ETHIO12.COM

የፍትህ ያለህ የሚሉት የ87 ዓመት አረጋዊቷ እሮሮ

<<ጉልበቴ እንደዛሬው ሳይደክም በ1976 ዓ.ም የሰራሁትን መጸዳጃ ቤት በተንሻፈፈ ፍርድ አፍርሽ ተብዬ ተወስኖብኝ የፍትህ ያለህ! ፍትህ ተዛብቶብኛል የሚሉት ገርበ ጉራቻ ከተማ ነዋሪ የ87 ዓመት አዛውንቷ ወይዘሮ እናኑ ክብረት ናቸው፡፡ ሰሚ አጥቼ እያለቀስሁ እገኛለሁና ህዝብና መንግስት ይፍረደኝ>> ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታቸው አቅርበዋል።

በገርበ ጉራቻ ከተማ ተወልደው እንዳደጉ የሚናገሩት ወይዘሮ እናኑ ክብረት፤ የእናታቸው እህት ወይዘሮ ኋላዬ ጉራራ ልጅ ስላልነበራቸው እርሳቸውን ከእናትና ከአባታቸው አስፈቅደው ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዳሳደጓቸው እና በኃይለስለሴ ዘመነ መንግስት አክስታቸው ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ አክስታቸው ሌላ ወራሽ ልጅ ስላልነበራቸው አሁን ይዘው እያስተዳደሩት ያለውን ቦታ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከአክስታቸው ከወይዘሮ ኋላዬ ጉራራ ወርሰው እያስተዳደሩት እንደሚገኙ ይናገራሉ።

ቦታውን በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ከአክስታቸው ሲወርሱት 2ሺ 622 ካሬ ሜትር ስፋትና በላዩ ላይ ሰባት ክፍል ቤት እንደነበረው ወይዘሮ እናኑ ጠቁመው፤ ስድስቱን ክፍል አከራይተው አንዱ ክፍል ቤት ደግሞ ራሳቸው እየኖሩበት እያለ በደርግ ዘመነ መንግስት የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ንብረት ለማድረግ በወጣው አዋጅ 47/67 መሰረት ስድስቱ ክፍል ቤትና 2ሺ 40 ካሬ ሜትሩ ቦታ ሲወረስ፤ በአዋጁ መሰረት ለብቻዋ ፈንጠር ብላ መሃል ላይ የተሰራች አንድ ክፍል ቤትና 582 ካሬ ሜትር ቦታ ለእርሳቸው እንደተወሰነላቸው ይናገራሉ።

ወይዘሮ እናኑ በአዋጁ መሰረት የተፈቀደላቸውን ቤትና ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ አሰርተው ከማስተዳደር ባለፈ በይዞታው ላይ ሌሎች ተጨማሪ ስምንት ክፍል ቤት ሰርተው አሁን ድረስ እያከራዩ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በደርግ ዘመነ መንግስት በተፈቀደላቸው ይዞታቸው ላይ ከማዘጋጃ ፈቃድ አውጥተው በ1976 ዓ.ም የሰሩትን ነባር መጸዳጃ ቤታቸውን ወይዘሮ ገነት መንግስቱ የተባሉ ጎረቤታቸው ፍትህን በጥቅም በመደለል የመጸዳጃ ቤታቸውን ግማሽ ክፍል አፍረሰው ወደ ግቢያቸው አካተው ማጠራቸውን ይናገራሉ።

እርሳቸውም እንዳብራሩት፤ በእርጅና ዘመናቸው የልጅ እጅ ከማየት በማለት ተጨማሪ ሰርቪስ ቤት ሰርተው በማከራየት ገቢያቸውን ለመደጎም አቅደው ከፊት ለፊት በመንገዱ በኩል ያረጀችውን ሰርቪስ ቤታቸውን እና አጥራቸውን አፍርሰው ባለቻቸው ትርፍ ቦታ ከፍቼ ዞን ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ህጋዊ የግንባታ ፈቃድ ወስደው ወደ ግንባታ መግባታቸውን ይናገራሉ።

ግንባታውን ጀምረው ገና መሰረቱን ሲያወጡ ጎረቤታቸው ወይዘሮ ገነት መንግስቱ ድንበር አልፈሻል ብለው ከገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ባለሙያ ይዘው መምጣታቸውን ወይዘሮ እናኑ ጠቁመው፤ ባለሙያውም የሚያካሂዱትን ግንባታ በፕላኑ መሰረትና በይዞታቸው ላይ ማካሄዳቸውን ለክቶ ካረጋገጠ በኋላ በጀርባ በኩል ከወይዘሮ ገነት መንግስቱ ጋር በሚያዋስነው ድንበር የእርሳቸው ነባር መጸዳጃ ቤት እንጂ አዲስ ግንባታ ያከናወኑት እንደሌለና ወሰን እንዳልገፉ፤ ነገር ግን ከወደ ፊት ለፊት በመንገዱ በኩል አዲስ ግንባታ በሚከናወንበት 50 ሴንቲ ሜትር ወደ መንገድ ታልፏልና ትለቂያለሽ በሚል ባለሙያው አስተያየት ሰጥቶ መሄዱን ይናገራሉ።

