በአንድ የወንጀል ክስ በተለይ የዋስ መብት በሚከለክል ክስ ላይ ዐቃቤ ሕግ (መንግስት) ሊገፋበት ከፈለገ ሒደቱ መፋጠን አለበት። ጊዜ የሚወስድ ከሆነ ፍ/ቤት የዋስ መብትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት። ዐቃቤ ሕግ ሁሌም ባይሆን ብዙ ጊዜ የዋስ መብት በማያሰጥ አንቀፅ የመክሰስ አዝማሚያ ይታይበታል። በክፋት ብቻም አንተርጉመው።

ማስረጃው ሲመረመር ወንጀሉ ከፍ ብሎ ቢገኝ ፍርድ ቤት ከፍ አድርጎ የመቅጣት መብት ስለሌለው ነው። ለምሳሌ ዐቃቤ ሕግ በተራ አገዳደል ከሶ ማስረጃው ግን በነውረኝነት በቂም በቀል በአንደኛ ደረጃ የተፈፀመ ግድያ መሆኑን ቢያረጋግጥም ፍርድ ቤቱ አንቀፁን የመለወጥ እና ቅጣቱን እና አንቀፁን ከፍ የማድረግ ስልጣን የለውም። ፍርድ ቤት በቂና ህጋዊ ምክንያት ሲቀርብለት ዝቅ የማድረግ ስልጣን ብቻ ነው ያለው። ዐቃቤ ሕግ ሆነህ ስታስበው ችግራቸው ይገባሀል።

ይህም ሆኖ ጉዳዩን በደንብ ካጠኑት ሊሰጉም አይገባም። ያም ሆኖ ቻርጁ ላይ በተጠርጣሪው ወይም በጠበቃው ተቃውሞ ሲቀርብ ፍርድ ቤቱ በጥልቀት ከመረመረው ዐቃቤ ሕግ ሁልጊዜ በከባዱ ወንጀል ስለሚከስ እንጂ ማስረጃው በተጠቀሰው አንቀፅ የማይደገፍ ሆኖ ሲያገኘው ፍርድ ቤት በማናቸውም ጊዜ ብቸኛ ስራው ፍትህ መስጠት ስለሆነ አንቀፁን ለውጦ ክሱን ዝቅ የማድረግ ስልጣኑን ሊጠቀምበት ይገባል። አንቀፁ ሲለወጥ ተከሳሹ የዋስ መብት ሊያገኝ ይችል ይሆናል። ምን ያህል የወንጀል ዳኞች ይሄ ስልጣን እንዳላቸው እንደሚያውቁም እላውቅም።

የፍርድ ሂደት በተንዛዛ እና በተራዘመ ቁጥር ማለትም አንድን ተጠርጣሪ በቀጠሮ በእስር ማቆየት Pre trial detention ከፍርድ በፊት ቅጣት ነው ። ይህ ሰው ነፃ ቢወጣ በእስር ለቆየበት ማነው የሚጠየቀው? ወያኔ በቀይ ሽብር ክስ በስመ ሞግሼ አራት ነው ስድስት ዓመት አንድን ሰው ማሰሯ ትዝ ይለኛል። ያውም ሰውየው በየቀጠሮው እየቀረበ የተከበረው ፍርድ ቤት እኔ የቀበሌ ተመራጭ ሆኜ አላውቅም፣ በዚህ ቀበሌም ኖሬ አላውቅም በማለት አቤት እያለ ነው ያን ሁሉ ዓመት የታሰረው። ፈረንጅ ሀገር ቢሆን ሚልየኖች ዶላር ይከፈለዋል። ባያካክስም ሙልጭ አይወጣም።

