Site icon ETHIO12.COM

የሃጫሉን ግድያን ተከትሎ በተከሰተዉ ሁከት የግድያ ወንጀል የፈጸሙ እንደየተሳትፏቸው ከአንድ እስከ 22 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በተከሰተዉ ሁከት የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች እንደየተሳትፏቸው ከአንድ ዓመት እስከ 22 ዓመት በጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ አካባቢዎች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በተከሰተዉ ሁከትና ብጥብጥ ዉስጥ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በ6 ዞኖች በሶስት ሺህ 373 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በመመስረት በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው የተከሳሾች ቁጥር 90 በመቶ በሚሆኑት ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ከተሰበሰቡት ማስረጃዎችም መካከል ከ90 በመቶ የማያንሱ ምስክሮች በችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን መስጠት ችለዋል፡፡ በህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ የተከናወኑ ተግባርትን እና የተገኙ ውጤቶችን ክስ ስንመሰርት እንዳደርግነው ሁሉ በቅርብ ቀን ሰፊ መግለጫ የምንሰጥ ሲሆን ከወንጀል ድርጊቶቹ መካከል አንዱን በተመለከተ ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ እንደሚከተለው አመላክቷል፡፡

በተከሳሾች እነጂሎ በዳሶ (35 ሰዎች) መዝገብ ከቀረቡት 11 ተከሳሾች መካከል 2ኛ ተከሳሽ (ሀቢብ በሪሶ)፣ 5ኛ ተከሳሽ ( አማን አቤ)፣ 6ኛ ተከሳሽ (ሙስጠፋ ዋሪሶ) እና 8ኛ (ሮባ ኤዳኦ) በወንጀል ህግ አንቀጽ 240/3፣ 539(1ሀ) እና 690(1ለ) መሰረት በኦሮሚያ ብ/ክ/መ ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ 01 ቀበሌ በቡድን በመሆን በቀን 23/10/2013 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ሲሆን የሟች አቶ ገለታዉ አዉላቸዉ መኖሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ ሰብሮ በመግባት በአምስት የቤተሰብ አባላት ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸም እና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተሳትፈዋ በሚል እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ (ሮባ አማን)፤ 14ኛ ተከሳሽ (ከድር ራበቶ)፣ 16ኛ ተከሳሽ (አለሙ ነጋሽ) እና 17ኛ ተከሳሽ (ሚኪ ጉዬ) በወንጀል ህግ አንቀጽ 240/3 እና 690(1ለ) ስር ተከሰዉ ክርክር ሲደረግ ከቆየ በኋላ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን 17/07/2013 ዓ.ም. በዋለዉ ችሎት የጥፋተኝነት ዉሳኔ በመስጠት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኋላ እንደ ወንጀል ተሳትፎአቸው፡-2ኛ ተከሳሽ (ሀቢብ በሪሶ) በ 20/ሀያ/ ዓመት ጽኑ እስራት ፣ 5ኛ ተከሳሽ (አማን አቤ) በ 22/ሀያ ሁለት/ ዓመት ጽኑ እስራት፤ 6ኛ ተከሳሽ (ሙስጠፋ ዋሪሶ) በ 20/ሀያ/ ዓመት ጽኑ እስራት 8ኛ ተከሳሽ (ሮባ ኤዳኦ) በ 18 /አስራ ስምንት/ ዓመት ጽኑ እስራት ፤ 7ኛ ተከሳሽ (ሮባ አማን) እና 14ኛ ተከሳሽ (ከድር ራበቶ) በወንጀል ህግ አንቀጽ 488/1 እና 690/1ለ ስር እያንዳንዳቸዉ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራት እና 1000 ብር የገንዘብ መቀጮ፣ 16ኛ ተከሳሽ (አለሙ ነጋሽ) እና 17ኛ ተከሳሽ (ሚኪ ጉዬ) በወ/ህግ አንቀጽ 488/1 / እና 690/1ለ/ ስር እያንዳንዳቸዉ በ 2 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ መሰጠቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡

በምስክርነት በመሳተፍ ለፍትህ ስርዓቱ ጉልህ ሚናችሁን ላበረከታችሁ ሁሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ ምንጭ አቃቤ ህግ


Exit mobile version