ETHIO12.COM

ሕወሃት 7 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያነት ማዋል እንዳይችልና እንዳያሸሽ ተደረገ

ህገ ወጥ ቡድኑ ብር 6,762,942,319 (ስድስት ቢሊየን ሰባት መቶ ስልሳ ሁለት ሚሊዬን ዘጠኝ መቶ አራባ ሁለት ሺ ሦስት መቶ አስራ ዘጠኝ ብር) የሆነን ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያነት ማዋል እንዳይችልና በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳያሸሽ (እንዳይሰዉር) መከላከል መቻሉ ተገለጸ

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድን ታሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወነዉ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ብር 6,762,942,319.23 (ስድስት ቢሊየን ሰባት መቶ ስልሳ ሁለት ሚሊዬን ዘጠኝ መቶ አራባ ሁለት ሺ ሦስት መቶ አስራ ዘጠኝ ብር) የሆነን ገንዘብ ሕገ-ወጥ ቡድኑ ለወንጀል መፈጸሚያነት ማዋል እንዳይችልና በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳያሸሽ (እንዳይሰዉር) መከላከል የተቻለ ሲሆን ፤ መጠኑ ብር 97,573,164.30 (ዘጠና ሰባት ሚሊየን አምስት መቶ ሰባ ሦስት ሺ አንድ መቶ ስልሳ አራት ብር ከሠላሳ ሳንቲም) የሆነ የሕወሃት ገንዘብ በሕግ አግባብ የዉርስ ዉሳኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከተዉ አካል ተላልፏል ፡፡

Se kildebildet

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል የሆኑት አቶ ዓለምአንተ አግደዉ እንደገለጹት የሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ ሕገ-ወጥ ቡድኑ ሲቆጣጠራቸዉ በነበሩና ገንዘብና ንብረታዉን ለሕገ-ወጥ ኃላማዉ ሊጠቀምባቸዉ ይችላል በሚል በተጠረጠሩ ድርጅቶች እንዲሁም በጦርነት በተሳተፉ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ በተደረገ የሃብት ክትትልና ምርመራ ዉጤታማ ሥራዎች መመዝገባቸዉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት አገራቸዉ ኢትዮጵያን ከድተዉ ከሕወሃት ጋር በመሰለፍ በጦርነት የተሳተፉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ገንዘብና ሃብት ላይ በተደረገ ክትትልና ማጣራት ሥራ ብር 44,911,466.19 ፣ ሸር የገዙበት ገንዘብ ብር 9,326,099.17 በድምሩ ብር 54,237,565.36 (አምሳ አራት ሚሊዬን ሁለት መቶ ሰላሳ ሰባት ሺ አምስት መቶ ስልሳ አምስት ብር ከሠላሳ ስድስት ሳቲም) እንዲሁም ሌሎች ብዛት ያላቸዉ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡

በኤፈርት/ት.ም.ዕ.ት ሥር በሚተዳደሩ እና ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ በተከናወነ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ብር 3,785,770,669.30 እና ሼር የተገዛበት የገንዘብ መጠን ብር 419,946,392.37 በድምሩ ብር 4,205,717,061.67 (አራት ቢሊዬን ሁለት መቶ አምስት ሚሊዬን ሰባት መቶ አስራ ሰባት ሺ ስልሳ አንድ ብር ከስልሳ ሰባት ሳንቲም) በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ እና ግምታቸዉ ከ 2 (ሁለት) ቢሊዬን ብር በላይ የሆኑ 179 የደረቅና የፈሳሽ ጭት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለማሸሽ ጥረት ሲያደርጉ የፍ/ቤት ትዕዛዝ በማዉጣትና የጋራ የሕግ ትብብር ጥያቄ ለጅቡቲ መንግስት በማቅረብ ወደ አገር ማስመለስ ተችሏል፡፡

በዚህም ህገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የኤፈርት /ት.ዕ.ም.ዕ.ት ድርጅቶችን ገንዘብና ንብረት ለተጨማሪ የወንጀል ተግባር መፈጸሚያ እንዳያዉል ከፍተኛ የመከላከል ሥራ መስራት የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የወንጀልና የሃብት ምርመራዉ ተጠናቆ ፍ/ቤት የመጨረሻ ዉሳኔ አስኪሰጥ ድረስ የኤፈርት / ት.ዕ.ም.ዕ.ት ድርጅቶች በፍ/ቤት በተሾሙ ገለልተኛ አባለ አደራ ቦርድ ስር ሆነዉ ለሕጋዊ አላማ ብቻ እንዲሰሩ ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ በሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድንና በዚህ ቡድን ስር በነበሩ አመራሮች ቀጥተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዉ በነበሩና ቡድኑ የድርጅቶችን ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያ ሊያዉል ይችል የነበሩ ሦስት ስቪል ማህበራት ላይ በተደረገ የሃብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ብር 400,150,617.87 እና ሼር የተገዛበት ገንዘብ ብር 5,254,910.10 በድምሩ ብር 405,405,527.97 (አራት መቶ አምስት ሚሊየን አራት መቶ አምስት ሺ አምስት መቶ ሃያ ሰባት ብር ከዘጠና ሰባት ሳንቲም) በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ እና ገለልተኛ አስተዳዳሪ በፍ/ቤት በማሾም የማህበራቱ ገንዘብ በሕወሃት ቡድን ለሕገ-ወጥ ዓላማ እንዳይዉል መከላከል ተችሏል፡፡

በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል በተከናወነዉ የሃብት ክትትልና ምርመራ ሥራ የሕወሃት የሆነ ብር 97,582,164.33 (ዘጠና ሰባት ሚሊዬን አምስት መቶ ሰማንያ ሁለት ሺ አንድ መቶ ስልሳ አራት ብር ከሠላሳ ሦስት ሳንቲም) በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ ሕገ-ወጥ ቡድኑ ለወንጀል ተግባር እንዳይጠቀምበት እና ማሸሽ እንዳይችል መከላከል ከመቻሉም በላይ ሕወሃት ሃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ላይ መሳተፉን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከምዝገባ የሰረዘዉ በመሆኑ ይህንን ገንዘብ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 99 (2) እና (3) መሰረት ዕዳዉን ሸፍኖ የሚተርፍ የፓርቲዉ ገንዘብ ካለ ለሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲዉል በምርመራ ከተሰባሰቡ ማስረጃዎች ጋር አባሪ በማድረግ መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ለቦርዱ እንዲተላለፍ ተደርጓል ሲሉ ዳይሬክተር ጄኔራሉ ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ አቶ ዓለምአንተ አግደዉ እንደገለጹት ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ ቡድኑ ይቆጣጠራቸዉ የነበሩ ገንዘቦችና ሀብቶችን ለተጨማሪ ጥፋት እንዳይጠቀምና እንዳያሸሽ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጦ በፍጥነት በመሰራቱ የመከላከል ሥራዉን ዉጤታማ እንዳደረገዉ እና አሁንም ቀሪ ሥራዎችን ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮና ሌሎች ከሚመለከታዉ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

FDRE Attorney General የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ


Exit mobile version