Site icon ETHIO12.COM

ሙስሊሙ ህብረተሰብ የረመዳን ፆምን በፍቅርና በመተጋገዝ እንዲያሳልፍ ተጠየቀ



ሙስሊሙ ህብረተሰብ የ1442 ኛው የረመዳን ፆም ለፈጣሪው በመገዛት፣ በፍቅር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ሊያሳልፈው ይገባል ሲል የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ::

በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለአዲስ አበባ ከተማና ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህዝበ ሙስሊሞች ዛሬ የተጀመረውን የ1442 ኛው የረመዳን ፆም በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል::

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አሊ መሃመድ ሽፋ የረመዳን ፆምን መጀመርን አስመልክተው፤ ረመዳን ወር የእዝነት፣ የፍቅር የአብሮነት የተቀደሰ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልፀዋል:: ችግረኞችን፣ አቅመ ደካሞችን እንዲሁም ወላጅ አልባ ህጻናትን በማገዝና ምጽዋት በመለገስ ህዝበ ሙስሊሙ እንዲያሳልፍም ጥሪ አስተላልፈዋል::

ረመዳን የእዝነትና የራህመት ወር ነው ብለዋል:: በመሆኑም በከተማው የሚገኘው ሙስሊሙ ህብረተሰብ የረመዳን ወርን በኢባዳ፣ በፍቅር ፣ በመረዳዳት እና በመተጋገዝ ሊያሳልፈው እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የፅኑ ህሙማን ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱን አስታውሰው፤ በዚህ በተቀደሰ ወር ውስጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለፀሎት በሚሰባሰብበት ጊዜ የጤና ባለሙያዎች የሚያስተላልፏቸውን ምክሮች በመቀበልና በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል::

በተለያዩ ክልሎች የሚታዩ ማንነትንና ኃይማኖትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች፤ የመፈናቀል፣ ለንብረት መውደም እንዲሁም ለህጻናት፣ ለእናቶችና አዛውንቶች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን አስታውሰው፤ የእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮትና የእምነቱ መሪዎች አጥብቀው እንደሚያወግዙም ተናግረዋል::

ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን በማውገዝ ለህዝቡ መልካም በማሰብና ቅድሚያ በመስጠት ችግሩን በውይይት መፍታት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል::

የህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከውጭ ኃይሎች እየተቃጣ ያለውን ትንኮሳ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በአገራዊ መንፋስ በመቆም ሊያወግዙት ይገባል ብለዋል:: ለጋራ ሀብታቸው በመቆም ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በገንዘብና በተለያዩ ድጋፎች እገዛ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም መክረዋል::

ዘንድሮ ለሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ቅስቀሳም ሰብአዊ መብትን ባከበረ መልኩ በሰላማዊ መንገድ ሊከናወን ይገባል ብለዋል:: ሙስሊሙ ህብረተሰብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ መሪዎችን በመምረጥ አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል::
ገመቹ ከድር

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version