹ ሊሆኑ የሚችሉ በተለይም እንደ ኢዜማ እና ብልጽግና ፓርቲዎች ውስጥ አማራ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸው ናቸው። የአማራ ብሄረተኜች ግን ትልቁ ችሎታቸው ድልድይ መስበር ነውና ለአንዷለም አራጌም ፣ ለደመቀ መኮንንም የአማራነት ሰርተፍኬት ካልሰጠን የሚሉ ደናቁርት ናቸው።

፫. የሀሳብ መሪ ፣ ዲሲፒሊን ፣ ግልጽ አደረጃጀት የሌለው ብሄረተኝነት። ደጋግሜ እንደጻፍኩት የአማራ ብሄረተኝነት የሀሳብ ግልጽነት clarity of thought የሌለው ፣ የአጭር እና ረጅም ጊዜ ግቡ በግልጽ የማይታወቅ ማይክራፎን የጨበጠ ሁሉ የሚመራው ነው። ከአማራ ብሄረተኞች ጋር በጋራ አጃንዳዎች ላይ በአንድነት እንስራ ብሎ የሚያስብ የትኛውን አመራር ማናገር እንዳለበት ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ በተለይም በውጭ ሀገራት ስፍር ቁጥር የሌላቸው መሪ ነን ባዮችና ማህበራት ያሉት ነው። እነዚህ ማህበራት ለምን ባንድ አይሰባሰቡም ለህዝቡ ጥቅም በጋራ አይሰሩም ብሎ የሚጠይቅ መልስ ማግኘቱን እንጃ።

፬. ተግባር ላይ አልቦ የሆነ ብሄረተኝነት። በአሁኑ ወቅት እንደ አማራ ህዝብ ለጥቃት የተጋለጠ የለም። ባለፈው አንድ አመት ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ክልሎች ውስጥ ብቻ ለግድያና ስደት የተዳረገውን ህዝብ ቁጥር ለዚህ ማሳያ ነው። ያም ሆኖ ስፍር ቁጥር የሌለው የአማራ ብሄረተኛ እታገልልለታለሁ ለሚለው ህዝብ በአለም አቀፍ ምድረክ ድምጽ መሆን ያልቻለ ፣ በሀገር ውስጥም ዱቄትና አልሚ ምግብ ሰፍሮ የወገኑን መከራ በጥቂቱም ያልቀረፈ ነው። ከዚህ ይልቅ ምንም ያልተቀናጁ የሶሻል ሚዲያ ካምፔይኖች ብዙዎቹም ከስድብና ዘለፋ ያልዘለሉ እንካ ሰላንትያዎችን ሲጭር የሚዉል አክቲቪዝም ነው።

እውነት ለመናገር በውጭ ሀገራት ያለው የአማራ ብሄረተኛ ነኝ ባይ ፣ ሌላውንም ኢትዮጵያዊ በጨዋነት አስተባብሮ የመተከል ተፈናቃዮችን በክብር ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ማቋቋም አቅም ያንሰው ነበርን ?

ለማንኛውም ስለ አማራ ብሄረተኝነት ብዙ ማለት ይቻላል። ብዙዎቹ እዚህ ስብስብ ውስጥ ያሉ ሰዎች መፈክር ከመስበቅ ያለፈ የውይይትና ሀሳብ መለዋወጥ ልማድ ስለሌላቸው ከላይ ያሉት ፍሬ ነገሮች ይበቃሉ። የአማራ ብሄረተኞች ሁሉን ጠላት አድርገው ከማሰብ ይልቅ አጋርና ወዳጅ ማብዛትን ፣ ከስድብና ዘለፋ ይልቅ መወያየትን ልማድ ቢያደርጉ የአማራ ህዝብ ከእነርሱ ባላነሰ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገናችን መሆኑን ተረድተው የዚህ ህዝብ መከራ በኢትዮጵያውያን የጋር ትግል እንጂ በእነርሱ የስሜት ፖለቲካ እንደማይቀረፍ ቢረዱ መልካም ነው።

Samson Michailovich የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ

Exit mobile version