Site icon ETHIO12.COM

ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ በሸኔ ታጣቂዎች ተገደለ

የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔት ዎርክ / ኦቢኤን ጋዜጤኛ ሲሳይ ፊዳ በሸኔ ታጣቂዎች መገደሉን የሚሰራበት ተቋም የቄለም ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያን ጠቅሶ ይፋ አደረገ። ሲሳይ የተገደለው ማህበራዊ ህይወቱን እያከናውነ ባለበት ወቅት መሆኑ ታውቋል።

ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ ትላንት ከቀኑ 11፡30 አካባቢ ከሰርግ ሲመለስ በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ ተዘጋጅተው በጠበቁት ሁለት የሸኔ ታጣቂዎች ነው ብበጥይት ተደብድቦ የተገደለው።

የግድያ ወንጀሉ መፈፀሙን በቄለም ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ሰላም አስከባሪ ምክትል ዳሬክተር ኢኒስፔክተር አህመድ ያሲን ናቸው ለኦቢኤን ያስታወቁት። ኢንስፔክተሩ የነብሰገዳዮቹ ማንነት መታወቁን አመልክተዋል።

“የወንጀሉ ፈፃሚዎች ማንነት ተደርሶበታል። በቅርብ ክትልል እየተደረገ ነው” በማለት የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ዳይሬክተር ተናግረዋል። ጋዜጠኛ ሲሳይ መልካም ስነ -ምግባር ያለውና ሕዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ሃቅ ላይ ተንተርሶ በትጋት የሚሰራ ጠንካራ ጋዜጠኛ እንደነበር መስሪያ ቤቱ ምስክሩን ሰጥቷል።

ባለሙያዎችን፣ ሰላማዊ ሰዎችንና የቤተሰብ ሃላፊዎች የግል ማህበራዊ ጉዳያቸውን ሲያከናውኑ እየጠበቁ መግደል፣ ቤተሰቦቻቸውን ከማይረሳ የሃዘን ጨለማ ውስጥ መክተትና ልጆቻቸውን ከህሊና ከማይጠፋ ሰቆቃ ላይ መጣል በምንም መስፈርት ለኦሮሞ ህዝብ የሚደረግ ትግል ሊሆን እንደማይችል በተደጋጋሚ የማህበረሰቡ አባላት የሚናገሩት ጉዳይ ነው።

በተለያዩ ጊዜያት ህጻናት ፊትና አደባባይ ጎዳና ላይ ወላጆችን መንድፋት የተለመደና በርካታ የክልሉን ነዋሪዎች ያማረረ ጉዳይ መሆኑንን የተጎጂ ቤተሰቦች በተደጋጋሚ አስታውቀዋል። እያነቡ ” ምን በድለን” ብለዋል። ሸኔ ይህንን የሚፈጽመው ለምን እንደሆነ ይፋ አለመግለጹ ደግሞ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። እስካሁን ከሸኔ በኩል ምንም የተሰማ ነገር ባይኖርም ዛሬ ማታ በናኮር መልካ አማካይነት እንደተለመደው በቪኦኤ ማስተባበያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።


Exit mobile version