በአማራ ክልል ከሰማኒያ በላይ ሙስሊሞች መገደላቸውን፣ አርባ ሰባት በላይ ሲታገቱ ከአስር ሺህ በላይ መፈናቀላቸውንና 260 ዘረፋዎች መከናወናቸውን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት 1ሺህ 445ኛውን የዒድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ባሰራጨው መግለጫ እንዳለው ይህን ሁሉ መከራ በሙስሊሙ ህዝብ ላይ ያደረሰው ” ጽንፈኛ” የሚባለው ሃይል ነው።
የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ጀውሃር ሙሐመድ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚኖሩ ሙስሊሞች ለ1ሺህ 445ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ ሲሉ አስቀድመው የመልካም ምኞት መልዕክት አድርሰዋል።አያይዘውም ሕዝበ ሙስሊሙ በጽንፈኛ ቡድኑ በሚደርሱ ጥቃቶች ሳይደናገጥ አምርሮ መታገል እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
በባህር ዳር የተካሄደውን የተቃውሞ ስለፍ ተከትሎ በተሰጠው መግለጫ ሙስሊሙ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ባስቸኳይ እንዲቆም ሰላም ወዳድ ዜጎች ሁሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ተማስጽኖ ቀርቧል።
የከፍተኛ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር በታሪክ አሳዛኝ እና ፈታኝ ጥቃት እየተፈጸመ ቢኾንም በአጥፊው ቡድን በደል አንገት መድፋት እንደማይገባ አበክረው ማስታወቃቸውን የአማራ ክልል መገናኛ አመልክቷል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ “አጥፊው ቡድን በጽንፈኝነትን እና ጥላቻ እየተገፋ የማይፈልገውን ሁሉ ጥቃት እያደረሰ ይገኛል” ብለዋል። አክለውም “ለዚህ ማሳያው በወንድሞች ላይ ከመስጊድ በር ሲወጡ የተፈጸመው ጥቃት ይጠቀሳል” ሲሉ ከአንድ ቤት አባትና ልጆችን በድምሩ ራት የቤተሰብ አባላት በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን አመላክተዋል። ይህንን ገዳይ ቡድን ሁሉም ተባብሮ ሕግ ፊት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
በእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳዋ እና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም ለበዓሉ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
ሼህ ሙሐመድ በዓሉን በተለመደው እና ሸሪያው በሚያዘው መንገድ በትዕግስት እንድታከብሩም ሲሉ ነው አሳስበዋል፡፡ መክረዋል። ሁሉም ከስሜት እንዲርቅ አስጠንቀቀዋል።
ሼህ ሙሐመድ “መጥፋት ያለበት አረመኔ ቡድን እንዲጠፋ በሕግ እንታገላለን” በማለት የህግ አግባብ መከተል አስፈላጊ መሆኑንን አስምረውበታል። ሕዝበ ሙስሊሙም 1ሺህ 445ኛውን የዒድ አል ፈጥር በዓል በየትኛውም መስገጃ በአንድ ላይ ኾኖ እና ተመሳሳይ ልብስ ለብሶ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያከብርም አደራ ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ሕዝበ ሙስሊም በዓሉን በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በታላቅ ድምቀት እንደሚያከብርም ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም አስገንዝበዋል፡፡ ምክር ቤቱ በጽሁፍ ያሰራጨው ሙሉ መግለጫ ከስር ያንብቡ።