Site icon ETHIO12.COM

ʺጌታውን መስሏልና ሐይቁን በድንጋይ ታንኳ ተሻገረው”

የሚመስሉትን ፀጋውን ያለብሳቸዋል፣ ይመስላቸዋል፣ የማይመስሉትን ደግሞ ይቀጣቸዋል፤ ምድር ለሰው ልጅ ተሰጠች፤ ሰውም በምድር ላይ ነገሰ፡፡ ምድርን የሰጣቸውን እንዲያስቡና እንዲያከብሩም ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡ ሕጉን የጠበቀ ሁሉ ምድርን ይገዛል፤ የሚገዛት ምድርም ትጠበቅለታለች፡፡ ሕጉን ያልጠበቀ ሁሉ መከራው ይፀናበታል፡፡

የሰማይ ዓይኖች ምድርን ተመለከቷት፡፡ ምድርም በሐጥያት አድፋለች፡፡ ሕዝቡ ሁሉ በአላፊ ነገር ተጠምዷል፡፡ አንዲት ምድር ግን በሕግና በስርዓት የምትመራ ሆና ተመለከቷት፡፡ ደስ ተሰኘ፡፡ ያቺን ምድርም ጠበቃት፡፡ ለምን ቢሉ በዚያች ምድር እርሱን የመሰሉ አይቷልና፡፡ እርሱን የሚመስሉትም መነሳታቸውን አያቋርጡም እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ይቀጥላሉ፡፡ ሰማይና ምድር ሳይኖሩ፣ ምንም ምንም ሳይፈጠር፣ የት እንደሚኖር፣ ከየት ጀምሮ እስከ መቼ እንደሚኖር የማይመረመር ጌታ ይኖር ነበር፡፡ ዓለም ሳይፈጠር ነበረ፣ ዓለምን ፈጥሮ ኖረ፣ ዓለምን አሳልፎ ይኖራል፡፡

ጌታ ደስ ብሎት የተመለከታት፣ አስቀድሞ የመረጣት፣ በኋላኛው ዘመንም ለምስከር ትሆን ዘንድ ያስቀመጣት፣ በሰማይ ሠራዊቶቹ የሚያስጠብቃት፣ በቅዱስ መንፈሱ የከለላት ምድር፤ ይህችም ምድር ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚች ምድር አያሌ ነገሥታት እየተነሱ አለፉ፡፡ ቅዱሳን አባቶችም እንዲሁ እየተነሱ የፅድቅን ሥራ እየሰሩ አላፊውን ዓለም ጥለው ወደ ማያልፈው አቀኑ፡፡ ሞትን እስከ ዘመነ ምፅዓት እንዳይቀምሱ የተፈቀደላቸው ደግሞ ከምድራዊ ዓለም ተሠወሩ፡፡ ዘመን ጨመረ፣ ዓመት ተቆጠረ፡፡ የቀደመው ዘመን አልፎ ሌላ ዘመን መጣ፡፡

በኢትዮጵያ ይነግሡ ዘንድ አምደ ፅዮን ተራቸው ደርሷል፡፡ አምደፅዮንም ነገሡ፡፡ በኃያሉ ዙፋን የተቀመጡት ንጉሥ በጥበብና በፀሎት እየተመሩ በሀገራቸው አያሌ ነገሮችን አደረጉ፡፡ መንግሥትን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረው የያዙ ነበሩና በዘመናቸው መልካም ነገሮችን አደረጉ፡፡ ንጉሥ አምድፅዮን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የከበረ ቦታ አላቸው፡፡ እኒህ ንጉሥ አስቀድሞ ለቅድስና የተዘጋጄ አንድ ልጅ ነበራቸው፡፡ ይህም ልጅ በልቡ መልካም ነገርን ይሻል፡፡ አሥተዳደጉ በቤተ መንግሥት ነውና የቤተመንግሥት ባለሟሎች ምድራዊ ንጉሥ ይሆን ዘንድ አጭተውታል፡፡ በሰማይ ደግሞ ለሌላ ቅድስና ታጭቷል፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩ ቅዱሳን መነኮሳት ወደ ቤተመንግሥት ይሄዱ ነበር፡፡ በቤተ መንግሥት በሄዱም ጊዜ ከንጉሱ ልጅ ጋር ይገናኙ ነበር፡፡ የንጉሡ ልጅም ስማቸው ያሳይ ነው፡ ያሳይም ከመነኮሳቱ በሚሰሙት ነገር ይደነቁ ነበር፡፡ ልባቸውም በቃሉ ፍቅር ተነደፈች፡፡

