Site icon ETHIO12.COM

የተማሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የትምህርት ምደባ ስራ ላይ ሊውል ነው



በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የትምህርት ምደባ ስራ ላይ ሊውል እንደሆነ ተጠቆመ፡፡ ከምደባ ወደ ቅበላ የማስጀመር ስራ ለመግባት መታቀዱ ተጠቆመ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ካውንስል ትናንት በተመሰረተበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ ተማሪዎችን የመመደብ ሥርዓቱን በተማሪዎቹ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ የሚያስችሉ ወሳኝ ክንውኖች እየተፈጸሙ ናቸው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንዲሁም ጥናት በማድረግ በቀጣይ የትምህርት ዘመን መጀመሪያ በተማሪዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አመዳደብ ተግባራዊ በማድረግ ከምደባ ወደ ቅበላ የማስጀመር ስራ መታቀዱንም ዶክተር ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የተማሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገን አሰራር በመስራት የትምህርት ጥራትን ማእከል ያደረገ ሥርዓት መመስረት ወሳኝ ነው፡፡ ካውንስሉም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማስጠበቅ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው፡፡

የካውንስሉ መመስረት የከፍተኛ ትምህርት ስልጠና ፕሮግራሞች የሀገሪቱን ፍላጎትና ገበያ ማእከል ያደረጉና ሀገሪቷንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላልም ብለዋል፡፡. (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version