የ87 ዓመት አዛውንቷ እንደሚሉት፤ ከሳሿ ከአዛውንቷ ጋር በሚያዋስናቸው ድንበር መካከል ያላቸውን ይዞታ ሙሉ ለሙሉ ጨርሰው በብሎኬት ሰርቪስ ቤት መስራታቸውን ጠቁመው፤ ነገር ግን በከሳሿና በተከሳሿ ድንበር መካከል ትርፍ ቦታ አለ ከተባለ ተጠብቆ ቢቀመጥ አልቃወምም የሚል ምላሽ ለባለሙያው ሰጥተው ግንባታቸውን እያከናወኑ እያለ ባለሙያው የወሰነው ውሳኔ አልስማማም በሚል ወይዘሮ ገነት ከፍርድ ቤት ክስ ይዘው መጥተው ግንባታቸውን እንዳሳገዱባቸው ይናገራሉ።

ወይዘሮ ገነት መንግስቱም በቀን 13/04/2013 ዓ.ም ለኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤት ጽፈው ባቀረቡት ክስ ከ10 ዓመት በፊት ግንባታ ሲያካሂዱ ወደ ፊት ለሚያከናውኑት የህንፃ ግንባታ እንቅስቃሴ እንዳይከለክላቸው ወደ ጎን ስፋቱ አንድ ነጥብ 4 ሜትር እና እርዝመቱ 28 ነጥብ 5 ሜትር የሆነ መሬት በተከሳሽዋ አቅጣጫ ትተው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ተከሳሽዋም ግንባታ ሲያካሂዱ ከወሰናቸው ላይ ወደ ጎን 50 ሳንቲ ሜትር ርቀው ግንባታ ማካሄድ ስላለባቸው በመካከላችን አንድ ነጥብ 9 ሜትር ክፍት ቦታ መኖር ያለበት ቢሆንም ቅሉ፤ ተከሳሽዋ ከቀን 20/03/2013 ዓ.ም ጀምሮ እርሳቸው በተከሳሽ አቅጣጫ የተውትን ክፍት ይዞታቸውን ወሰን በማለፍ የቤት እና የአጥር ግንባታ ለማካሄድ መሰረት በማውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ስለዚህ ተከሳሽዋ ወሰን አልፈው በይዞታይ ላይ የገነቡትን ግንባታ በራሳቸው ወጪ አንስተው ከወሰኑ ላይ ግማሽ ሜትር ርቀው እንዲገነቡ ይወሰንልኝ በሚል ክስ እንደተመሰረቱባቸው ወይዘሮ እናኑ ይናገራሉ።

በአንጻሩ ተከሳሿም በቀን 21/04/2013 ዓ.ም በጽሁፍ ባቀረቡት መልስ እርሳቸው ወደ ከሳሿ ወሰን አልፈው የጀመሩት ግንባታ እንደሌለ ጠቁመው፤ የራሳቸውን ያረጀ ሰርቪስ ቤትና አጥር አፍረሰው በራሳቸው ይዞታ ላይ ህጋዊ የግንባታ ፈቃድ ጉዳዩ ከሚመለከተው ከሰሜን ሸዋ ዞን ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት አውጥተው ግንባታውን እያከናወኑ እንደሚገኝና የማንም ድንበር እንዳልገፉ በማስረዳት የቀረበው ክስ ወድቅ ይደረግልኝ ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ማመልከታቸውን ይናገራሉ።

ፍርድ ቤቱም በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የግራና ቀኙን የሰው ማስረጃ ከማድመጥ ባለፈ ከከተማው ፕላን አንጻር ተከሳሽ ወደ ከሳሽ ወሰን በማለፍ ያከናወኑት ግንባታ አለ? ወይስ የለም? ታልፎ ከሆነ ምን ያህል ነው? በወሰናቸው መካከል መቅረት ያለበት ወይም ክፍት መደረግ ያለበት የመሬት ስፋትስ ምን ያህል ነው? የሚሉ ጭብጦችን የገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት አጣርቶ ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት እንዲያደርግ መታዘዙን ወይዘሮ እናኑ ተናግረዋል።

የገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሰረት ባለሙያ ወደ ቦታው ልኮ የተላከው ባለሙያ ቦታውን አይቶና ለክቶ ሪፖርቱን በተገቢው መንገድ ለፍርድ ቤቱ መላኩን የሚናገሩት ወይዘሮ እናኑ፤ ጽህፈት ቤቱም ለፍርድ ቤቱ በላከው መረጃ በከሳሽና በተከሳሽ መካከል በጀርባ በኩል በሚያዋስነው ተከሳሽ ምንም የገፉት ድንበር አለመኖሩን፤ ነገር ግን ከፊት ለፊት ወደ ከሳሿ ድንበር ሳይሆን ወደ መንገድ በኩል 50 ሴንቲ ሜትር ታልፏል በሚል በደብዳቤ ገልጿል ብለዋል።