“አቤቱ ቃሌን አድምጥ፣ ጩኸቴንም አስተውል፣ የልመናዬን ቃል አድምጥ፣ ንጉሤና አምላኬ ሆይ አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለሁ፡፡ በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፡፡ በማለዳ በፊትህ እቆማሁ፤ እጠብቃለሁም፡፡ አንተ በደልን የማትወድ አምላክ ነህና ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም፡፡ በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፡፡ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ፡፡ ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፡፡ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል፡፡ እኔ ግን በምኅረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፡፡ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ፡፡ አቤቱ ስለ ጠላቶቼ በጽድቅህ ምራኝ፡፡ መንገዴን በፊትህ አቅና” እንዳለ መጻሕፍ በማለዳው የተመረጡት ቅዱስ ሰው መንገዳቸው ይቀና ዘንድ ፈጣሪያቸውን ለመኑ፡፡

መነኮሳቱ ስለገዳማዊ ሕይወት የነገሯቸውን በዓይናቸው ያዩት ዘንድ ይኖሩትም ዘንድ ሻቱ፡፡ ጌታም ልባቸው የሻተውን ይፈፅምላቸው ዘንድ አጥብቀው ለመኑ ተሳካላቸውም፡፡ የንጉሡ ልጅ የምድር ንግሥና ለሚሹት የእኔ መሻት ግን በመሳይ ነው ብለው ከቤተ መንግሥት ወጡ፡፡ የምድራዊውን ዙፋን ይወርሱ ዘንድ የታሰቡት ቅዱስ ሰው ከአላፊው መንግሥት ዘላላማዊው ይሻለኛል አሉ፤ግሩምም ተባለ፡፡ ምን አይነት መታደል ነው፡፡ ከሞቀ ቤት፣ ከሞላ ድሎት ወጥቶ ጤዛ እየላሱ፣ ቁር እየታገሱ፣ ድንጋይ እየተንተራሱ መሄድን የሚመኝ ማን አለና፤ እሳቸው ተድላና ደስታ የመላበት ቤተ-መንግሥት አላስቀናቸውም፡፡ አልይህ ብለው ወጡ፡፡ በቤ-ተመንግሥት እያሉም ቃለ እግዚአብሔርን ተምረው ነበርና መንገዳቸውን የቀና አደረገው፡፡

ʺሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነብሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል ? ወይስ ሰው ስለ ነብሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” እንዳለ ነብሳቸውን ለመሙላት ጽድቅን መረጡ፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ደረሰ፡፡ የአባታቸውን ዙፋን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ንቀውት እየዘመሩ ስለተጓዙ ʺመናኔ መንግሥት” ይባላሉ፡፡ ወደ ደብረ መንኮል ደብረ እግዚ ሄዱ፡፡

በዚያ ገዳምም አቡነ መድኃኒነ እግዚእ የሚባሉ ቅዱስ አባት ነበሩ፡፡ አቡነ ያሳይ የእግዚአብሔር ጸጋ ያደረባቸው ሰው መሆናቸውንና ወደ እርሳቸውም እየመጡ መሆኑን በመንፈስ ዐውቀውት ስለነበር በደስታ ተቀበሏቸው፡፡ በረዳትነት ከወንድሞቻቸው ጋር ጨመሯቸው፡፡ አቡነ ያሳይም የገዳም መነኮሳትን በማገልገል በመንፈሳዊ ተጋድሎ ብዙ ደከሙ፡፡ በደብረ መንኮል ገዳምም ተአምራትን አደረጉ፡፡

ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር መልአኩን ወደ ገዳሙ ላከ፡፡ መካነ ገድላቸው በጣና ሐይቅ አካባቢ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ʺወላዴ አእላፍ ቅዱሳን” የሚባሉት አቡነ መድኃኒነ እግዚእም የሃይማኖት ምግባራቸውን፥ የተጋድሎ ትሩፋታቸውንና የሠሩትን ተአምር አይተው፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቀው በአንድ አመነኮሷቸው፡፡ የመነኮሱት ቅዱሳንም ሰባት ነበሩ፡፡ በአመነኮሷቸው ጊዜም መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን መላው፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰማ፡፡ ብርሃን በከዋከብት አምሳል ወጥቶ ነበርና ʺሰባቱ ከዋክብት” ተባሉ ይላሉ አበው፡፡ በዚያ ገዳም የነበራቸው አገልግሎት ተጠናቀቀ፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር ከገዳሙ ወጡ፡

