Site icon ETHIO12.COM

እነ ስብሃት ነጋና ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤት ” የፍርድ ሂደት ለማጓትት ነው” ሲል ጣለው

አቶ ስብሃት ነጋ እና ሌሎች 41 የህወሃት የሲቪል እና ጦር አመራሮች ላይ ክርክር የተጀመረዉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች የሽብር እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን ማፍረስ ወንጀል መፈፀማቸውን በማስረጃ ስላረጋገጥኩኝ ክስ ከመመስረቱ በፊት የምስክሮችን ቃል ጠብቆ ለማቆየት የቀዳሚ ምርመራ ተካሂዶ የምስክሮች ቃል እንዲመዘገብ ለፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም በጽሁፍ ባቀረበው አቤቱታ መነሻነት አቤቱታ ቀርቦ የነበረው፡፡

በዚሁ መሰረትም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በቀዳሚ ምርመራ ሂደቱ ቀርበዉ እንዲደመጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ተከሳሾች በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አቤቱታዎችን ቢያቀርቡም ጥያቄዎቻቸው ከህግ አንጻር ተቀባይነት ሳያገኙ እየቀረ ቆይቷል፡፡

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠዉ ብይን የተከሳሾች አቤቱታ አቀራረብ ፍትህን ለማዘግየት ታስቦ ተከፋፍሎ የቀረበ መሆኑን በመግለጽ የቀረቡትን ጥያቄዎች ተችቶ ብይን በመስጠት የተጀመረው የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን የመስማት ሂደት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ብይን የሰጠባቸዉ አቤቱታዎች በመሰረታዊነት ሁለት ጭብጥ የያዙ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ተከሳሾች የተለያዩ ህጎች ላይ የህገ-መንግስት ትርጉም እንዲሰጥ ጉዳዩ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ የሚጠይቅ ሲሆን ሌላኛው ጭብጥ በዚሁ መዝገብ ስር ጉዳያቸው እየታየ ካሉ ተከሳሾች መካከል 10 ተከሳሾች በግል ሃኪም ለመታከም እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት አቤቱታ ነዉ፡፡

ተከሳሾች የህገ-መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት ፍርድ ቤቱ ለህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ እንዲመራላቸዉ የጠየቋቸው የህግ ጉዳዮች፡-

(1) የትግራይ ክልል ምክር ቤት ያወጣዉ የምርጫ አዋጅ ህገ-መንግስታዊነት፤

(2) የትግራይ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ምክር ቤት ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም ያወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህገመንግስታዊነት፤

(3) የምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ህገ-መንግስታዊነት እንዲሁም

(4) የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 19 እና 20 በቀዳሚ ምርመራ ክርክር ላይ ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሁኔታን የሚመለከቱ ነበሩ፡፡

ፍርድ ቤቱም የምስክር እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጁ እና የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 19 እና 20 በቀዳሚ ምርመራ ክርክር ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ በተመለከተ በቀደመ የችሎት ውሎ በተካሄደ ክርክር የህገ-መንግስት ትርጉም የማያስነሱ መሆናቸዉ የተወሰነ በመሆኑ ትርጉም አያስፈልጋቸዉም በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡

ይሁንና ቀሪ ጉዳዮችን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል ጠብቆ ለማቆየት የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ቃል ከመስማት በዘለለ መደበኛ ሙግት የማይሰማ በመሆኑ ወደ ፊት መደበኛውን ክርክር ለመዳኘት ስልጣን ያለዉ የፌዴራሉ ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት የሚያከራክርባቸው ጉዳዮች ናቸው ሲል ጥያቄዎቹን ሳይቀበላቸው ቀርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ብይኑን በሰጠ ጊዜም ይህም ሆኖ ተከሳሾች በጉዳዩ ላይ ክርክር ቢኖራቸዉ እንኳ በመጀመርያዎቹ ቀጠሮዎች ማቅረብ ሲገባቸዉ በየጊዜዉ ጥያቄዎችን እየከፋፈሉ ማቅረባቸዉ ፍትህን ለማዘግየት በማሰብ ነዉ በማለት የጥያቄ አቀራረቡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርኣት ህግ የተደነገገውን የአቤቱታ አቀራረብ ስርኣትን ያልተከተለ ነዉ በማለት ተችቶታል፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾች በግላቸዉ ለመታከም ያቀረቡትን ጥያቄ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ያቀረቡት ተከሳሾች ህክምናቸውን ባሉበት ማረምያ ቤት ሆነዉ እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነገር ግን በግል ሃኪሞቻቸው መታከም የግድ ከሆነና የግል ሃኪሙ ተገቢውን ምርመራ አድርጎ በሆስፒታል ሆነዉ እንዲታከሙ የሚያዝ ከሆነ ብቻ በጠባቂዎች ታጅበዉ መታከም እንደሚችሉ ወስኗል፡፡በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የተጀመረዉ የዐቃቤ ሕግን ቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች መስማት ሂደት እንዲቀጥል በማዘዝ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከግንቦት 17 ቀን 2013 ጀምሮ እንዲሰሙ ቀጠሮ ሰጥቶ ምስክሮች እንዲቀርቡ በማዘዝ የእለቱ የችሎት ውሎ ተጠናቅቋል፡፡

ምንጭ – ጠቅላይ አቃቤ ህግ


Exit mobile version