ከወደ ፊት ለፊት በመንገዱ በኩል አጎራባቾቻቸው ባጠሩት ተዋረድ ልክ እርሳቸውም ማጠራቸውን፤ ነገር ግን ከፊት ለፊት በኩል ወደ መንገድ ገፍተዋል ከተባሉ እንደህዝብ ወደ መንገድ ይመለስ ሲባል ወደ መንገድ እመልሳለሁ እንጂ በከሳሽና በተከሳሽ መካከል የምለቀው ምንም ትርፍ ቦታ የለም የሚሉት የ87 ዓመት አዛውንቷ ፤ ነገር ግን ከሳሿ የገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ለፍርድ ቤት የላከውን መረጃ በመቃወም በሰሜን ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት በኩል ጉዳዩ ይጣራልኝ በሚል በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ የከሳሿን መብት ጠብቆ በሰሜን ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ጉዳዬን አጣርቶ እንዲልክ ፍርድ ቤቱ ማዘዙን ተናግረዋል።

ከሰሜን ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት የመጡ ሁለት ባለሙያዎች እርሳቸው ሰው ሞቶ ቀብር ቆይተው ሲመለሱ በሌሉበት ግቢያቸውን እየለኩ እንዳገኟቸው የሚናገሩት ወይዘሮ እናኑ፤ ምንድነው ብለው ወደ ግቢያቸው ሲገቡ ጎረቤቶቻቸው <<ለሞተ ሰው ታለቅሻለሽ በቁምሽ ለሞትሽው ለራስሽ አልቅሽ። አንቺ በሌለሽበት ግቢሽ እየተለካ ነው>> ሲሏቸው እርሳቸውም ባለሙያዎቹን እንዴት ባለቤት በሌለበት ቦታዬን ትለካላቹህ በሚል ሲጠይቁ የሚመልሱት አጥተው መደናገጣቸውን ያወሳሉ።

ባለሙያዎቹ እርሳቸው ከለቅሶ ከመምጣታቸው በፊት ቦታውን ለክተው ችካል እንደቸከሉ፤ ነገር ግን የቸከሉትን ችካል ለእርሳቸው ሳያሳዩ ደብቀው ቦታው ባሉበት ተለክቷል የሚል ፊርማ እንዳስፈረሟቸው ቅሬታ አቅራቢዋ ጠቁመው፤ ባለሙያዎቹም እርሳቸውን ካስፈረሟቸው በኋላ <<እንግዲህ ታርቃችኋል>> የሚል ነገር ሲናገሩ <<ምንድነው ታርቃችኋል ታርቃችኋል የምትሉት? የምን እርቅ ነው? በፍርድ ቤት የታዘዛችሁት መረጃ አጣርታችሁ እንድትልኩ ነው እንጂ እንድታስታርቁ አይደለም>> የሚል ምላሽ ሲሰጡ <<ታርቃችኋል ታርቃችኋል>> እያሉ ትተዋቸው እንደሄዱ ይናገራሉ።

ባለሙያዎቹ <<ጆሮ ዳባ ልበስ>> ብለው ትተዋቸው ሲሄዱ ወዲያውኑ ኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤት ሄደው ሳያውቁ አጭበርብረው ታርቃችኋል በሚል እንዳስፈረሟቸውና እርሳቸው በሌሉበት በድብቅ ሳያዩ ችካል ቸክለው መሄዳቸውን ለፍርድ ቤቱ ሲያሳውቁ ፍርድ ቤቱም <<በቀጠሮዎ ሲመጡ አብረው ቅሬታዎትን ማቅረብ ይችላሉ>> ብሎ ወደ ቤታቸው እንደመለሳቸው ቅሬታ አቅራቢዋ ይናገራሉ።

የዞኑ ባለሙያዎች እርሳቸው አዲስ ግንባታ በሚያካሄዱት በኩል ምን ያህል አልፈዋል? ወይስ አላለፉም? ከሳሽ ከ10 ዓመት በፊት ግንባታ ሲያካሂዱ ለወደፊት ለሚከናውነው ግንባታ እንዳያስቸግረኝ አንድ ነጥብ 4 ሜትር ትርፍ ቦታ ትቻለሁ ያሉት ክፍት ቦታ ምን ያህል እውነታ ነው? በተከሳሽና በከሳሽ ድንበር መካከል የትኛው ግንባታ ነው የጥንት? የትኛው ግንባታ ነው አዲስ? የሚለውን ጭብጥ አጣርተው ለፍርድ ቤቱ መረጃ መላክ ሲጠበቅባቸው፤ ነገር ግን ባለሙያዎቹ እርሳቸው የሰሩትን ግንባታ አፍረሰው እለቃለሁ ብለው እንደተስማሙ አድርገው ለፍርድ ቤቱ መረጃ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከሳሽ 50 ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ ተከሳሽ እርቃ እንድትገነባ ይወሰንልኝ በሚል ፍርድ ጠይቃው እያለ ባለሙያዎቹ በጥቅም ተደልለው ፍርድ ያልተጠየቀበትን ይዞታ በመለካት እርሳቸው አዲስ ግንባታ በሚገነቡበት በኩል ርዝመቱ 90 ሴንቲ ሜትር መሬት እና በጀርባ በነባር መጸዳጃ ቤታቸው በኩል ርዝመቱ 70 ሴንቲ ሜትር ቦታ ገፍታለች በሚል በ1976 ዓ.ም የሰሩትን ነባር መጸዳጃ ቤት አዲስ ግንባታ ያከናወኑ አስመስለው ግማሹን ወደ ከሳሿ ይዞታ ስር በማካተት ለፍርድ ቤቱ መረጃ መላካቸውን ተናግረዋል።