አቡነ ያሳይ ከቅዱሳን ጋር ሲመጡ በመንገድም አንድ ወጣት እሸት ሲጠብቅ አገኙት፣ እባክህን እሸት አብላን አሉት፡፡ እሸቱ አልደረሰም እንጂ ብሰጣችሁ በወደድኩ ነበር አለ፡፡ አቡነ ያሳይም የወጣቱን የልብ ቅንነት አይተው እሸቱን ባረኩት፡፡ እሸቱም ለመብል ደረሰ፡፡ ከእሸቱም በሉ፡፡ ውሃም ስጠን አሉት፡፡ አባቶቼ የውሃው መገኛ ራቅ ይላል አላቸው፡፡ ሊያመጣም የውሃ መቅጃውን ይዞ ተነሳ፡፡ ቅንነቱንም አዩ፡፡ ቆይ አትሂድ አሉት፡፡ አለቱንም ባረኩት ውሃ ፈለቀ፡፡ በዚያ ዘመን ባርከው ያፈለቁት ውሃም ዛሬ ድረስ ፀበል ሆኖ ያገለግላል ይላሉ አበው፡፡

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባና አቡነ ያሳይ በጣና ዳርቻ በዋሻ ውስጥ ሆነው መፀለይ ጀመሩ፡፡ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ 12 ዓመታትም በዚያው ፀኑ፡፡ በዚያ ስፍራም በሰርክ ፀሎት ያደርሱ ነበር፡፡ ስለ ዓለም ሀጥያት ምድር እንዳትጠፋ አብዝተው ይማፀኑ ነበር፣ በረከት በምድርና በሰው ልጅ ይበዛ ዘንድም ይማፀኑ ነበር፡፡ በዚያ ስፍራም የእግዚአብሔር መንፈስ ወረደ፡፡ ጌታም አቡነ ሳሙኤልን ʺይህስ ቦታ የወዳጄና የወዳጅህ የአቡነ ያሳይ ቦታ ነው፡፡ የአባቱን ዙፋን ንቆ ወደ እኔ መጥቷልና፡፡ አንተም ወደ አዘጋጀውልህ ቦታ ሂድ አለ” አቡነ ሳሙኤልም ወደ ገዳመ ዋሊ ዋልድባ ሔዱ፡፡ ያ ቦታ ለእሳቸው የተመረጠ ነበርና፡፡

ጌታ የቅድስና ዘመናቸውን አይቶ ገዳም ይገድሙ ዘንድ ፈቀደላቸው፡፡ ታቦትም ይሰጣቸው ዘንድ ወደደ፡፡ ታቦተ መድኃኒዓለምን ከንጉሡ እጅ ተቀብለው መጡ፡፡ ቤተ መቅደሱን ያንፁ ዘንድም አዘዛቸው፡፡ በእግዚአብሔር ረዳትነት በእሳቸው የማይሰለች ፀሎት ቤተ መቅደሱን አነፁ፡፡ የማን እንደ አባ አቡነ ያሳይ መድኃኒዓለም አንድነት ገዳም አፈ መምህር አባ ሀብተ ማርያም እንደነገሩኝ ታቦተ መድኃኒዓለምን ከንጉሡ ዘንድ ተቀበሉ፡፡ በየብሡ አድርገው የእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አረፈበት ሥፍራ ለመሄድ ከሐይቁ ደረሱ፡፡ ከእሳቸው ጋር ሲሄዱ የነበሩ ሰዎችም እርስዎ ለእግዚአብሔር ቅርብ ነኝ ይላሉ እስኪ እንደ ሙሴ ባሕርን ከፍለው ይሻገሩ፡፡ ወይንም ደመና ጠቅሰው ይሂዱ ይሏቸው ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ያሳይ በቀና ልባቸው ፀለዩ፡፡ ጌታም ‹‹ወዳጄ ያሳይ ሆይ አትጨነቅ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ከጎንህ ያለውን ድንጋይ በባሕሩ ላይ ጫነው፤ ድንጋዩም ለልጅ ልጅ እኔ ዓለምን ለማሳለፍ እስከምመጣበት ሰዓት ድረስ መታሰቢያ ትሁንህ›› አላቸው፡፡ ልጆቼስ (ተከታዮቼ) በምን ይሻገራሉ አሉ፤ እነርሱስ በመጎናፀፊያቸው ይሻገራሉ አላቸው፡፡ በሙሉ እምነት የተባሉትን አደረጉ፡፡ አቡነ ያሳይም የመድኀኒዓለምን ጽላት ይዘው በድንጋዩ ላይ እንደተቀመጡ ድንጋዩ እንደታንኳ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ፡፡ ባሕሩም ከማዕበሉ ብዛት የተነሣ ይታወክ ነበር፡፡ እሳቸውም ያለ ምንም ቀዘፋ ልብሳቸውም ውኃ ሳይነካው ፈቃደ እግዚአብሔር ባረፈበት ቦታ ደረሱ፡፡

