Site icon ETHIO12.COM

የወንጀል ተካፋይ የሆነን ሰው ምስክር አድርጎ ከክስ ነፃ ስለማድረግ

1ከክስ ነፃ የማድረግ ምንነትና አይነት

ከክስ ነፃ ማድረግ ማለት ከቃሉ መረዳት እንደሚቻለው በህግ ከሚጣል ግዴታ፣ ከመከሰስ ወይም ከቅጣት ነፃ ለማድረግ የሚወሰን ውሳኔ ነው፡፡ ከክስ ነፃ ማድረግ የተለያየ አይነት ያለው ሲሆን ምስክርን ከክስ ነፃ ማድረግ፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመንግስት ሀላፊዎችን ከክስ ነፃ ማድረግ፣ የሉዓላዊነት ነፃነት እና የዲፕሎማሲ ነፃነት ሊሆን ይችላል፡፡

2. ምስክርን ከክስ ነፃ ማድረግና ዓላማው

በወንጀም ፍትህ አስተዳደር በውንጀል የተሳተፈን ሰው ከክስ ነፃ በማድረግ እንደ ምስክር መጠቀም በተለያዩ ሀገራት ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር ነው፡፡ ይህ አሰራር ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የሚጠረጠር ሰው በጉዳዩ ዙሪያ ጠቃሚ ማስረጃ የሚሰጥና ለምርመራና ክስ ስራ ውጤታማነት ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ከክሱ ነፃተደርጎ የምስክርነት ቃል እንዲሰጥ የሚደረግበት ነው፡፡ አንድ ሰው ከክስ ነፃ የሚደረገው ከእሱ ለሚገኘው ማስረጃ/ምስክርነት ለውጥ ተደርጎ ነው ማለት ነው፡፡

በወንጀል ተካፋይ የሆነውን ምስክር ከክስ ነፃ ማድረግ ሁለት አይነት አለው፡ ግለሰቡ ምስክር ከሚሆንበት ወንጀል ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ አንዱ ሲሆን ግለሰቡ የሚሰጠው ማስረጃ/ምስክርነት ቃል በእሱ ላይ እንደማስረጃ እንዳይቀርብ ብቻ ማድረግ ሁለተኛው ነው፡፡ከክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው በወንጀል ድርጊቱ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ የሆነውን ሰው ነፃ በማድረግና ምስክርነቱን በመጠቀም ከባድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራን ውጤታማና ቀላል ማድረግን ዓላማ በማድረግ ነው፡፡ አሰራሩ ከባድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረግ የህዝብን ጥቅም የማስከበር እና የምስክሩን ጥቅም ለማጣጣም የተዘረጋ ነው፡፡ይህ አሰራር ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውጤታማነት የሚያበረክተው ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል፣ ምስክሩ በተጽዕኖ የተሳሳተ ማስረጃ እንዳይሰጥ በጥንቃቄ እና በልዩ ሁኔታ አስፈላጊው መስፈርት ሲሟላ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል ይመከራል፡፡ ለአብነት ነፃ የተደረገው ሰው የሚሰጠው ማስረጃ በሌሎች ማስረጃዎች እንዲደገፍ እና የሚሰጠው ምስክርነት ትክክለኛነቱ የመስቀለኛ ጥያቄ በመሳሰሉ ስልቶች እንዲረጋገጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

3. ምስክርን ከክስ ነፃ የማድረግ ቅድመ ሁኔታ

በወንጀል የተሳተፈን ሰው ከክስ ነፃ ማድረግ እና እንደ ምስክር መጠቀም በተለያዩ ሀገራት የተለያየ አሰራር ያለው ሲሆን በሀገራት የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችም ይለያያሉ፡፡ በዚህ መሰረት በአንዳንድ ሀገራት ከክስ ነፃ የሚደረገው ሰው ምስክር የሚሆንበት ጉዳይ እና እሱ ነፃ የሚሆንበት የወንጀል ጉዳይ ግንኙነት ያላቸው መሆን ይገቧል፡፡ በተጨማሪም ከክስ ነፃ ለማድረግ የጉዳዮቹ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ነፃ የሚደረገው ሰው የሚሰጠው ማስረጃ/ምስክርነት ክብደትም ከግምት ይገባል፡፡ ይህ ማለት ነፃ የሚደረገው ሰው የሚሰጠው ምስክርነት ለጉዳዩ ውጤታማነት ወሳኝና ጠቃሚ ማስረጃ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡በሌላ በኩል የተወሰኑት ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከወንጀል ክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ የተደረገውን ሰው ከፍትሐብሔር ተጠያቂነት አያድነውም ወይም በፍትሐብሔር ክስ ሊቀርብበት ይችላል፡፡በአጠቃላይ የብዙ ሀገራት የህግ ማዕቀፍ እንደሚያሳየው ምስክርን ከክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው ግለሰቡ ምስክር የሚሆንበት ወንጀል ከባድነት፣ የምስክርነቱ ጠቃሚነትና ቅቡልነት እንዲሁም ግለሰቡ በወንጀሉ ያለው ተሳትፎና ምስክር የሚሆንባቸው ሰዎች ያላቸው ተሳትፎ እንደ መመዘኛ ተወስዶ ነው፡፡

4. ከክስ ነፃ ማድረግ በኢትዮጵያበሀገራችን

በተለይ በሙስና ወንጀል ጉዳዮች የወንጀል ተሳትፎው አነስተኛ የሆነን ሰው ከክስ ነፃ ማድረግና በሌሎች ላይ ማስረጃ እንዲሆን ማድረግ የተለመደ አሰራር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሀገራችን የህግ ማዕቀፍ ሲታይ በተለያዩ የህግ ሰነዶች እውቅና የተሰጠው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አሰራር እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡በ2003 ዓ.ም የወጣው የሀገራችን የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ ለወንጀል ተግባር በተቋቋሙ ቡድኖች፣ በረቀቁ ዘዴዎች ወይም በትጥቅ በታገዘ ወይም በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት አመፅ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፈ ሰው ሌሎች ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት እና ለምርመራና ክስ ስራው ውጤታማነት ጠቀሜታ ያለው ማስረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ከሆነ በዐቃቤ ህግ ውሳኔ ተጠያቂነቱ ዝቅ የሚልበት ወይም በሙሉ የሚቀርበት አሰራር በህግ እንደሚወሰን ያስቀምጣል፡፡

ይህ አሰራር ተግባራዊ የሚደረገው እንደ ሙስና፣ ሸብርተኝነት ወይም ወንጀሉ ውስብስ ሆኖ የተጠርጣሪውን ትብብር ማግኘት አስፈላጊ በሚሆንበት ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል ፖሊሲው ያመላክታል፡፡በሌላ በኩል የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 በወንጀል ተካፋይ የሆነ ሰው ስለተፈፀመው ድርጊት ጠቃሚ ማስረጃ ከሰጠ ከክስ ነፃ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀፅ 4 (1) ላይ አንድ ሰው መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ ነፃነት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ማንሳት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡በአጠቃላይ ከላይ ከተጠቀሱት የሀገራችን ህግ ማዕቀፎች መረዳት የሚቻለው አሰራሩ ተግባራዊ የሚደረገው ከባድና ውስብስብ በሆኑና የተከሳሹን ትብብር በሚፈልጉ ወንጀሎች፣ በግለሰቡ የሚሰጠው ማስረጃ ለምርመራውና ክስ ስራው ውጤታማነት ጠቃሚ ከሆነ እና ግለሰቡ ማስረጃ/ምስክርነት ከሰጠ እንደሆነ ነው፡፡

FDRE Attorney General የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ


Exit mobile version