Site icon ETHIO12.COM

የእኛ ሰው በጋዛ

አበራ መንግስቱ የተወለደው ጎንደር ነው። በአምስት አመቱ ከቤተሰቡ ጋር ወደ እስራኤል አቅንቶ ሰሞኑን ሃማስ በተደጋጋሚ ሮኬት የሚተኩስባት አሽኬሎን የተባለች ከተማ ይኖር ነበር።

በሀገረ እስራኤል በታላቅ ወንድሙ ሞት የከፋ ሀዘን የደረሰበት አበራ በተለይ ከአስር አመት በፊት ለአእምሮ ሕመም ይደረጋል። ተረጋግቶ መስራት አልቻለም። ቆይቶ ከእነ አካቴውም ሰራውን ትቶት ገንዘብ ሲቸግረው ከቤተሰብና ጓደኞቹ እየጠየቀ እግሩ ወደመራው መዞር አበዛ። ቤተሰቦቹ በተደጋጋሚ ወደ ህክምና ተቋም ወስደውታል። ግን አልተሻለውም። ሰውነቱን በስለት እየበጣ ደሙን ማፍሰስ ጨምሮ ሕይወቱን ለአደጋ የሚዳርግ ተግባር በራሱ ላይ ይፈፅም ነበር። ሀኪም ቤት ተወስዶ የተሰጠውን መድሃኒት በአግባቡ አይጠቀምበት። አጋች እጅ ሊገባ ከቀናት በፊት ሀኪም ቤት ተወስዶ የተሰጠውን መድሃኒት የትም ከበተነው በኋላ ቤተሰቦቹ ገንዘብ እንዲሰጡት ሲጠይቅ ፈቃደኛ አልሆኑለትም። ተነስቶ የት እንደሄደ ሳይታወቅ ቀናት ያልፋሉ። ቤተሰቦቹ ለሁለት አመታት ሲያደርግ እንደነበረው ሰነባብቶ ይመለሳል ብለው ተስፋ አድርገዋል። በመሃል ከወደጋዛ ሀማስ የእስራኤልን ሰላይ እንዳሰረ አድርጎ በዜና ያስወራል። የአእምሮ ህመም የሚያሰቃየውን፣ መድሃኒትም ምግብም በቅጡ የማይወስደውን፣ ለሁለት አመታት ራሱን ያጎሳቆለውን አበራ መንግስቱ ነበር በሰበር ዜና መነጋገሪያ የሆነው። አበራ እስራኤልን ከመዞር አልፎ ወደጋዛ አቋርጦ ሲገባ ያጋጠመው የሀማስ አሰቃቂ ምርመራና እስር ነው። ሌላ ክርክር ሲመጣባቸው ደግሞ መደራደሪያ አደረጉት።

ይህ ከሆነ ሰባት አመታት አልፈዋል። በወቅቱ ቤተ እስራኤላዊያን የቻሉትን ጫና አድርገዋል። ቤተሰቦቹ ግራ እየገባቸውም የልጅ ጉዳይ ሆኖባቸው ብዙ ደክመዋል። ከእስራኤል ተቋማት እስከ ጀኔቫ ድረስ ደጅ ጠንተው “ልጃችን ታማሚ ነው። አስለቅቁልን” ብለው አልቅሰዋል። ለሃማስ ደግሞ ዓለም አቀፍ ጫናው እስረኛ እንዲፈታ አያደርገውም። እስረኛው ዋጋ እንደሚያወጣ ማሳያ፣ የራሱን አጀንዳ ማጉያው ነው።

ወቅቱ እንደአሁኑ ማሕበራዊ ሚዲያ ዘምቶ በብዙ ሕዝብ ዘንድ መሰማት እድል አልነበረውም። በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያውያን እክል ሲገጥማቸው ወገኖቻቸው ጉዳያቸውን አጀንዳ ያደርጉላቸዋል። በቂ ባይሆንም በቅርቡ ቻይና እና ቱርክ እስር ላይ የሚገኙ እህቶቻችን ጉዳይ መጥቀስ ይቻላል። በእርግጥ አበራ በሀማስ ከመያዙ በፊት ሶማሊያ ውስጥ ሰው ገድለሃል ተብሎ ሕይወቱ ሊያልፍ የነበረው ኢትዮጵያዊ ጉዳይ በወገኖቹ ዘንድ መነጋገሪያም ነበር። በወገኑ ጩኸትና በአርቲስት ቴዲ አፍሮ እገዛም ከእስር ቤት እንደወጣ በጊዜው ተዘግቧል። አበራ ይህን እድል አላገኘም።

አበራ የታሰረው ጋዛ ውስጥ ነው። በሀማስ እጅ ነው የወደቀው። ሀማስ በገንዘብም በሕዝብ ጩኸትም እስረኛ አይፈታም። በሕዝብ ጩኸት ቢሆን ከሕዝብ ያለፈ ተቋማት ጥረት አድርገዋል። ሚዲያዎች ዘግበውታል። በገንዘብ ቢሆን ቤተሰቦቹ ባይችሉ እስራኤል ሚሊዮን ዶላሮችን ትከፍል ነበር። የአበራን ጉዳይ ያከበደው ሀማስ አመለካከትና አሰራር ነው። ለሀማስ እስረኛ የሚያሰቃዩት፣ ወይንም አስረው የሚያስቀምጡት፣ አሊያም የሚበቀሉት ብቻ አይደለም። የታሰሩበትን ሁሉ በአንዴ አስፈታበታለሁ የሚለው የእስር ቤት መክፈቻ ቁልፍ ነው። አንድ እስራኤላዊ አግቶ ወይንም አስሮ ከመቶ እስከ ሺህ የሚደርሱ እስረኞች እንዲፈቱለት መደራደሪያ ያደርገዋል። የአእምሮ በሽተኛውን አበራ መንግስቱንም የእስራኤል ጦር ሰራዊት አባል አስመስሎ በእስራኤል የተያዙ እስረኞች እንዲፈቱለት ከፍ ያለ መደራደሪያ አድርጎት እንደነበር በወቅቱ ተገልፆአል።