በዚያም ጊዜ ʺባሕርን በድንጋይ የተሻገረ ማን እንደ አባ ያሳይ ” ተባለ፡፡ የገዳሙ ስምም ማን እንደ አባ ተባለ፡፡ ቤተ መቅደስ አነፁ፡፡ ታቦተ መድኃኒዓለምን አስገቡ፡፡ ገዳምም ገደሙ፡፡ እሳቸው የተሻገሩባት የድንጋይ ታንኳም ዛሬ ድረስ በገዳሙ ትገኛለች፡፡

ቅዱስ መንፈስ በዚያ ስፍራ አለ፡፡ አዕዋፋት ይዘምራሉ፡፡ ሐይቁ በማዕበል ይወዛዋዛል፡፡ ዛፎች ለጌታቸው ምስጋና የሚያቀርቡ ይመስላሉ፡፡ ጎንበስ ቀና ሲሉ አጀብ ያሰኛሉ፡፡ አበው መነኮሳት ስጋዬን ለመነኩሴ ነብሴንም ለስላሴ ብለው ሳያርፉ ለአገልግሎት ይፋጠናሉ፡፡ ስጋቸውን እያስራቡ ነብሳቸውን ይመግባሉ፡፡ ስለ ዓለም ሀጥያት፣ ስለ ምድር በረከት፣ ስለ ኢትዮጵያ ፅናት፣ ስለ ሕዝቦቿ አንድነት ሳይሰለቹ ይማፀናሉ፡፡ ከሚታዩት መነኮሳት በላይ በምንኩስና የዘጉ መነኮሳትም በዚያ ገዳም ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ስለ ምድራዊ ዓለም ይማፀናሉ እንጂ ዓለምን ማዬት አይሹም፡፡ ይህ ታምረኛ ገዳም በ1326 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡ ገዳሙ በጎንደር በደንቢያ ምድር ከጎርጎራ በስተ ምዕራብ በቅርብ ርቀት ይገኛል፡፡ በየብስም በሐይቅም መሄድ ይቻላል ለሁሉም የተመቻቸ ውብ ሥፍራ ነው፡፡

በዚያ ዘመን እንድ ትምሕርት የሌላቸው ነገር ግን ልባቸው ንፁሕ የሆነ ሰው ነበሩ፡፡ እኒያ ሰውም ወደ ገዳምም መግባት ፈለጉ፡፡ ወደ ገዳም በሚሄዱበት ጊዜም ሰዎች መንገድ ላይ አገኟቸው፡፡ የት እየሄዱ እንደሆነ ጠየቋቸው፤ ወደገዳም እንደሚሄዱም ነገሯቸው፡፡ ገዳምስ በዚሕ በቅርብ አለ አሏቸው፡፡ ድንቅ ነው ነገር ግን ትምሕርት የለኝምና ምን ብዬ ጌታዬን ልለምን እያሉ ያስቡ ነበር፡፡ በሰው የተመሰለ ሰይጣንም ʺአትማረኝ አትማረኝ” እያልክ ፀልይ አሏቸው፡፡ የተባሉትን እያደረጉ ዘመናትን አሳለፉ፡፡ ለ40 ዓመታትም በዋሻ ውስጥ ተቀመጡ፡፡
ከዘመናት በኋላ አቡነ ያሳይ አማኞችን ሲያስተምሩ ቆይተው በድንጋይ ታንኳቸው ሲመለሱ እኒያን አባት ʺአትማረኝ አትማረኝ ” እያሉ ሲጸልዩ ይሰሟቸዋል፡፡ ወደ ዋሻውም ቀረቡ፡፡