በጥቅሉ የሰሜን ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች በጥቅም ተደልለው የተዛባ መረጃ ለፍርድ ቤቱ መላካቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ የሰሜን ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት በቀን 08/06/2013 ዓ.ም በመ/ቁ ዲኤች 3/775/85/2 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በላከው የተዛባ መረጃ መሰረት ከሳሽ ተከሳሽን 50 ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ እንድትገነባ ይወሰንልኝ ብላ ክስ ያቀረበች ሆኖ እያለ፤

የሰሜን ሸዋ ዞን የኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤት ባለሙያዎቹ የሰጡትን የተዛባ መረጃ በመያዝ በመዝገብ ቁጥር 57489 በቀን 24/06/2013 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ተከሳሽ ወሰን በማለፍ በስተምስራቅ አቅጣጫ ርዝመቱ 90 ሴንቲ ሜትር መሬት እና በምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ ርዝመቱ 70 ሴንቲ ሜትር ከሆነው መሬት ላይ ያካሄዱትን ግንባታ በራሳቸው ወጪ በማንሳት ይዞታውን ለከሳሽ ትልቀቅ በማለት የወሰነው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን ወይዘሮ እናኑ ይናገራሉ።

እንዲሁም ከሳሽ ከ10 ዓመት በፊት ግንባታ ሲያካሂዱ ወደ ፊት ለሚያከናውኑት ግንባታ እንቅፋት እንዳይሆንብኝ በሚል የተውኩት ቦታ ላይ ይዞታዬን በማለፍ ተከሳሽ ግንባታ እያከናወነች ነው በማለት የከሰሱ ሆኖ እያለ፤ ፍርድ ቤቱ ነባር ይዞታ የሆነውን እና በደርግ ጊዜ በ1976 ዓ.ም የገነቡትን መፀዳጃ ቤት እና አጥር ጭምሮ ይፍረስ ማለቱ ውሳኔው ማስረጃን ሳይመዝን እና በዘፈቀደ የተሰጠ ፍርድ ለመሆኑ ማሳያ ነው። መሰረታዊ የህግ ስህተትም የተፈጸመበት ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የተከሳሽ 2ኛ የሰው ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምስክርነት ከ10 ዓመት በላይ የእርሳቸውን ቤት ተከራይተው ሲኖሩ በተከሳሽና በከሳሽ መካከል ያለው ወሰን መጸዳጃ ቤት እንጂ አጥር አልነበረም ብለው ምስክርነታቸውን መስጠታቸውን ወይዘሮ እናኑ ጠቁመው፤ ከሳሽ ከ10 ዓመት በፊት ግንባታ ሳካሂድ ወደ ፊት ለማከናውነው ግንባታ እንዳይከለክለኝ አንድ ነጥብ 4 ሜትር በተከሳሽዋ አቅጣጫ ትቼ ነበር ያሉት ከእርሳቸው የሰው ማስረጃ ምስክርነት ጋር የሚጣረስ ነው። ከሳሽ ትቼዋለሁ የሚሉትን መሬትም አጥረው በይዞታቸው ስር ባላደረጉበት ሁኔታ ግንባታ ተከናውኖበታል መባሉ ተገቢነት እንደሌለው ወይዘሮ እናኑ ይናገራሉ።

ወይዘሮ እናኑ አክለውም፤ የከሳሽ ምስክሮች በነዋይ ተደልለው ጉዳዮን በቅርበት ሳያውቁት ተከሳሽ ድንበር አልፋ ግንባታ አካሂዳለች በሚል የመሰከሩትን ማስረጃ ፍርድ ቤቱ መቀበሉን ጠቁመው፤ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ የእርሳቸውን የሰው ማስረጃ ጉዳዩን በቅርበት የማያውቁት መሆኑን ከምስክርነት ቃላቸው ላይ መገንዘብ ተችሏል በማለት የሰጠው ውሳኔ የተከሳሽን የሰው ማስረጃ ቃል ከግምት ያላስገባና በአግባቡ ያልተመዘነ በመሆኑ ፍትሃዊነት የጎደለው እና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ሲሉ ይኮንናሉ።

በተጨማሪም ከሳሿ በድንበራችን መሃል 50 ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ ትገንባ ሲሉ ፍርድ የጠየቁ ሲሆን እርሳቸውም በበኩላቸው በእርሳቸው መጸዳጃ ቤት እና በከሳሽ ግንባታ መሀከል የተባለው 50 ሴንቲ ሜትር ትርፍ ቦታ ካለ ቢጠበቅ እንደማይቃወሙ ባስረዱበት ሁኔታ እና የእርሳቸው ግንባታ ቀደምት መሆኑ እየታወቀ ርቀት ያልጠበቀ ተደርጎ የእርሳቸው መጸዳጃ ቤት ይፍረስ መባሉ ምን ያህል ፍትህ መዛባቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ይላሉ የ87 ዓመቷ አዛውንት።

