Site icon ETHIO12.COM

«ክረምቱ ሰብዓዊ ድጋፉን እንዳይገታው መሠረተ ልማቱን መልሶ የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ነው» ሌ/ጀ ዮሐንስ ገብረመስቀል

«ክረምቱ ሰብዓዊ ድጋፉን እንዳይገታው መሠረተ ልማቱን መልሶ የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ነው» ሌተና ጀነራል ዮሐንስ ገብረመስቀል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ

በትግራይ ክልል በነበረው ችግር መሠረተ ልማቱ በተለይ ድልድዮች በመጎዳታቸው ክረምት ገብቶ የሰብዓዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተና ጀነራል ዮሐንስ ገብረመስቀል አስታወቁ፡፡

ሌተና ጀነራል ዮሐንስ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ከተከሰተው ጉዳት አኳያ ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እስካሁን ብዙ ርቀት የተኬደ ሲሆን የተጎዱ መሠረተ ልማቶችንም መልሶ ለመገንባት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

እንደ ሌተና ጄኔራል ዮሐንስ ገለፃ፤ በክልሉ በሰላም ማስከበር ሂደቱ ለጉዳት የተዳረጉ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ወደሥራ የማስገባት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ለአብነትም ተቋርጦ የነበረው የባንኮች አገልግሎት በአብዛኛው ተከፍቶ እንዲሰራ ተደርጓል፡፡መብራትና ስልክም ቢሆን በተያያዥ ወደ 75 በመቶ በላይ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ይሁንና ከመንገድ ጋር የተያያዙ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመዋል፡፡በተለይም ድልድይ ላይ የደረሰው ጉዳት በቀላሉ የሚፈታ ስላልሆነ ብዙ ነገሮችን እየገታ ይገኛል፡፡ሰብዓዊ ድጋፉ ሕዝቡ በሚፈልገው ልክ እንዳይደርስ እንቅፋት ከሆኑ ነገሮችም ውስጥ አንዱ ይህ ነው፡፡

ክረምቱ የባሰ ፈተና ውስጥ እንዳይከተን ሥራዎቹ በቀላሉ የሚፈቱበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል ያሉት ጄኔራል ዮሐንስ፤ ጊዜው ክረምት የሚገባበት ወቅት ነው ፈጠን ብለን ይህንን የማስተካከል ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ያሉት ሌተና ጄኔራል ዮሐንስ፤ ድልድዮቹን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባትም ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል ብለዋል፡፡ via -(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version