አቡነ ያሳይም በሰውዬው ጸሎት በመገረም ቀርበዋቸው ʺአባቴ ምን ዓይነት ጸሎት ነው የሚጸልዩት?” አሏቸው፡፡ እኒያም አባት ʺአባቴ እንደ እርስዎ ያሉ አባት መጥተው ‹አትማረኝ› እያልክ ጸልይ ብለውኝ ነው” አሏቸው፡፡ አቡነ ያሳይም ʺእንዲህ ዓይነት ምክር የሚመክር ጠላት ዲያብሎስ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምረው ‹ማረኝ› እያሉ ይጸልዩ “አሏቸው፡፡ ቃለ እግዚአብሔርንም አስተማሯቸው፡፡ ነግረዋቸው ሲጨርሱም በድንጋይ ታንኳቸው ወደ ባዕታቸው አቀኑ፡፡ ʺአትማረኝ” እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባትም ʺማረኝ” እያሉ መጸለይ ጀመሩ፡፡ ጥቂት እንደ ጸለዩም ጠፋባቸው፡፡ አቡነ ያሳይ ሳያመልጧቸው ድጋሜ ይነግሯቸው ዘንድ ሊጠይቁ ሲመለከቱ አቡነ ያሳይ በሐይቅ ላይ በድንጋይ ታንኳ እየሄዱ ተመለከቷቸው፡፡

አዲሱን ጸሎት መልሰው ያስጠኗቸው ዘንድ አቡነ ያሳይ ርቀው ሳይሄዱባቸው እኒያ አባት በውኃ ላይ በእግራቸው እየተራመዱ በመከተል ይደርሱባቸዋል፡፡ ከኋላቸውም ሆነው ʺአባታችን ጸሎቱ ጠፋብኝ፤ እባክዎን እንደገና ያስተምሩኝ” አሏቸው፡፡ አቡነ ያሳይም፤ ሐይቁን በእግራቸው እየረገጡ ሳይሰጥሙ ሲሄዱ አይተው ተደነቁ፡፡ መብቃታቸውንም ተመለከቱ፡፡ ʺአባቴ እግዚአብሔር የሚመለከተው የልብ ነውና እንዳስለመዱት ይጸልዩ የእርስዎ ይበልጣል፤ ከአፍ ልብ ይቀድማል” አሏቸው፡፡ እኒያ አባትም በቀደመ ፀሎታቸው ቀጠሉ፡፡ ልባቸው መዳንን ይመኝ ነበርና ጻድቅ ሆኑ፡፡ በቅድስናም በዚያው ገዳም አረፉ፡፡ እኒያ አባት ጸሎት ያደረሱበት ሥፍራ ዛሬም በማን እንደ አባ አቡነ ያሳይ መድኃኒዓለም አንድነት ገዳም ይገኛል፡፡ ስሙም አትማረኝ ዋሻ ይሰኛል፡፡

ገዳሙን ንጉሡ ፋሲል አድሰው ሰርተውታል፡፡ ከእሳቸው ዘመን በኋላም በተለያዬ ጊዜ እድሳት ተደርጎለታል፡፡ ጌታ ገዳሙን እንደ ኢየሩሳሌም አደርግልሃለሁ፡፡ ውሃውንም እንደ ዮርዳኖስ ይሆንልሃል ብሎታልና ቃል ኪዳኑ አለበት ይላሉ አበው፡፡ በመጋቢት 27 ቀንም ይከብራል፡፡ በገዳሙ የኢቴጌ ምንትዋብና የባለቤታቸው የአፄ በካፋ የሥጦታ ዕቃዎች፣ የብራና መጻሕፍት፣ ያልታዩና ያልተመረመሩ አያሌ ቅዱሳት ቅርሶች እንደሚገኙ አባ ሀብተ ማርያም ነግረውኛል፡፡ ገዳሙ በውስጡ የሚገኙ ታረካዊና መንፈሳዊ ቅርሶችን በክብር የሚያስቀምጥበት ዘመና ቤተ መዘክር እንደሚያስፈልገውም አፈ መምህሩ ነግረውኛል፡፡

ኢትዮጵያ አቅፋ የያዘቻቸው፣ ጠብቃ ያኖረቻቸው አያሌ ሚስጥራት አሏት፡፡ እነዚያ ሚስጥራትም የዓለም ሚስጥር መፍቻ ቁልፎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ሚስጥር ናት፡፡ ገዳሙን ይዩት፤ ይጎብኙት፣ ይረኩበታል፤ መልካም ነገርም ያገኙበታል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ፎቶ፡ ከድረ ገጽ

Via አብመድ. (አሚኮ)

Exit mobile version