እንዲሁም ከሳሿ የገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት በፕላኑ መሰረት መረጃን ፈትሾ ለፍርድ ቤቱ የላከው መረጃ ውድቅ ይደረግልኝ ብለው በማመልከታቸው ውድቅ እንዲደረግና ድጋሚ በሰሜን ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደር  እና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት በኩል እንዲጣራ መታዘዙ ህጋዊ መሰረት የሌለው እና ቀደም ብሎ ከገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ካቀረበው ሪፖርት ጋር የሚጣረስ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዋ ገልጸዋል።

ነገር ግን እርሳቸው እንዳሉት የዞኑ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች የላኩት መረጃ በገለልተኛ አካል ይፈተሽ በሚል በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ሳያደምጥ ውሳኔ መስጠቱ በፍትህ ሰርዓቱ አድሎአዊ አሰራር መኖሩን ቁልጭ አደርጎ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ የሰሜን ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት መሃንዲሶች ወይም ባለሙያዎች ከከሳሿ ጋር በመመሳጠር ሐሰተኛ የሆነ ሙያዊ አስተያየት ለፍርድ ቤት አቅርበዋል የሚሉት አዛውንቷ፤ የድንበር ይገባኛል ውዝግቡ ዳግም በገለልተኛ አካል ወይም ባለሙያ እንዲጣራ ይታዘዝልኝ በሚል በችሎት ፊት ደጋግመው ቀርበው ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን ቅሬታ ሳይቀበል ቀርቷል በለዋል፡፡ ፍርድ ባለሙያዎቹ በጥቅም ተደልለው ከጭብጥ ውጭ የሰጡትን ሙያዊ አስተያየት ተቀብሎ በ1976 ዓ.ም የሰሩትን ነባር መጸዳጃ ቤታቸውን እና አጥራቸውን ጭምር አፍርሰው እንዲለቁ የሰጠውን ውሳኔ ለበላይ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ እያሉ ባሉበት ሁኔታ ከሳሽ ነባር መጸዳጃ ቤታቸውን ግማሹን ክፍል ወደ ይዞታቸው ቀላቅለው እንዳጠሩባቸው ተናግረዋል።

አቤቱታ አቅራቢዋም የኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ከሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ቅደም ተከተሉን ጠብቀው ይግባኝ ማለታቸውን ጠቁመው፤ ነገር ግን በከሳሽና በተከሳሽ መካከል ያለውን የወሰን ይገባኛል ውዝግብ በገለልተኛ ባለሙያ ይጣራልኝ በሚል ለሁሉም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ቢያመለክቱም ፍርድ ቤቶቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ጉዳያቸውን ሳይመለከቱ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔዎች መሰረታዊ የህግ ስህተት አልተፈጸመበትም በሚል ውሳኔውን ማጽናታቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሮ እናኑ ከሳሿ አሁን ላይ ከእርሳቸው ጋር የድንበር ይገባኛል ውዝግብ የገቡበት ቦታ ቀደም ሲል ከኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አንስቶ ደርግ ይዞታቸውን እስከወረሰበት ድረስ የእርሳቸው ይዞታ እንደነበር ጠቁመው፤ ከሳሿ ይሄንን ይዞታ እንዴት ከመንግስት እጅ ወደ ግል ይዞታቸው አዛውረው ሆቴል ሰርተውበት እያስተዳደሩት እንደሚገኝ ጥያቄውን ለመንግስት አካል ትተው፤ ነገር ግን መንግስት ከእርሳቸው ቀደምት ይዞታ ላይ ወስዶ ለከሳሽ ሰጥቶ ከሳሽ የገነቡት አዲሱ ግንባታ ይፍረስ ሳይባል የእርሳቸው በደርግ ዘመነ መንግስት የተገነባ ነባር መጸዳጃ ቤታቸው ይፍረስ ተብሎ ተወስኖባቸው በደል ላይ በደል እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

በከሳሽና በተከሳሽ መካከል ይገባኛል ክርክር በተነሳበት ድንበር በኩል ነባር መጸዳጃ ቤታቸው ባይኖር ኖሮ አይደለም 50 ሴንቲ ሜትር ቀርቶ አስር ሜትር ክፍት ቦታ ቢኖር ፍርዱን ለፈጣሪ ሰጥተው ቦታውን ለከሳሽ ለቀው በዚህ እድሜያቸው ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት እንደማይንከራተቱ ወይዘሮ እናኑ ገልጸው፤ ከሳሽ በኢህአዴግ ስርዓት የሰሩት መጸዳጃ ቤታቸው ይፍረስ ሳይባል ነገር ግን በ1976 ዓ.ም የሰሩት ነባር መጸዳጃ ቤታቸው ድንበር ታልፎ የተሰራ በሚል እንዲፈርስ በመደረጉ በስተእርጅና መጸዳጃ ቤት አጥተው ለችግር መዳረጋቸውን ይናገራሉ።

ከዚህ ባሻገር መጸዳጃ ቤት የሌለው ግቢ ላይ እንዴት እንኖራለን እያሉ ተከራዮቼ እየለቀቁ ሄደውብኛል የሚሉት የ87 ዓመት አዛውንቷ፤ መጸዳጃ ቤታቸው በመፍረሱ ጉልበታቸው ሳይደክም የሰሩትን ቤት እያከራዩ ቀሪ ዘመናቸውን እንዳይጦሩ እንቅፋት ከመፍጠሩም በላይ በእርጅና ዘመናቸው መጸዳጃ ቤት አጥተው ለችግር ተጋልጫለሁና ህዝብና መንግስት ይፍረደኝ ሲሉ ወይዘሮ እናኑ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የተከሳሽተከራዮችምንይላሉ?

