Site icon ETHIO12.COM

ትግል መልኩን እየቀያየረ ይቀጥላል . . .

ከ1997 ጀምሮ የምመኛትን ኢትዮጵያ ለማየት በግልም በድርጅትም ታቅፌ የተቻለኝን ጠጠር ወርውሬያለሁ። ትናንትም ዛሬም ኢትዮጵያ አሸንፋ፤ ያለ ልዩነት ለሁሉም ዜጎቿ የተስፋ ምድር ሆና ከማየት የዘለለ ህልም የለኝም። የፖለቲካ ትግል የማደርገውም ከዚሁ የፀና መሻት የተነሳ ነው!

እነሆ ዛሬ አምርሬ እታገለው የነበረው ህወሓት የለም። በኢትዮጵያ ምድር የረጨው መርዙ ግን ብዙ ትግል ይፈልጋል ብዬ አምናለሁ። በዘመናት ውስጥ ተጠራቅሞ ለኛ የቀረልን ውዝፍ ችግርን ጨምሮ ህወሓት ትቶት የሄደውን አሜኬላ ለቅሞ ወደ ተስፋ የሚደረገውን ጉዞ ቀና ለማድረግ የበዛ ትዕግስት የሚፈልግበት ወቅት ላይ እንዳለን ይሰማኛል። ጊዜው የተለየ ትግል ማድረግ ግድ የሚልበት ነው።

በዚህ ፈታኝ የሽግግር ወቅት በመንግስት አስተዳደር ውስጥ የኢትዮጵያ ብሮድካትስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ላይ መመደቤ፤ ከአፍላነቴ ጀምሬ ላያት የምመኛት ኢትዮጵያ ከተቃውሞ ትግል ባለፈ በፀጋዬ መጠን የተቻለኝን ሰርቼ እውን እንድትሆን የምታገልበት የተለየ እድል እና አዲስ የትግል ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ አምናለሁ።

ወዳጆቼም ሆናችሁ የማትረዱኝ ወገኖቼ እንድታውቁት የምሻው አንድ እውነት አለ – አካሄዱ ይለያይ እንጂ ሁላችንም አላማችን የተሻለ ነገን ማየት ነው ብዬ አምናለሁ። የተሻለች ኢትዮጵያን የማይናፍቅ ኢትዮጵያዊ የለምና። ይህ እውን እንዲሆን ሁሉም ሰው በቀና መንፈስ የየራሱን ጠጠር ቢወረውር እወዳለሁ።

እኔ መንገዴንና ትግሌን የበለጠ ወደ መንግስትና የህዝብ አስተዳደር በመቅረብ ቀጥያለሁ – ሁላችሁም በያላችሁበት አላማችሁን ኢትዮጵያን አድርጋችሁ በጋራ ህልማችንን እውን እንደምናደርግ ተስፋ አለኝ። በረባ ባልረባው እያማረርን አቧራውን ከምናስጨስ የቱንም ያህል ፈተና ቢበዛበትም ሁሉን ተቋቁሞ ትቢያውን መጥረግ ይሻላል። ቆሻሻ ተፀይፎ ከዳር እያዩ እንዲፀዳ መመኘት ዋጋ የለውም – ከስፍራው ዘልቆ በገቢር ማፅዳት ግድ ይላል።

ምስጋና፦ በተለያየ መገናኛ መንገድና ከዚሁ መንደርም በተመደብኩበት ኃላፊነት መልካሙን ሁሉ የተመኛችሁልኝና ምክራችሁን የለገሳችሁኝ ወዳጆቼ ሁሉ ፈጣሪ ያክብርልኝ – አመሰግናለሁ! በተለያየ ምክንያትና ካለመረዳት በመነጨ አሉታዊ አመለካከት ነቀፌታችሁን የሰነዘራችሁ ወገኖቼም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ – ፍፁም አይደለሁምና ድካሜን አይቼ እበረታ ዘንድ አበርክቶታችሁ ቀላል አይደለም! ስለሁሉም ነገር ሁላችሁም ተባረኩ!

በተረፈውስ የፖለቲካ ሀሁ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ላመንኩበት ነገር ወጀቡን እየተጋፋሁ ያለኝን ሁሉ ከመስጠት ተቆጥቤ አላውቅም – ወደፊትም ለሀገሬና ለወገኔ ምንም ሳልሰስት ባለኝ አቅም ሁሉ እንደማገለግል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። #EthiopiaPrevails

መልካም ይሆናል ✌🏾Yonatan TR

”የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል የተሰጠኝን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ̋
አቶ ዮናታን ተስፋዬ የብሮድካሰት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር


(ኢ ፕ ድ)
👉 ሹመቱ መንግስትና ፓርቲም የተለያዩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል፤

የተጀመረውን አገራዊ ለወጥ ለማሰቀጠል የተሰጠኝን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀቱን የብሮድካስት ባለሰልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ አስታወቁ።

ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባላስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ከዳር ይደርስ ዘንድ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመጠቀም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ናቸው።

“አሁን በመንግስት አስተዳደር ላይ የተመደብኩበት ቦታ ላይ ሆኜ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ግቡን እንዲመታ እንደ አንድ አጋዥ ሀይል ራሴን በመቁጠር ሀላፊነቴን በአግባቡ ለመወጣት ተነሰቻለሁ” ብለዋል።

̋ሀገራችን ለወጣቶች ምቹ ጥለናት የማንሰደድባት ሀገር አንድትሆን በተለያየ መንገድ ስታገል ነበር” ያሉት አቶ ዮናታን፤ አሁን የተሰጣቸው ሀላፊነት ከባድና ሌላ የትግል ምእራፍን የሚከፍት መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይ በወጣትነት እድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች በመንግሰት አስተዳደር ውስጥ መካተታቸውና የሪፎርሙ አካል መሆናቸው የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ ከአንድ ፓርቲ ውጭ ያለ አመለካከት ያለውን ሰው መግፋት እስከዛሬ ድረስ ያልጠቀመ አካሄድ በመሆኑ አሁን የተጀመረው አካሄድ የሚያስመሰግንና መንግስትና ፓርቲም የተለያዩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

Exit mobile version