ይሁንና አበራ የእስራኤል ሰራዊት ምልመላ ላይ “ብቁ አይደለህም” ተብሎ ተመልሷል። ለአመታት የአእምሮ ጤና ህክምና የተከታተለበትን መረጃዎች ይፋ ተደርገዋል። የአበራ ቤተሰቦች እነዚህን መረጃዎች ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት አድርሰው፣ ተቋማቱ በሀማስ ላይ ጫና አድርገዋል። ሀማስ ግን አበራ የእስራኤል ጦር ሰራዊት አባል እንደነበር አስመስሎ በፎቶ ሾፕ የተሰራ ምስል እየለጠፈ በማስተባበል ታጋቹን የእስረኛ ማስፈቻ ቁልፍ አድርጎት ለመጠቀም ብዙ ርቀት ሄዳል።

የዓለም አቀፍ ተቋማት አበራ የአእምሮ ህመም እንዳለበትና በእስራኤል ሰራዊት ውስጥ እንዳልነበር ያላቸውን ማስረጃ በማቅረብ ሃማስ ላይ ጫና ሲያደርጉ ሀማስ እንዲሁ ከመልቀቅ በተወሰኑ እስረኞች ሊደራደር ፍላጎት እንደነበረው መረጃዎች ወጥተው የነበር ቢሆንም ደጋፊዎቹ ጫና ያደርጉብኛል በማለት እንዳልገፋበት ተነግሯል። በሃማስና ደጋፊዎቹ ዘንድ አንድ እስረኛ በመቶና በሺህ ሰው ካልተቀየረ “በርካሽ ቀየርከው” ይባላል።

አበራ ከመያዙ ከሁለት ወር በፊት ሀማስ ሶስት እስራኤላዊያንን አግቶ በመግደሉ ምክንያት የተቀሰቀሰና ሶስት ሳምንታትን የቆየ ከባድ ጦርነት መደረጉ ይታወሳል። የአበራ ጉዳይ በዓለም ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ ከነበረው ጦርነት በኋላ የተፈጠረና ብዙም ትኩረት ያላገኘ ነው ማለት ይቻላል። ለተወሰኑ ጊዜያት የሰብአዊ መብት ተቋማት ውትወታ፣ የቤተሰቦቹ ውጣ ውረድ በኋላ የአበራ ጉዳይ ተረስቷል። በህመም እየተሰቃየ፣ ከቤተሰብ ጋር፣ የተሻለ ህክምና በሚያገኝበት ሀገር እስራኤል ያልተሻለው አበራ በሀማስ እስር ቤት ውስጥ በሕይወት ስለመቆየቱም እርግጠኛ መሆን አይቻለም። ከእነ ሕመሙ በሕይወት ካለ ደግሞ ሰሞኑን የዓለም ዜና በሆነችው ጋዛ በአሸባሪው ሀማስ እስር ቤት ውስጥ ምን ያህል ስቃይ እያሳለፈ እንደሆነ መገመት ከባድ ነው። በሀማስ እጅ የገባው አበራ ጉዳይ በሌሎች ዘንድ ቢዘነጋም ለቤተሰቡ ግን ምስቅልቅል ጥሎ አልፏል። ልጃቸውን ለማስፈታት ሲከላተሙ የነበሩት ላይ በርካታ ችግሮች ደርሰዋል። ዛሬ ይህ ጦርነት ሲቀሰቀስ የአበራ ቤተሰቦች ለአመታት የተዘነጋው የልጃቸው ጉዳይ እንደገና ያሳስባቸዋል። በሕይወት ካለ በድብደባው የሚጎዳ ይመስላቸዋል። ሀማስና አጋሮቹ የሚጎዱት ይመስላቸዋል። ምን አልባት ከጦርነቱ በኋላም በታሰሩ ሰዎች፣ በተያዙ አስከሬኖች ድርድር ይፈታልን ይሆን ብለው ተስፋ ያደርጉም ይሆናል።

ኢትዮጵያውያን በብዙ ዓለም ሀገራት ሲኖሩ በርካታ ችግሮች ይገጥማቸዋል። የእኛ ሰው በአሜሪካ በሰው ይገደላል። የእኛ ሰው በቻይና፣ በቱርክ እስር ቤት አሳዛኝ ሕይወት ያሳልፋል። የእኛ ሰው በአረብ ሀገራት ጎዳና ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ይሞታል። በእስር ይሰቃያል። የእኛ ሰው የመን ውስጥ ታስሮ የሚያየው ፍዳ ዘግናኝ ነው። የእኛ ሰው ባሕር ሲያቋርጥ የአሳ ቀለብ ይሆናል። የእኛ ሰው በሶማሊያ ተይዞ ተሰቃይቷል። የእኛ ሰው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያቀና ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ… እጅግ አስከፊ እስር ያጋጥመዋል። የእኛ ሰው ሊቢያ ላይ በአይ ኤስ በአሰቃቂ ሁኔታ ታርዷል። ብዙዎቹን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እናስታውሳለን። የማናስታውሳቸው ብዙዎች ናቸው። አበራ ከዘነጋናቸው መካከል ነው። በሕይወት ካለ የሚገኘው በአሸባሪ እስር ቤት ነው፣ በአውሮፕላንና በሚሳኤል በምትደበደብ የዋይታ ከተማ እስር ቤት ውስጥ፣ ጋዛ።

Via – Getachew Shiferaw

Exit mobile version