የገርበ ጉራቻ ነዋሪና ከአቤቱታ አቅራቢዋ ግቢ ተከራይተው ከስድስት ዓመት በላይ እንደኖሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት አውላቸው እንደገለጹት፤ የከተማው ማህበረሰብ የመጸዳጃ ቤቱን ፍሳሽ የፍሳሽ ቆሻሻ በሚያነሱ መኪኖች ማስነሳት ፍላጎት የለውም፡፡ ምክንያቱም በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ብር ማውጣት ስለማይፈልጉ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሻቸውን የሚለቁት ቱቦ ቀብረው በላዩ ላይ ጣውላ አልብሰው ወደ መንገድ ነው፡፡

በመሆኑም አሁን በከሳሽና በተከሳሽ ድንበር መካከል ይገባኛል ጥያቄ የተነሳበትን ቦታ ተከሳሽ በሃሰት አስመስክረው ከአዛውንቷ የወሰዱት ድንበር ስለገፉ አይደለም፡፡ ከሳሽም ቦታውን ለሌላ ስራ ለማዋል ወይም ግንባታ ሊያከናውኑበት ፈልገውት አይደለም፡፡

ከሳሽ ከአዛውንቷ በሚያዋስናቸው ድንበር በኩል ሙሉ ለሙሉ ይዞታቸውን ጨርሰው ግንባታ ስለሰሩበት የመጸዳጃ ቤታቸውን ፍሳሽ በቱቦ አድርገው ወደ አዛውንቷ ግቢና ወደ መንገድ ለመልቀቅ ስላሰቡ ነው ፡፡የአዛውንቷን የጥንት መጸዳጃ ቤት በሃሰት አስመስክረው ወደ ይዞታቸው ያካተቱት ብለዋል።

ከሳሽ ቦታውን የተከራከሩበት እውነት ቦታ ተገፍተው ሳይሆን ለመጸዳጃ ቤት ማስተንፈሻ ፈልገውት ነው የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ ከሳሽ ከጀርባ በኩል መጥተው ይገባኛል ብለው የተከራከሩት የመጸዳጃ ቤት ፍሳሻቸውን ወደ አዛውንቷ ግቢ ለመልቀቅ በማሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ገርበ ጉራቻ ውስጥ አንዱ በአንዱ ላይ የመጸዳጃ ቤቱን ፍሳሽ መልቅ እንደ ባህል ከታየ ውሎ አድሯል፡፡ በከተማዋ ወጣ ተብሎ ተዘዋውሮ ቢታይ አንዱ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሹን ወደ አንዱ ግቢ መልቀቅ የተለመደ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህም አስነዋሪ ባህል ህብረተሰቡን ለከፋ የጤና ችግር እየዳረገው እንደሚገኝ የከተማዋ ነዋሪ ገልጸው፤ በአዛውንቷ ቤት መውጫ ባለው መንገድ ያሉ ሆቴሎች የመጸዳጃ ቤታቸውን ፍሳሽ ወደ መንገዱ ስለሚለቁ ቀደም ሲል መኪና ያልፍበት የነበረው መንገድ አሁን ላይ እንኳን መኪና ሊያልፍበት ቀርቶ እነርሱ ከግቢ ወጥተው ሲንቀሳቀሱ ተቸግረው እንደሚያልፉ እና አሁን ላይ ይባስ ብሎ የአከራያቸው መጸዳጃ ቤት በከሳሽ በመታጠሩ ያለመጸዳጃ ቤት ለመኖር መቸገራቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ክረምት ላይ ሁሉም የከተማዋ ማህበረሰብ በሚባል መልኩ የመጸዳጃ ቤቱን ፍሳሽ ወደ መንገድ ስለሚለቅ በተለይ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ የጠላ ድፍድፍ መስሎ ተጋግሮ በመንገድ ለማለፍ ያጸይፋል፤ ያስቸግራል።

ይህንን እኩይ ተግባር ለማስቀረት የከተማዋ ነዋሪ ሁሌም እንደሚታገል ወይዘሮ ገነት ጠቁመው፤ ነገር ግን በተለይ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ለፍሳሽ ማስመጠጫ መኪና ከመክፍል ይልቅ መንገድ ላይ በቱቦ አገናኝተው መልቀቁ ስለሚቀላቸውና ወጪ ስለማያስወጣቸው የሆቴል ባለሃብቶች በገንዘብ የህብረተሰቡን ጥያቄ እያፈኑ እስካሁን ለችግሩ መፍትሄ እንዳልተገኝለት ወይዘሮ ገነት ተናግረዋል፡፡