እኛ ሀገር ወደ ስራውም እንኳን አይመለስም፣ ቤተሰብ ተበትኖ፣ ልጆች ተርበው፣ ትዳር ፈርሶ ሊጠብቀው ሁሉ ይችላል። ምንም ጊዜ ለክስ ደጋፊ ማስረጃ ካለ የተፋጠነ የፍርድ ሒደት ግድ ይላል። በተለይ ተጠርጣሪው የዋስ መብት ተከልክሎ እስር ላይ ሆኖ የሚከራከር ከሆነ የሴኩቱሬን Phrase ልጠቀምና በመብረቃዊ ፍጥነት Lightening speed ባይሆንም የተቻለው ሁሉ ተደርጎ በፍጥነት እልባት ሊሰጠው ይገባል።
አንድ ፍርድ በአራት ቦታ ይታያል፣ ፍርድም ያገኛል። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው:-

  1. Court of law ፍርድ ቤቶች
  2. Court of public opinion ህዝብም ይፈርዳል
  3. የታሪክ ፍርድ። ታሪክም ይፈርዳል
  4. የእግዚአብሔር ፍርድ
    አፄ ኃይለስላሴ ጥልያን ወረረችን ብለው ለሊግ ኦፍ ኔሽን አቤት ሲሉ ሰሚ በማጣታቸው፣ ስለተሾፈባቸው፣ በፉጨት ስለረበሿቸው

“ይቺ አሁን የምትሰሯት ግፍ ታሪክ እና እግዚአብሔር ያስታውሷታል”

ያሉት ይሄው እውነት ሆኖ እስካሁን ይጠቀሳል።
ዳኞች በተራ ቁጥር 1 ላይ ናቸው። ግና ህዝብ፣ ታሪክ እና እግዚአብሔርም የዳኞችን ፍርዳቸውን ምንጥር አድርጎ እንደሚመረምረው አውቀው ለሕሊናቸው ብቻ መታዘዝ አለባቸው። አፄ ኃይለስላሴ እንዳሉትም ሐይማኖተኛ ከሆንክ ከሀይማኖት አኳያም ካየኸው እግዚአብሔርም ይፈርዳል።

የወያኔ እንዲህ መዝረክረክ የእግዜር ፍርድ መሆን አለበት። እግዜርን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመርያ ነው ይላል መፅሀፋችን። ዳኞች እግዜርንም ሊፈሩ ይገባል። በቁርአንም በሌላውም ቅዱሳን መፅሀፍ ይሄው ነው።

ወደተነሳንበት ስንመለስ አንድን ተጠርጣሪ አስሮ፣ ዐቃቤ ሕግ የዋስ መብት በሚከለክል አንቀፅ እንዲከስ ተደርጎ በቀጠሮ አስሮ ማቆየት ኢፍትሐዊ ነው። ወያኔ ያላግባብ አስራ በጎን ማረኝ ብላችሁ ማመልከቻ ፃፉ ብላ የይቅርታ ማመልከቻ ፎርም አዘጋጅታ በየእስር ቤቱ ታዞር ነበር። ይሄ ቀሽም ትያትር አሁን መቅረት አለበት። ፍርድ ቤቶች ነፃ ሆነው ከተጠርጣሪም ሆነ ከዐቃቤ ሕግ (መንግስት) ሳይወግኑ ለሕግ እና ለህሊናቸው ብቻ ታዛዥ ሆነው በነፃነት ሊሰሩ ይገባል። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ብቻ ነች ወያኔን (ዐቃቤ ሕጉን) ወጊድ ማስረጃ የለህም ብላ ስዬን የለቀቀችው። ከብርቱካን ሌላ ማንም ዳኛ ይሄን የማድረግ ወኔ አላሳየም። አሁን ትናንትና ኬርያ እንኳን የተለቀቀችው ዐቃቤ ሕግ ፈቅዶ ፣ ትለቀቅ ብሎ ለፍርድ ቤት አመልክቶ ነው።
ዳኞች ለሕግ እና ለሕሊናቸው ብቻ ታዛዥ የሚሆኑበት ጊዜ ይናፍቀኛል
ቸር ይግጠመን

Via – Guangul Teshager J

Leave a Reply