የገርበጉራቻከተማአስተዳደርመሬትአስተዳደርናአጠቃቀምጽህፈትቤትምላሽ

የዝግጅት ክፍላችን ወደ ገርበ ጉራቻ ከተማ አቅንቶ ጽህፈት ቤቱን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን በደብዳቤ ጭምር የጠየቀ ሲሆን፤ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ለቦታው አዲስ እንደሆኑና ጉዳዮን እንደማያውቁት ገልጸዋል።

ነገር ግን የዝግጅት ክፍላችን ጽህፈት ቤቱ ለፍርድ ቤት በከሳሽና በተከሳሽ ጉዳይ ላይ የላከውን መረጃ ፋይል ወጥቶ ይሰጠን በሚል በጠየቀው ጥያቄ መሰረት የገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ኃላፊና ባለሙያዎች እንዲሁም የገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አለማየሁ ተክለማሪያም ጭምር ባሉበት እልህ አስጨራሽ የመረጃ ፍለጋ ስራ ተሰርቷል።

ነገር ግን በከሳሽና ተከሳሽ ፋይል ውስጥ ለፍርድ ቤት የተሰጠ መረጃ የሚከተለው ብቻ ነው በሚል የከተማዋ ከንቲባ አቶ አለማየሁ በሰጡን መረጃ እንደገለጹት፤ ስለወይዘሮ ገነት መንግስቱና በገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር መካከል ስላለው ክርክር የኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 5420 በቀን 15 /08/2011 ዓ.ም ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከሰሜን ሸዋ ዞን መሬት ማኔጅመንትና ከሰሜን ሸዋ ዞን ከተማ ልማት ጋር በመሆን በቀን 24/ 08 /2011 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ በቦታው ተገኝቶ ጉዳዩን በጋራ አጣርቶ እንዲልክ የኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤት የገርበ ጉራቻ ከተማ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤትን ትዕዛዝ መስጠቱን ተናግረዋል።

ነገር ግን በተባለው ቀንና ሰዓት የገርበ ጉራቻ ከተማ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ጉዳዩን ለማጣራት በቦታው ቢገኝም በጋራ ጉዳዩን እንዲያጣሩ የተባሉ ሌሎች አካላት ባለመገኝታቸው ጉዳዩን ለማጣራት ያልቻለ መሆኑን የገርበ ጉራቻ ከተማ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ለኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤት መግለጹን ተናግረዋል።

አቶ አለማየሁ ከዚህ ውጭ በከሳሽና በተከሳሽ ፋይል ውስጥ በተደረገው ፍተሻ ጽህፈት ቤቱ በከሳሽና በተከሳሽ ድንበር ይገባኛል ውዝግብ ላይ መረጃ እንዲሰጥ ተጠይቆ የሰጠው መረጃ እንደሌለ፤ ከዞንም ይሁን ከፍርድ ቤት ስለከሳሽና ተከሳሽ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ የባለሙያ አስተያየት ተጠይቆ የተሰጠ መረጃ አለመኖሩንና ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ በድንበር ይገባኛል ውዝግብ ጉዳይ ለጽህፈት ቤቱ ያቀረቡት ቅሬታ እንደሌለ ተናግረዋል።

የሰሜንሸዋዞንመሬትአስተዳደርናአጠቃቀምጽህፈትቤትምላሽ

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡርጌ ለማ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ የኩዩ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀን 25/ 05 /2013 ዓ.ም በመ/ቁ 57489 ለጽህፈት ቤቱ በላከው ደብዳቤ የገርበ ጉራቻ ከተማ አስተዳደር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት በተከሳሽና ከሳሽ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ላይ ለፍርድ ቤቱ ያላከውን መረጃ በእናንተ በኩል ዳግም አጣርታችሁ በ08/06/2013 ዓ.ም እንድትልኩ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ጽህፈት ቤቱም ጉዳዩን እንዲያጣሩ የወሰን ጉዳይ የስራ ሂደት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ታዬ ጂዳን እና የቅየሳ ባለሙያ የሆኑትን አቶ አበራ ብሩን ወደ ቦታው የላከ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም በትዕዛዙ የግራና የቀኝ ምስክሮችን በደብዳቤ አሳውቃችሁ ምስክሮቹ ባሉበት እንድታጣሩ ባለው መሰረት ባለሙያዎቹ ወይዘሮ ሳምራ ሽኩሪ፣ ወይዘሮ ገነት አውላቸው እና አቶ ሙሃመድ ናስር የተባሉ ሶስት የተከሳሽና የከሳሽ ምስክሮች ባሉበት ቦታውን መለካታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ኡርጌ ባለሙያዎቹም ከከሳሽና ተከሳሽ ባለፈ ምስክሮቻቸው ባሉበት ካርታቸውን ይዘው በካርታው መሰረት ቦታውን ለክተው ችካል መቸከላቸውን ጠቁመው፤ ባለሙያዎቹ ቦታውን በለኩት መሰረት ተከሳሽ በምስራቅ በኩል 90 ሴንቲ ሜትር እንዲሁም በምዕራብ በኩል 70 ሴንቲ ሜትር እንዳለፉ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም ባለሙያዎቹ ባሉበት ከሳሽና ተከሳሽ ተስማምተናል ሲሉ መፈራረማቸውን ጠቁመው፤ ተከሳሿ ድንበር አልፈው የገነቡት ግንባታ ካለ በራሳቸው ወጪ አፍርሰው እንደሚለቁና ያለፉትንም ትርፍ ቦታ ለከሳሽ እለቃለሁ በሚል ተስማምተው በውሉ ላይ መፈረማቸውን ተናግረዋል።

ጽህፈት ቤቱም ባለሙያዎቹ ያቀረቡትን መረጃ በቀን 08/06/2013 ዓ.ም በመ/ቁ ዲኤች 3/775/85/2 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ እንደላከ የሚናገሩት ምክትል ኃላፊው፤ ጽህፈት ቤቱም ለፍርደ ቤቱ በላከው መረጃ ተከሳሽ በምስራቅ በኩል 90 ሴንቲ ሜትር እንዲሁም በምዕራብ በኩል 70 ሴንቲ ሜትር እንዳለፉ፤ ተከሳሿ ድንበር አልፈው የገነቡት ግንባታ ካለ በራሳቸው ወጪ አፍርሰው እንደሚለቁና ያለፉትንም ትርፍ ቦታ ለከሳሽ እለቃለሁ በማለት መፈረማቸውንና የተያዙ ቃለ ጉባኤዎችን ጭምር አካቶ በተባለው ቀን ለፍርድ ቤቱ መላኩን ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው ይሄን ምላሽ ሲሰጡ የዝግጅት ክፍላችን የሰሜን ሸዋ ዞን መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች እና የገርበ ጉራቻ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ለፍርድ ቤቱ የላኩት መረጃ እንዴት ሊጣረስ ቻለ? እናንተስ እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ልዩነቱ እንዴት ሊመጣ ቻለ ብላቹህ ወርዳቹህ ፈትሻችኋል ወይ? ከከተማ አስተዳደሩ ፅህፈት ቤት ጋርስ ተናባቹኋል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳላቸው ሲሆን፤ እርሳቸውም በምላሻቸው የገርበ ጉራቻ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ለፍርድ ቤት የላኩትን መረጃ አላየነውም። ብናየው ኖሮ ልዩነቱ እንዴት መጣ በሚል ይፈተሽ ነበር። ነገር ግን ፍርድ ቤቱም ከታችኛው ጽህፈት ቤት ጋር አብራቹሁ ሰርታችሁ ላኩ ብሎ ትዕዛዝ ስላልሰጠ ባለሙያዎቹ ፍርድ ቤቱ ባዘዘው ትዕዛዝ መሰረት ሰርተው ሪፖርት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የዝግጅት ክፍላችንም አክሎ ቅሬታ አቅራቢው ባለሙያዎቹ በጥቅም ተደልለው የተዛባ መረጃ ለፍርድ ቤቱ ከመስጠት ባለፈ እርሳቸው እንደተስማሙ አድርገው አጭበርብረው አስፈርመውኛል የሚል ቅሬታ አላቸው። ስለዚህ በባለሙያዎቹ የሰሩት የማጣራት ስራ ምን ያህል ተገቢነው የሚለውን እንደገና የሚፈተሽበት አግባብ አለ ወይ? በባለሙያዎቹ የተላከው መረጃ ምን ያህል ትክክል ነው የሚለውን ወርዳቹህ ለማጣራትስ ምን ያህል ቁርጠኝነቱ አለ በሚል ጥያቄ አንስተንላቸዋል።

አቶ ኡርጌም እንደገለጹት ቅሬታ አቅራቢዋ ለፍርድ ቤቱ በተላከው መረጃ ላይ ቅሬታ ካላቸው መጥተው ቅሬታ ማቅረብ ይችሉ ነበር። ነገር ምን አይነት ቅሬታ ባልቀረበበት የዞኑ ጽህፈት ቤት ለፍርድ ቤቱ የላከውን መረጃ ትክክለኛ ነው አይደለም ተብሎ ለመናገር አይቻልም። ስለዚህ ቅሬታ አቅራቢዋ ቀርበው ለጽህፈት ቤቱ ቅሬታቸውን ካቀረቡ ዞኑ ላይ እና ከተማ አስተዳደሩ ላይ ያለውን መረጃ በማመሳከር የትኛው ትክክል ነው አይደለም የሚለውን ማረጋገጥ ይቻላል።

በጥቅሉ ቅሬታ አቅራቢዋ ቅሬታ አለኝ ካሉ ቀርበው ቅሬታቸውን ካቀረቡ ዛሬም ቢሆን ቅሬታቸው የማይታይበት ምንም አግባብ የለም። ስለዚህ ጽህፈት ቤቱም ቅሬታ አቅራቢዋ ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት ወርዶ ፈትሾ የዞኑ ጽህፈት ቤት የላከው መረጃ ላይ ስህተት ካለ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ በጽህፈት ቤቱ በኩል ባለሙያዎቹ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013

Exit mobile version